መሐመድ ሳላህ የህዳር ወር ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተመረጠ

የሊቨርፑሉ አጥቂ መሐመድ ሳላህ የፕሮፌሽናል እግርኳስ ተጫዋቾች የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የህዳር ወር ምርጡ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል። 

በዚህ የውድድር ዘመን በእንግሊዝ አራት ዲቪዥኖች ላይ በየወሩ ምርጥ ተጫዋቾችን በኦን ላየን የድምፅ አሰጣጥ እያስመረጠ በሚሸልመው ስናክ ሚዲያ አማካኝነት የሊቨርፑሉ የመስመር አጥቂ የወሩ ተሸላሚ ሆኗል።

ሳላህ ባለፉት ሳምንታት ልዩ የሆነ ድንቅ ብቃቱን ያሳየ ሲሆን፣ ለክለቡ የህዳር ወር ውጤታማ ጉዞም ወሳኙን ሚናን ተጫውቷል። ግብፃዊው ተጫዋች በዚህ ወር በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሰባት ግቦችን ማስቆጠር ከመቻሉም ባሻገር በዚህ ወር በሁሉም ውድድሮች ላይ ምንም ሽንፈት ያልገጠመው የየርገን ክሎፑ ቡድን ሶስት ጨዋታዎችን እንዲያሸንፍና በአንዱ ደግሞ በአቻ ውጤት እንዲለያይ ማድረግ ችሏል።

በሚያስደንቅ ሁኔታም የ25 ዓመቱ ተጫዋች ሚና በክለቡ ደጋፊዎች ልብ ውስጥ በቶሎ መግባት አስችሎታል። የቀድሞው የቼልሲ እና ሮማ ተጫዋች የወሩ ምርጥ ተጫዋችነት ድምፅ ማግኘቱ ብቻ ሳይሆን፣ ከተሰበሰበው ድምፅ ከቀሪዎቹ ተጫዋቾች በ36 በመቶ ብልጫ በመውሰድ በ54 በመቶ ድምፅ አሸናፊ መሆን ችሏል። ለማንችስተር ዩናይትድ ወቅታዊ ስኬት ትልቅ ሚና መጫወት የቻለው አሽሊ ያንግና የቼልሲው ኤዲን ሃዛርድ ለምርጫው በብዙ ርቀት የተከተሉ ተጫዋቾች ናቸው።

ሙሉ ውጤቱ ከታች ያለውን ይመስላል።

መሐመድ ሳለህ (ሊቨርፑል)– 54%
አሽሊ ያንግ (ማን ዩናይትድ) – 18%
ኤዲን ሃዛርድ (ቼልሲ) – 9%
ሪቻርሊሰን (ዋትፎርድ) – 8%
ኬቨን ደ ብሩይኔ (ማን ሲቲ) – 6%
ኸርዳን ሻኪሪ (ስቶክ) – 5%

Advertisements