ኮንቴ፡ ቼልሲ ፒኤስጂንም ሆነ ባርሴሎናን አይፈራም

አንቶኒዮ ኮንቴ ለቼልሲ የሻምፒዮንስ ሊግ ስኬት ዋናኛ መሰናክል ባርሴሎና እና ፒኤስጂ ሳይሆኑ ፕሪሚየር ሊጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

ቼልሲ ማክሰኞ ምሽት ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር 1ለ1 በመለያየት ሮማን ተከትሎ በምድቡ ሁለተኛ ሆኖ በማጠናቀቁ የሌዮኔል መሲው ባርሳ እና የኔይማሩ ፒኤስጂ በተጨማሪም የቱርኩ ክለብ ቤሽኪታሽ 16 ክለቦች ተሳታፊ የሚሆኑበት የማጣሪ ዙር ላይ ሊገጥሙት የሚችሉ ክለቦች ናቸው።

ይሁን እንጂ ኮንቴ ከአውሮፓውያኑ ኃያላን ክለቦች መካከል የትኛቸውንም እንደማይፈሩ ገልፀው ነገር ግን በሃገር ውስጥ ሊጉ ላይ የሚያስፈልግ ጠንካራ የሆነ የቡድን ጥልቀት የአውሮፓ መድረክ ዋንጫዎችን ማሸነፍ ለእንግሊዛውያኑ ክለቦች አስቸጋሪ እንደሆነም ተናግረዋል።“አምስት ቡድኖች ወደቀጣዩ ደረጃ ማለፍ ችለዋል ማለት ይህ ሊግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ነው።” ሲሉ ኮንቴ ተናግረዋል።

“በዚህ የውድድር ዘመን ሊጉ ከባድ መሆኑን አትዘንጉ። በርካታ ጨዋታዎችን መጫወት አለብህ። ነገር ግን ወደከፍተኛዎቹ የሩብና ግማሽ ፍፃሜዎች ላይ ስትድረስ የእንግሊዝ ክለቦቹ በርካታ ጨዋታዎችን ካደረጉና የደከመ እግር ከያዙ በኋላ ይሆናል። በዚህም ምክኒያት [ሻምፒዮንስ ሊጉን] ማሸነፍ አስቸጋሪ ይሆናል።” ኮንቴ አክለውም “ምርጥ ቡድኖችን ለመግጠም ራስህን ማዘጋጀት ይኖርብሃል። የእኛ ተጋጣሚዎችም ከእኛ ጋር ባመገናኘታቸው ደስተኛ አይሆኑም።” በማለት ጣሊያናዊው አሰልጣኝ ገልፀዋል።

በአውሮፓ እግርኳስ ደንብ መሰረት ሰኞ ይፋ በሚሆነው የዕጣ ማውጣት ስነስርዓት በዚህ የማጣሪያ ዙር የእንግሊዝ ክለቦች እርስ በርስ አይገናኙም።

Advertisements