አሳሳቢ / በስታዲየም ስርዓት አልበኝነት ላይ የሚመክር የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ተካሄደ

“በስታዲየም ስርዓት አልበኝነት አሸናፊ የለም” በሚል መሪ ሀሳብ በሀገራችን እየታዩ ባሉ የስታዲየም ስርዓት አልበኝነት ዙሪያ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ዛሬ በአዘማን ሆቴል ተደርጓል።

ይህ የተለያዩ ክለቦች አስተዳዳሪዎች፣ የደጋፊ ማህበራት አባላት፣ አስጨፋሪዎች፣ የስፖርት መገናኛ ብዙሀን ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈው የውይይት መድረክ የስታዲየም ስርዓት አልበኝነትን የተመለከተ ጥናታዊ ፅሁፍ የቀረበበት እና ከተሳታፊዎች በችግሮቹና መፍትሔዎቹ ዙሪያ ሀሳብ የተሰነዘረበት ነበር።

የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርን በመወከል በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ፅሁፉን ያቀረበው ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ በስታዲየም አካባቢዎች የሚታዩ ስርዓት አልበኝነቶች ወደለየለት የስታዲየም ነውጠኝነት የመቀየር አዝማሚያ እያሳዩ እንደሆነና አሄዳቸው በቶሎ ካልተቀጨ መዘዛቸው የከፋ እንደሚሆንም የተለያዩ መከራከሪያ ሀሳቦችን እና የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮን እንደ ምሳሌ እያነሳ አስረድቷል።

በመጨረሻም ከተሳታፊዎች ለችግሩ መነሻ እንደምክንያት ተብለው የተጠቀሱ እንዲሁም ደግሞ በመፍትሔ ሀሳብነት የተነሱትን ጉዳዮች በማዳበር በቀጣይ ለሚመለከታቸው አካላት ትልቅ ግብአት ሊሆን የሚችል ጥናታዊ ፅሁፍ ይዞ ለመምጣት ሀላፊነቱ በድጋሚ ለጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ተሰጥቶ የምክክር መድረኩ በስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ጋዜጠኛ ዩናስ ተሾመ የመዝጊያ ንግግር መቋጫውን አግኝቷል።

 

Advertisements