የተረጋገጠ / ሁጎ ብሩስ ከካሜሮን ብሔራዊ ቡድን ሀላፊነታቸው ተነሱ

2017 ላይ የአፍሪካ ዋንጫን ከካሜሮን ጋር ማሸነፍ የቻሉት የ65 አመቱ ቤልጄማዊው ሁጎ ብሩስ ለ 2018 የአለም ዋንጫ ላይ ካሜሮንን ማሳተፍ ባለመቻላቸው ከሀላፊነታቸው ተነስተዋል።

የካቲት 2016 ላይ “የማይበገሩት አንበሶቹን”ማሰልጠን የጀመሩት ሁጎ ብሩስ ከካሜሮን ጋር በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ ግብፅን 2-1 በማሸነፍ  ዋንጫ ቢያነሱም ቡድኑን ይዘው ወደ ራሺያው የአለም ዋንጫ ግን ማቅናት ሳይቻላቸው ቀርቷል።

ናይጄሪያ እና ዛምቢያ ይገኙበት በነበሩበት የአለም ዋንጫው የምድብ ማጣሪያ ከምድባቸው ማጠናቀቅ የቻሉት ሶስተኛ ሆነው ሲሆን ይህም ደረጃ በ 2018 የአለም ዋንጫው ላይ እንዲሳተፉ አላደረጋቸውም።

ካሜሮን ከነበረችበት ምድብ ናይጄሪያ እና ዛምቢያ እስከ መጨረሻው ጨዋታ ድረስ አንገት ለአንገት ከተያያዙ በኋላ ናይጄሪያ የምድቡ የበላይ ሆና ወደ አለም ዋንጫው ማቅናቷ ይታወሳል።ካሜሮን ሶስተኛ ሆና በማጠናቀቋ ውጤቱ ለሁጎ ብሩስ ከሀላፊነታቸው እንዲነሱ ምክንያት ሆኗል።

አሰልጣኙ የአፍሪካ ዋንጫን ካገኙ በኋላ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እና ክለቦች የተሻለ የስራ እድል ተፈጥሮላቸው የነበረ ቢሆንም ከካሜሮን ጋር መሰንበት ምርጫቸው አድርገው ቆይተዋል።

ፍላጎት ካሳዩ ክለቦች ውስጥም የግብፁ አል አህሊ የሚጠቀስ ሲሆን ከብሔራዊ ቡድን ደግሞ የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን ይጠቀሳሉ።

አሰልጣኙ በቅርቡ ይፋ በተደረገው የካፍ የአመቱ ምርጥ አሰልጣኝ እጩ ውስጥ ከሄክቶር ኩፐር፣ሁሲን አሞታ፣ገሞት ሮህር እና ሚሀዮ ካዚምቤ ጋር መካተታተቸው ይታወሳል።

በቤልጄም ቆይታቸውም አንደርሌክት፣ጌንት እና ክለብ ብሩዥን ማሰልጠን የቻሉ ሲሆን ለአራት ጊዜም የአመቱ የቤልጄም ኮከብ አሰልጣኝ ተብለው መመረጥ ችለዋል።

ካሜሮን ቀጣይ አሰልጣኟን ባታሳውቅም ምናልባትም የቀድሞ የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋች የነበረው ሪጎበርት ሶንግ ሀላፊነቱን ሊረከብ እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል።

Advertisements