የኢትዮጵያ ከ 17 አመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከናይጄሪያ አቻው ጋር በአቻ ውጤት ተለያየ

በዩራጋይ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአለም ከ 17 አመት በታች የሴቶች የአለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ የሴት ብሔራዊ ቡድን ከናይጄሪያ አቻው ጋር ተጫውቶ በአቻ ውጤት አጠናቋል።

በአዲስ አበባ ስታድየም ከቀኑ 10:00 ጀምሮ የናይጄሪያ የሴቶች ከ 17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድንን የገጠሙት የኢትዮጵያ የሴትብሔራዊ ቡድን 1-1 ጨዋታውን አጠናቋል።

ብዙ ተመልካች በስቴድየም ተገኝቶ ባልተከታተለው ጨዋታ እንግዶቹ በ 18ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ፕሪሺየስ ቪንሴንት ያሻገረችውን ኳስ ኳስ ጆይ ጄሪ አስቆጥራ መሪ መሆን ችለዋል።

ብዙም ሳይቆዩ በድጋሜ በቀኝ መስመር ላይ ትጫወት የነበረችው ፕሪሺየስ ቪንሴንት ከመሀል የተሻገረላትን ቆንጆ ኳስ የግብ ጠባቂዋ አባይነሽ መውጣት ተከትላ ከፍ አድርጋ የላከችው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቷል።

የኢትዮጵያ የሴት ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያ ግማሽ በቀኝ መስመር ላይ አስፍቶ በትመር ጠንክር አማካኝነት ወደ ፊት ለመጓዝ ጥረት ቢያደርጉም በፍጥነት እና በአካል ብቃት የተሻሉ የነበሩትን ናይጄሪያዎች በቀላሉ ማለፍ ሳይቻላቸው ቀርቷል።

በመጀመሪያው ግማሽ ለባለሜዳዎቹ ሊጠቀስ የሚችለው አጋጣሚ 15ኛው ደቂቃ ላይ ነፃነት መና በቮሊ ለመምታት የሞከረችበት እንዲሁም 31ኛ ደቂቃ ላይ ረድኤት ያልተጠቀመችው ቆንጆ አጋጣሚ ይጠቀሳሉ።

በሁለተኛው ግማሽ የተሻለ ፉክክር የተደረገበት የነበረ ሲሆን ባለሜዳዎቹ የአቻ ጎል ለማስቆጠር ናይጄሪያዎችን ጫን ብለው ለመጫወት ሞክረዋል።

የአቻነቷን ጎልም በድንቅ ሁኔታ 63 ኛው ደቂቃ ላይ ታሪኳ ገቢሶ ከርቀት የመታችው የቅጣት ምት ኳስ ከመረብ አርፏል።ከጎሉ በኋላም ደስታቸውን ከአሰልጣኛቸው ሰላም ጋር በመሆን ገልፀዋል።

ናይጄሪያዎች ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በረጅሙ ከጎል ክልላቸው በማራቅ አለፍ አለፍ እያሉ ደግሞ ለማጥቃት ቢሞክሩም ግልፅ የጎል እድል መፍጠር አልቻሉም።ጨዋታውም ሳይሸናነፉ 1-1 መጠናቀቅ ችሏል።

ሁለቱ ሀገራት የመልስ ጨዋታቸውን በናይጄሪያ ካደረጉ በኋላ አሸናፊው ቡድን ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያልፍ ይሆናል።

Advertisements