አርሰናል ከ ዩናይትድ / የሞውሪንሆ ስብስብ ለነገው ጨዋታ ሶስት ተጫዋቾቹን በጉዳት ሲያጣ ወሳኝ አማካኙን ማሰለፉም አጠራጣሪ መሆኑ ተገለፀ


ጆሴ ሞውሪንሆ ከነገው የአርሰናል ወሳኝ ጨዋታ በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የማቲች መሰለፍ አጠራጣሪ መሆኑን ገልፀው ፊል ጆንስ፣ ኤሪክ ቤሊ እና ማርዋን ፌላኒ በበኩላቸው ከጨዋታው ውጪ መሆናቸውን አስታውቀዋል።  

ዩናይትድ ነገ ምሽት ወደ ኢምሬትስ የሚያመራው ከመሪው ማንችስተር ሲቲ በስምንት ነጥቦች ርቆ ሲሆን በነገው ጨዋታ የሚሸነፍ ወይም በአቻ ውጤት የሚጨርስ ከሆነና ሲቲ በበኩሉ በሜዳው ኢትሀድ ስታዲየም ዌስትሀምን ካሸነፈ ልዩነቱ ይበልጥ የሚሰፋ ይሆናል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም የኦልትራፎርዱ ክለብ ከተጠባቂው ጨዋታ በፊት ያጋጠመው የተጫዋች ጉዳት በክለቡ ውስጥ ጭንቀት የፈጠረ ሲሆን ፖርቹጋላዊው የክለቡ አለቃ በሰጡት መግለጫም ተከላካዮቻቸው ጆንስና ቤሊ እንዲሁም የጉልበት ጉዳት ያለበት ፌላኒ ከነገው ፍልሚያ ውጪ መሆናቸውን ማረጋገጫ ሰጥተዋል። 

በሌላ በኩል ከዋትፎርድ ጋር በነበረው ጨዋታ ጉዳት የገጠመው ማቲች ከነገው ትንቅንቅ ውጪ እንደሆነ ተገልፆ የነበረ ቢሆንም በነገው ዕለት የመሰለፍ መጠነኛ እድል እንዳለ ሞውሪንሆ በመግለፅ ለቡድኑ ደጋፊዎች ተስፋን የሚሰጥ አስተያየት ሰጥተዋል።

ሞውሪንሆ በንግግራቸው “ማቲች አጠራጣሪ ነው። እንደሚደርስ (ለነገው ጨዋታ) ተስፋ አደርጋለሁ። ነገርግን አብሮን ይኖራል ብዬ ማረጋገጫ ልሰጥ አልችልም። እስቲ ከጨዋታው በፊት ያለውን ስሜትና የማሟቅ መንፈስ እንመልከት። 

“እንደማስበው ይመለሳል። እኔም እሱም እንዲመለስ እንፈልጋለን። ነገርግን ማረጋገጫ መስጠት የማልችል ሲሆን ፌላኒ በበኩሉ ከቡድናችን ጋር አልተጓዘም።” በማለት የማቲች መኖር ወሳኝ መሆኑን ነገርግን በነገው ጨዋታ ብቁ ሆኖ በመመለሱ ዙሪያ ማረጋገጫ መስጠት እንደማይችሉ አስረድተዋል።

ሞውሪንሆ ህዳር 2014 ላይ የቼልሲ አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት ሊቨርፑልን በሜዳው አንፊልድ 2-1 ከረቱ ወዲህ በስድስት የሊጉ ትልልቅ ቡድኖች ላይ ምንም ጨዋታ ከሜዳቸው ውጪ ማሸነፍ ያልቻሉ ሲሆን ባለፈው የውድድር ዘመን ዩናይትድ በቼልሲ፣ ቶትነሀም እና አርሰናል ሲሸነፍ ከሲቲና ሊቨርፑል ጋር በአቻ ውጤት ጨዋታውን መፈፀሙ አይረሳም። 

በሌላ በኩል ዩናይትድ ህዳር 2014 ላይ አርሰናልን በኢምሬትስ ከረታው ወዲህ መድፈኞቹን በሜዳቸው ማሸነፍ ያቃተው ሲሆን የአርሰን ሼንገር ስብስብ በበኩሉ የነገውን ጨዋታ የሚጀምረው በሜዳው ተከታታይ 12 ድል አስመዝግቦ መሆኑ የኦልትራፎርዱን ስብስብ ፈተና እንደሚጨምረው ይጠበቃል።

የቡድኑ ፖርቸጋላዊ አለቃ በበኩላቸው ግን ስብስባቸው ከሜዳው ውጪ ትልልቆቹን ሲገጥም ከሚከተለው የጥንቃቄ አጨዋወት በተቃራኒው የሼንገርን ስብስብ አጥቅቶ ለመጫወት እንደተዘጋጀ ቃል የገቡበትን አስተያየት ሰጥተዋል።  

ሞውሪንሆ በንግግራቸው “ኳስን ስናገኝ በ 11 ተጫዋቾቻችን በሙሉ ለማጥቃት እንሄዳለን። ምክንያቱም ኳስ በእኛ ስር ሲሆን በረኛው ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቃል። አርሰናል ኳስ በሚይዝበት ወቅት ደግሞ በ 11 ተጫዋቾቻችን እናጠቃለን።

“በጊዜ በጊዜ ሂደት ጨዋታን እጫወታለሁ። የአጨዋወት መንገዴም እሱ ነው። በትናንትናው ዕለት ቦርግ ከ ማክኖር (Borg vs. McEnroe) የሚል አስደሳች ፊልም ስመለከት ነበር። 

“እናም በፊልሙ ላይ የቦርግ አሰልጣኝ በመሀል በመሀል ስለአንድ ነጥብ እንዲያስብ የሚነግረው (ለቦርግ) ሲሆን እኔም ለተጫዋቾቼ ስለጨዋታው ብቻ እንዲያስቡ ነግሬያቸዋለሁ። አርሰናል ነው። በቃ ጨዋታ ብቻ ነው። ከጀርባው ስንት ነጥብ እንዳለ አናስብም። 

“በቃ አርሰናል ነው። በሌሎች ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ለእኛ አስቸጋሪ ነው። በጨዋታው ላይ ማተኮር ብቻ ነው።” በማለት ቡድናቸው ትኩረቱ ጥሩ ጨዋታ በማድረግ ላይ እንጂ ነጥብ በማግኘት ላይ እንዳልሆነ ለማስረዳት ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል።

Advertisements