ስለዓለም ዋንጫው የምድብ ድልድል ዕጣ አወጣጥ ሊያውቋቸው የሚገቡ ነጥቦች

32 ሃገራትን የሚያሳትፈው የሩሲያው ፊፋ 2018 የዓለም ዋንጫ የመጨረሻው የምድብ ድልድል የዕጣ ማውጣት ስነስርዓት ዛሬ (አርብ) አመሻሹ ላይ በሞስኮ፣ ክሪሚሊን ይከናወናል። ተከታትዩ ፅሁፍም ስለምድብ ድልድል ዕጣ አወጣጡ ሊያውቋቸው የሚገቡ መሰረታዊ ነጥቦችን ያስቃኝዎታል።

የምድብ አባቶች እነማን ናቸው?

አዘጋጇን ሃገር ሩሲያን ጨምሮ ባፊፋ/ኮካ ኮላ የዓለም ሃገራት የጥር ወር ደረጃ መሰረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ጀርመን፣ ብራዚል፣ ፖርቱጋል፣ አርጄንቲና፣ ቤልጂየም፣ ፓላንድና ፈረንሳይ በምድብ አባትነት በመጀመሪያው ከዕጣ ማውጪያ ቋት ውስጥ የተቀመጡ ሃገራት ናቸው።

የመጨረሻው የዕጣ አወጣት ስርዓት በስንት ሰዓት ይከናወናል? 

የዕጣ ማውጣት ስነስርዓቱ በሩሲያም ሆነ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር አመሻሹ ላይ 12፡00 ይጀምራል።

የዕጣ ማውጣት ስነስርዓቱ የት ይከናወናል?

የዕጣ ማውጠት ስነስርዓቱ 6,000 ሰዎችን መያዝ አቅም ባለው የሞስኮው ክሬሚሊን ቤተመንግስት የሚገኝ የኮንሰርት አዳርሽ ውስጥ የሚከናወን ነው። አዳራሹ ከዚህ ቀደም እንደ ሉቺያኖ ፓቫሮቲ፣ ፕላሲዶ ዶሚንጎ፣ ኹልዮ ኢግሊሲየስ እና ኤልተን ጆን ያሉ የዓለማችን አንጋፋ ሙዚቀኞች ስራዎቻቸውን ያቀረቡበት ከመሆኑም በተጨማሪ በለ ሲርኩ ዱ ሶሊየል አማካኝነት በርካታ የኦፔራ እና የባሌት ጥበባዊ ስራዎች ቀርበውበታል።

የዕጣ ማውጣት ስነስርዓቱን ማን ይመራዋል?

በ1986ቱ የሜክሲኮ የዓለም ዋንጫ የወርቅ ጫማ አሸናፊው እና የቀድሞው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን የፊት መስመር ተጫዋቹ ጋሪ ሊንከር ከሩሲያዊቷ የስፖርት ጋዜጠኛ ማሪያ ኮማንዳንያ ጋር በእግርኳሱ ዓለም ታላቅ ስም ተክለው ካለፉት ፈረንሳዊው ላውረን ብላ፣ እንግሊዛዊው ጎርደን ባንክስ፣ ብራዚላዊ ካፉ፣ ጣሊያናዊው ፋቢዮ ካናቫሮ፣ ኡራጓዊው ዲያጎ ፎርላን፣ አርጄንቲናዊው ዲያጎ ማራዶና፣ ስፔናዊው ካርሎስ ፑዮል፣ እና ሩሲያዊቷ ኒኪታ ሲሞንያን በመታገዝ የዕጣ ማውጣት ስነስርዓቱን በመደረኩ ላይ ይመሩታል።

ወደዓለም ዋንጫው ያለፉ ሃገራት እንዴት በአራቱ የዕጣ ድልድል ማውጫ ቋት ውስጥ ተለይተው ሊቀመጡ ቻሉ?

ሩሲያ ብቻ በአዘጋጅነቷ የመጀመሪያው የምድብ አባት ቋት ውስጥ በቀዳሚነት ስትገባ የጥር ወሩ የፊፋ/ኮካ ኮላ የዓለም ሃገራት የብቃት ደረጃ  የተቀሩትን 31 ሃላፊ ሃገራት በአራት የዕጣ ማውጫ ቋት ውስጥ እንዲሰደሩ ምክኒያት ሆኗል። 

የመጨረሻው የዕጣ ማውጣት ሂደቱ ምንምን ይመስላል?

ስምንት ስምንት ሃገራትን በመለየየት 32 ሃገራቱን በአራት አራት ቦታ ከፍሎ ያስቀምጠው የዕጣ ማውጫ ቋት ባዶ እስኪሆን ድረስ ተራ በተራ አራት ኣራት ቡድኖችን የያዘ ስምንት ምድብ ይሰራል (ከምድብ ኤ እስከምድብ ኤች ድረስ)። አዘጋጇ ሩሲያ በምድብ ኤ የመጀመሪያ የምድብ አባት ሆና መጀመሪያው ቦታ ላይ ስትቀመጥ ሌሎቹ በእሷ ቋት ውስጥ የሚገኙት ሰባት ሃገራት ግን ከቢ እስከ ኤች ባሉት የተቀሩት ምድቦች ላይ በቀዳሚነት የምድብ አባት ሆነው ይቀመጣሉ። ቀሪ የቡድኖቹ የምድብ ቦታዎች (ቋት 2፣ 3 እና 4 ላይ የሚገኙት)፣ በሚደረገው የዕጣ ማውጣት እንደየዕድላቸው የምድብ ቦታቸውን የሚያገኙ ይሆናል።

14 ሃገራትን በውድድሩ ላይ ከሚያሳትፈው የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር ሃጋራት ውጪ በስምንቱ ምድብ ውስጥ በተመሳሳይ ኮንፌዴሬሽን ላይ የሚገኙ ሃገራት በአንድ ምድብ ውስጥ አይመደቡም።

Advertisements