“የአርሰናል አድናቂ ነበርኩ።” – ፖግባ

የማንችስተር ዩናይትዱ ኮከብ ፖል ፖግባ ከፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ሁሉ የአርሰናል ጨዋታ እያየና ክለቡንም እያደነቀ እንዳደገ ገልፃዋል።

ፖግባ እና ማንችስተር ዩናይትድ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ከሚገኘው ማንችስተር ሲቲ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት የማጥበብ ተስፋ ሰንቀው ወደለንደኑ ኤሚራትስ ስተዲየም አቅንተው ዛሬ [ቅዳሜ] ምሽት መድፈኞቹን ይገጥማሉ።

እናም ለፖግባ ይህ ጨዋታ በፈረንሳይ በነበረበት ወቅት ለመመልከት ይወደው የነበረውን ክለብ በተቃራኒ የሚገጥምበት መሆኑን የተለየ ትርጉም ይኖረዋል።

ፖግባ በአርሰናል እንዲማረክ አብይ ምክኒያት የነበረው ደግሞ ክለቡ ከፈረንሳይ ጋር የነበረው ጥብው ቁርኝት ነበር። በተለይም የዩናይትዱ አማካኝ የቴሪ ሆነሪ አድናቂ ነበር።

“በፈረንሳይ እነሱ ትልቅ [ክለብ] ናቸው።” ሲል ፖግባ ከቅዳሜው ጨዋታ በፊት ለፉትቦል ፎከስ ተናግሮ “እነሱ [አርሰናሎች] በጣም ብዙ ፈረንሳዊያን ተጫዋቾች ነበሯቸው። እኔም የአርሰናል አድናቂ ነበርኩ። ቴሪ ሆነሪ ደግሞ እመለከተው የነበረ ተጫዋች ነው።

“ደጋፊነቴ ትንሽ እንጂ ያበዱኩ ደጋፊ ግን አልነበርኩም። ነገር ግን በጣም ብዙ የአርሰናል ጨዋታዎችን ተመልክቻለሁ። እነሱ በጣም ታላቅ ክለብ ነበሩ።” ሲልም ፈረንሳያዊው የቀድሞ የጁቬንቱስ ተጫዋች አክሎ ተናግሯል። 

Advertisements