ሜሲ ከ ሮናልዶ / ሁለት የእግር ኳሱ ዓለም ፈርጦች 10 የአለም ኮከብነት ክብሮች

ሜሲ ወይስ ሮናልዶ? ከሁለቱ ማን የተሻለ ይሆን? ቀጣዩ የሚኪያስ በቀለ ፅሁፍ ሚዛናዊና ምክንያታዊ ማወዳደሪያዎችን ተጠቅሞ ከዛሬው ተጠባቂ የፍራንስ ፉትቦል መፅሄት ሽልማት በፊት ሁለቱን ተጫዋቾች እንደሚከተለው ያነፃፅራቸዋል።

የሁለቱ እግር ኳሰኞች ያለፉትን አስርት አመታት በአለም ኮከብነት ሽልማት ላይ ማንንም ተጫዋች ሳያስገቡ እየተፈራረቁ መንገስ ሌሎች እግር ኳሰኞች የሉም እንዴ የሚል ጥያቄን የሚያጭር መሆኑ የሁለቱን ተጫዋቾች ከሌሎቹ ተጫዋቾች ከፍ ብሎ መሰቀል ይነግረናል።

በነዚህ የአለም ኮከብ ተጫዋችነት ሽልማት ጊዜያት ውድድሩ ሶስት ጊዜያት ስሙን የባለንዶር፣ የፊፋ ባለንዶር እንዲሁም የፊፋ የአለም ምርጥ ተጫዋች ሽልማት እያለ ቢቀያይርም አሸናፊነት ዘውድ ደፊዎች እነዚሁ ሁለት የተቀቡ ኮከቦች ብቻ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱ በአንድ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ አመታትና አስርታትን ሳይሰበሩ የቆዩ ክብረ ወሰኖችን እንክትክታቸውን እያወጡ ሰባብረው በቁጥጥራቸው ስር አውለዋል። ሁለቱም በየአመቱ ከ 50 በላይ ግቦችን የማስቆጠር ስኬትን በመደበኛነት እየተገበሩት ይገኛል። በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ ሁለቱም በእግር ኳስ ዘመናቸው ለክለብና ሀገራቸው ባደረጉት ጨዋታዎች ያስቆጠሩትን ግብ ከ 500 በላይ አድርሰዋል። 

አለም አቀፍ የስፖርት ጋዜጠኞችና ተንታኞች ከሁለቱ ኮከቦች የትኛው በአለም ዘመናዊ እግር ኳስ ላይ በቀዳሚነት መቀመጥ አለበት በሚለው ክርክር ዙሪያ ሁለቱ ተጫዋቾች ያላቸውን የግል መለያ እየጠቀሱ ሁሌም ሲከራከሩ ይታያል። በሁለቱ አብሪ ኮከቦች ዙሪያማ የሁለቱ አድናቂዎች አንዱን በመደገፍና ሌላኛውን በመቃረን በኩል ያለው ዱላ ቀረሽ ንትርክ ለመግለፅ የሚከብድ አይነት የጦዘ ነው።

የሁለቱ ተጫዋቾች ፉክክርም በቡጢ ስፖርት በመሀመድ አሊ እና ጆ ፍሬዘር፣ በቴኒስ በቦርን ቦርግ እና ጆን ማክኖር ወይም ደግሞ በፎርሙላ አንድ በአይርተን ሴና እና አሌን ፕሮስት መሀከል ከነበረውን አይረሴ ትንቅንቅ ጋር የሚነፃፀር አይነት ትልቅ ትኩረት ሳቢ ጉዳይ ነው። ሮናልዶ በ 2012 በሰጠው ቃለ መጠይቅ “እንደማስበው በፉክክር ውስጥ አንዳንዴ እንገፈታተራለን። ይሄ የፉክክሩ ትልቅነት ነው።” ሲል ጉዳዩን መግለፁ ይታወሳል።

በሌላ በኩል የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በአንድ ወቅት “እንደማስበው በመሀከላቸው ያለውን ፉክክር እነሱን አያስጨንቃቸውም። ምርጥ ለመሆን በመፈለግ የሚፈጠር የራሳቸው ግላዊ ክብር እንዳላቸው አስባለሁ።” በማለት የሁለቱ ተጫዋቾች ፋክክር ትኩረት መሳብ እንደሌለበት ተናግረዋል። 

ሜሲ በበኩሉ በእሱና በሮናልዶ መሀከል ምንም አይነት የፉክክር መንፈስ እንደሌለ “ሚዲያው እና ፕሬሱ ብቻ ነው እኛን ተቀናቃኝ እንድንሆን የሚፈልገው። ነገርግን እኔ መቼም ከክርስቲያኖ ጋር ተፋልሜ አላውቅም።” በማለት ሁኔታውን ለማብረድ ሙከራ ሲያደርግ ታይቷል።

በተመሳሳይ መልኩ ሮናልዶ ከአመታት በፊት በእሱና ሜሲ መሀከል ያለው ግላዊ ግንኙነት ያማረ አለመሆኑ የሚወራውን በተመለከተ በሰጠው አስተያየት “እንደ ሌሎች ብዙ ተጫዋቾች እኛም ከእግር ኳስ አለም ውጪ ሌላ ግንኙነት የለንም። ይህንን ያለንን የፉክክር ሂደት በአዎንታዊ መንፈስ እንመልከተው። ምክንያቱም እሱ ጥሩ ነገር ነው።” በማለት ወደፊት ከፉክክር መንፈስ በፀዳ መልኩ አብረው በፍቅር መንፈስ በጋራ እንደሚታዩ መግለፁ አይረሳም።

ነገርግን ሁኔታው ከመብረድ ይልቅ እየጨመረ የሄደ ሲሆን የወሰዷቸው የግል ሽልማቶች ቁጥርም ተመጣጣኝ እየሆነ መምጣትም በመሀከላቸው ያለውን ፉክክር ይበልጥ እንዲከር አድርጎታል። በተመሳሳይ ዘንድሮም ከወር በፊት በተደረገው የፊፋ የአለም ምርጥ ተጫዋች ሽልማት ላይ ተከታትለው ሲጨርሱ በአጠቃላይ ባለፉት አስር አመታት የወሰዱት የአለም ኮከብነት ሽልማቶች በነጠላ እኩል አምስት በአንድ ላይ ደግም ቁጥሩ አስር ደርሶ ተፋጠዋል።

ሮናልዶም ከሽልማቱ በኋላ በኮከብነት ምርጫው ተመጣጣኝ ደረጃ ላይ የመድረሳቸው ነገር የፋክክራቸው መጨረሻ ሳይሆን መጀመሪያ እንደሆነ ሲናገር መሰማቱ ገና በቀጣይ ብዙ የምናያቸው የፉክክር መንፈሶች እንደሚኖሩ ማረጋገጫ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘም በቀጣዩ ፅሁፉ የኢትዮአዲስ ስፖርቱ ሚኪያስ በቀለ ሚዛናዊነት እና ምክንያታዊ መመዘኛዎችን ተከትሎ ነጥብ እየያዘ ከዛሬ ምሽቱ የፍራንስ ፉትቦል መፅሄት የአለም ኮከብነት ሽልማት ጋር በተያያዘ ሁለቱን ተጫዋቾች እንደሚከተለው ያነፃፅርልናል።


1. ግብ የማስቆጠር ችሎታ ንፅፅር

የሜሲ ግብ የማስቆጠር ችሎታ

በየሳምንቱ የጎል ክብረ ወሰኖችን ለሚሰባብረው አርጀንቲናዊ ጎል ማስቆጠር ማለት ጨዋታ ነው። ሜሲ የገርድ ሙለርን የባርሴሎና የምንግዜም ኮከብ ግብ አግቢነት ክብረ ወሰን ሲሰብር ገና እድሜው 24 ነበር። ከዚህ በተጓዳኝ በአንድ የውድድር ዘመን ብዙ ግቦችን (73) የማስቆጠር ክብረ ወሰን እና የላሊጋው የምንግዜውም ኮከብ ግብ አስቆጣሪነትን በጋራ የያዘውም እሱው እራሱ ነው። 

በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ ነጠላ አመት ውስጥ (በ 2012) ለክለቡና ለሀገሩ በ 69 ጨዋታዎች ላይ 69 ግቦችን በማስቆጠር  ለ40 አመታት በገርድ ሙለር የተያዘውን ክብረ ወሰን ስብርብሩን ያወጣው የባርሴሎናው ጥበበኛ 10 ቁጥር ነው። እሱ  ያለምንም ጥርጥር ከምንግዜዎቹም ታላላቅ ጎል አስቆጣሪዎች መመደብ የሚችል ገዳይ ጎል አነፍናፊ ነው። 

ያገኘው ነጥብ : 10/10

የክርስቲያኖ ግብ የማስቆጠር ችሎታ

በሚያስደንቅ ሁኔታ ጎል በማስቆጠር ዙሪያ ሮናልዶ የሜሲን የግቡን መረብ የማግኘት ችሎታ መስተካከል የሚችልና  ከምንግዜዎቹም ታላላቅ ግብ አስቆጣሪዎች አንዱ ነው። 

በእርግጥ ሮናልዶ ወደ ሪያል ማድሪድ ከመጣበት 2009 ወዲህ ከሜሲ በጣም አነስተኛ ብልጫ ያለውን የጎል ምጣኔ ማሳየት የቻለ ሲሆን እስከ 2016/17 የውድድር ዘመን ፍፃሜ ድረስም በ 394 ጨዋታዎች ላይ 406 ያህል ግቦችን (ይህም ሜሲ  በተመሳሳይ ወቅት በጨዋታው ካስመዘገበው የ 1.01 በመቶ ምጣኔ በትንሹ ብልጫ ያለውን የ 1.03 ምጣኔን አሳክታል) ማስቆጠር ችሏል። 

እዚህ ላይ ግን ሮናልዶ ከሜሲ በበለጠ የፊት አጥቂነትን ሚና በዋናነት ይዞ መቀጠሉ ከቀኝ ክንፍ ለሚነሳውና የጨዋታ አቀጣጣይነትን ሚና ጭምር ከሚወስደው ሜሲ በተሻለ አስተዋፅኦ እንዳደረገለት የማይካድ ሲሆን ሁኔታውም ሮናልዶ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ ብዙ ግብ የማስቆጠርን (ምንም እንኳን የራውልን የቻምፒዮንስ ሊግ የቀደመ ክብረ ወሰን ሜሲ ቀድሞ የሰበረው ቢሆንም) ክብረ ወሰንን እንዲመራ እንዳስቻለው ይነገራል።

ያገኘው ነጥብ : 10/10

2. በጭንቅላት ግብ የማስቆጠር ችሎታ ንፅፅር

የሜሲ በጭንቅላት ግብ የማስቆጠር ችሎታ

የጭንቅላት ኳስ ሜሲ ካለው አጭር ቁመትና ከባርሴሎና አጨዋወት (ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ኳስን መሬት ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል አጨዋወት ተግባራዊ ስለሚደረግ) አንፃር ከአለም ምርጥ የጭንቅላት ኳስ አስቆጣሪዎች እንዳይመደብ እንቅፋት ሆኖበታል። 

በአጠቃላይ ሜሲ በጭንቅላት ኳስ ዙሪያ ደካማ ተደርጎ የሚወሰድ ቢሆንም በ 2009 የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ማንችስተር ዩናይትድ ላይ በግሩም ሁኔታ በጭንቅላት ያስቆጠራት ኳስ ብዙዎች ያስታውሷታል። 

ያገኘው ነጥብ : 7/10

የሮናልዶ በጭንቅላት ግብ የማስቆጠር ችሎታ

በመሬት ላይ ጥሩ ብቃት ያለው ሮናልዶ በአየር ላይም እንደ አንድ አየር ላይ አስቸጋሪ የመሀል ተከላካይ እራሱን በመዘርጋትና ሀይልን በመጠቀም ኳስን በአየር ላይ የሚያድን ተጫዋች ሲሆን ለቁጥር የሚታክቱ ግቦችንም በጭንቅላቱ ማስቆጠር ችሏል። 

በ2016/17 የውድድር ዘመን ሮናልዶ በሁሉም ውድድሮች ላይ ካስቆጠራቸው 42 ግቦች ስምንቱ በጭንቅላቱ ያስቆጠራቸው ናቸው። 

ወሳኝ ነጥብ : ከዚህ ጋር በተያያዘ (Watch: Normals trying to replicate Ronaldo’s 6ft 8in jump) ብሎ ዩቲዩብ ድረገፅ ላይ በመፈለግ ይህን ቪዲዮ መመልከት ጠቃሚ ይመስላል።

ያገኘው ነጥብ : 9/10

3. የአብዶ ችሎታ ንፅፅር

የሜሲ የአብዶ ችሎታ 

ሜሲ በኳስ ላይ ባለው የማጣጠፍ ችሎታው ከምንግዜዎቹም ምርጡ ቢባል የማይበዛበት አይነት አብዶኛ ተጫዋች ነው። 

ኳስ እግሩ ስር ሲገባ ያለው የአስተሳሰብ ፍጥነት ከእግሮቹ ፈጣን ሩጫ ጋር ሲደመሩ በጣም ጣባብና በተቃራኒ ተጫዋቾች የተሞላ የሜዳውን ክፍል ኳስ እግሩ ላይ ተሰፍቷል ወይ እስኪባል ድረስ በቀላሉ አሳብሮ መሄድ የሚያስችል ክህሎትን የያዘ ባለልዕለ ሀያል ክህሎት ባለቤት ነው። 

ሜሲ ያለው አነስተኛ የሰውነት ምጣኔ ለመሬት ስበት የቀለለ የሚያደርገው መሆኑ ከኳስ ውጪ ያለውን ፍጥነት ከኳስ ጋር መድገም የሚያስችለው ሲሆን ይህ ችሎታውም ሜሲን ከሁሉም በተለየ እሱን ማየት አዝናኝ ያደርገዋል። 

ወሳኝ ነጥብ : የሜሲን የተለየ የአብዶ ችሎታ ለማረጋገጥ ዩትዩብ ላይ ይህንን (Watch : Superb Messi dribble against Eibar) ፅፎ በመፈለግ የሚመጣውን ቪዲዮ መመልከት በቂ ይመስላል።

ያገኘው ነጥብ : 10/10

የሮናልዶ የአብዶ ችሎታ 

ሮናልዶ ጥሩ የአብዶ ችሎታ እንዳለው የማይካድ ቢሆንም ፈርጉሰን ይወዱት በነበረው ከክንፍ እየነሳ (out-and-out winger) ተከላካዮችን ያስጨንቅበት ከነበረበት ሚና ወደ ፊት አጥቂነት በመቀየሩና ሙሉ ትኩረቱን ጎል በማስቆጠር ላይ በማድረጉ ኳስን ከመግፋት ይልቅ መጨረስ ስራው ሆኗል።

ነገርግን በፊት መስመር ላይ መጫወቱን ልምድ አድርጎ ቢቆይም የአብዶ ችሎታው አሁንም አብሮት ያለ ሲሆን የማድሪዱ ኮከብ የአብዶ ችሎታ ድንገቴ ክስተት ተብሎ የሚገለፅ አይነት ሲሆን የሜሲ በበኩሉ ፍስስ የሚልና ተፈጠራዊ ይዘት ያለው ነው። 

ያገኘው ነጥብ : 8/10

4. ኳስ የማቀበል ችሎታ ንፅፅር

የሜሲ ኳስ የማቀበል ችሎታ

የሜሲ ኳስ የማቀበል አቅም ሰዎች በሚያስቆጥራቸው ግቦች እና አብዶዎች ላይ ትኩረት ስለሚያደርጉ ብዙም ያልተወራለት ቢሆንም ያለው እይታ እና ኳሱን የሚገባው ቦታ ላይ የማድረስ ብቃት ትናንትም ዛሬም ከምንግዜዎቹም ምርጦች አንዱ ያደርገዋል። 

በ2015/16 ወደክንፍ የተለጠጠና ወደኋላ ሳብ ያለ ሚናን ከተረከበ ወዲህ ሜሲ ያለውን የፈጠራ ችሎታ ማሳደግና የሚያቀብላቸው ኳሶች ይበልጥ የተመጠኑና ምጥቀት ያላቸው ሆነዋል። በ 2016/17 የውድድር ዘመንም 78 የግብ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበልም አርጀንቲናዊው ኮከብ ማስደመሙን ቀጥሏል።

ያገኘው ነጥብ : 10/10

የሮናልዶ ኳስ የማቀበል ችሎታ

የሮናልዶን ኳስ የማቀበል ስኬት ከሜሲ ጋር ማወዳደር ሁለቱ ቡድኖች ካላቸው አጨዋወት የተለያየ ከመሆኑ አንፃር በተወሰነ ደረጃ አዋጭ አይመስልም። ባርሴሎና ሳቢ በሆነ የአንድ ሁለት ቅብብል ላይ የተመሰረተ አጨዋወትን የሚከተል ሲሆን ማድሪድ በበኩሉ ፈጣን እና በድንገቴ የማጥቃት እግር ኳሱ ተለይቶ ይታወቃል።

ነገርግን ሮናልዶ በ2016/17 80 በመቶ ኳስ የማቀበል ስኬት በማስመዝገብ ጠንካራ መሆኑን አስመስክራሉ። የጎል ኳስ አመቻችቶ በማቀበል ረገድ ግን 78 የጎል እድሎችን ከፈጠረው ሜሲ በጣም ባነሰ መልኩ ሮናልዶ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን የፈጠረው 30 የጎል እድሎችን ብቻ መሆኑ ፖርቹጋላዊውን ተጫዋች በንፅፅሩ ተጎጂ አድርጎታል።

ያገኘው ነጥብ : 8/10

5. የቅጣት ምትን ወደ ጎል የመቀየር ስኬት ንፅፅር

የሜሲ የቅጣት ምት ችሎታ

የሜሲ በቆመ ኳስ ላይ ያለው ዕይታና ፈጠራ ከሌሎች የቅጣት ምት ጠበብቶች ከፍ ብሎ እንዲቀመጥ አስችሎታል። እሱ ቅጣት ምቱን ከመምታቱ በፊት ቀዳዳን የመፈለግና ኳስ የተቃራኒዎቹን ቡድን አባላት አልፋ ቀዳዳው ላይ የምታርፍበትን መንገድ የመለየት ብቃቱ በቀላል አገላለፅ ምጡቅ የሚያስብለው አይነት ነው። 

ሜሲ ከቆመ ኳስ ጀርባ ላይ ሮናልዶ ያለውን ያህል ሀይል የሌለው ቢሆንም ያለው ዝግጁነት ቅጣት ምቶቹን ልዩ ያደርጋቸዋል። በ 2015/16 ለክለቡ ባርሴሎና እና ለሀገሩ ያስቆጠራቸው ዘጠኝ የቅጣት ምት ግቦች በአለም እግር ኳስ ከማንም በላይ ከፍ አድርገውም አስቀምጠውታል። 

በ2016/17 ደግሞ ቁጥሩ ወደ አምስት ዝቅ ቢልም በጥር 2017 ብቻ በአንድ ወር ውስጥ ሶስት ግቦችን ከቅጣት ምት አስቆጥሯል። 

ያገኘው ነጥብ : 9/10

የሮናልዶ የቅጣት ምት ችሎታ

የሮናልዶ ሀይል እና ኳስ በሁሉም አቅጣጫ እንድትጓዝ የማድረግ አቅም ፖርቹጋላዊውን ተፈሪው የቆመ ኳስ ጠበብት ያደርገዋል። በጣም ጥቂቶች ብቻ ሮናልዶ ቅጣት ምት የሚመታበትን (ከመምታቱ በፊት ወደኋላ የሚቆጥርበትና ትንፋሽ የሚሰበስብበትን ትዕይንት) አይነት ሌላ አቻ ልዩ መንገድ ተክነዋል። 

ሮናልዶ በማድሪድ ቤት ቅጣት ምትን ወደጎል የመቀየር ችሎታው ወርዶ ቢቆይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መሻሻልን አሳይቶ በ 2015/16 ሶስት ግቦችን ከቅጣት ምት ሲያገባ በ 2016/17 ሌሎች አራት ቅጣት ምቶችን ወደ ግብነት ቀይሯል።

ወሳኝ ነጥብ : የሮናልዶን የቅጣት ምት ችሎታ የሚያሳየውን ይህን (Watch : Ronaldo’s stunning free kick for Man Utd against Portsmouth in 2008) ቪዲዮ ከዩትዮብ ላይ ማግኘት ትችላላችሁ። 

ያገኘው ነጥብ : 8/10

6. የፍፁም ቅጣት ምትን ወደ ጎል የመቀየር ስኬት ንፅፅር 

የሜሲ የፍፁም ቅጣት ምት ችሎታ

ሜሲ ለተወሰኑ አመታት ከፍፁም ቅጣት ጎል የማስቆጠር ችግር አጋጥሞት የነበረ ሲሆን በ 2014/15 እና በ2015/16 ካገኘው 17 ፍፁም ቅጣት ምቶችም 10 ያህሉን ብቻ ወደጎል ቀይሮ በፍፁም ቅጣት ምት ሲቸገር ታይቷል።

ባሳለፍነው የ 2016/17 የውድድር ዘመን ግን ወደቀደመ የቅጣት ምት አቅሙ ተመልሶ ለክለቡና ለሀገሩ ካገኘው 11 ፍፁም ቅጣት ምት 10 ያህሉን ወደግብ በመቀየር ካለፉት አመታት ተሽሎ መገኘቱን አስመስክሯል። 

በአጠቃላይ ስንመለከተው ደግሞ ሜሲ እስከ 2016/17 መጠናቀቂያ ድረስ በእግር ኳስ ዘመኑ ካገኘው ፍፁም ቅጣት ምት 78.7 በመቶ (74 አግብቶና 20 ያህሉን ስቶ) ያህሉን ብቻ ወደ ግብነት ቀይሮ 82.6 በመቶ (95 አግብቶና 20 ያህል ስቶ) ያህል ያገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ወደጎል ከቀየረው ሮናልዶ አንሶ ተቀምጧል። 

ያገኘው ነጥብ : 7/10

የሮናልዶ የፍፁም ቅጣት ምት ችሎታ

የሮናልዶ የፍፁም ቅጣት ምት ስኬት ባለፋት ጥቂት አመታት መቀነሶችን ያሳየ ሲሆን ያለፉትን ሁለት አመታት ብቻ ብንመለከት እንኳን በ 2015/16 ለክለቡና ሀገሩ ካገኘው 13 ፍፁም ቅጣት ምት ስምንት ያህሉን ብቻ ወደግብ ሲቀይር በ2016/17 ካገኘው 12 ፍፁም ቅጣት ምት ወደግብ የቀየረው ዘጠኝ ያህሉን ነው።

እነዚህ የቅርብ ጊዜ የፖርቹጋላዊው በፍፁም ቅጣት ምት ዙሪያ የመንሸራተት ችግሮችም በላሊጋ ላይ ቀጥለው ሮናልዶን በላሊጋው ታሪክ ብዙ ፍፁም ቅጣት ምቶችን የሳተ (እስከ 2016/17 መጠናቀቂያ እሱ 10 ሲስት ሜሲ ዘጠኝ ያህል አምክኗል) የሚል አሉታዊ ክብረ ወሰን እንዲይዝ አድርጎታል። 

ከነዚህ ሁላ በኋላም ግን የሮናልዶ አጠቃላይ ፍፁም ቅጣት ምትን ወደግብ የመቀየር ስኬት ጥሩ የሚባል አይነት ሲሆን እስከ 2016/17 የውድድር ዘመን መጠናቀቂያ ድረስ ካገኛቸው 115 ፍፁም ቅጣት ምቶች 95 ያህሉን ወደግብ መቀየር ችሏል። 

ያገኘው ነጥብ : 9/10

የአካል ብቃት ንፅፅር 


7. የሜሲ የአካል ብቃት ደረጃ 

አርጀንቲናዊው ኮከብ 1 ሜትር ከ 70 ሳ.ሜ ብቻ የሚረዝም እንደመሆኑ ደቃቃ ከሚባሉ እግር ኳሰኞች የሚመደብ ሲሆን በታዳጊነት እድሜውም የበዛ የቁመት እጥረቱና ደካማ የአካል ብቃቱ የእግር ኳስ ተጫዋች የመሆን እድሉን እስከ መጨረሻው ሊያጨናግፍበት ከጫፍ ደርሶ ነበር። 

ነገርግን እሱም የአለም እግር ኳስ ተመልካችም እድለኛ ሆኖ የተደረገለት የሆርሞን ህክምና ሰርቶ አለም ልብ ቀጥ በሚያደርገው ተፈጥራዊ ተሰጥኦው ለመደመም በቅቷል።

ሜሲ ያለው ደቃቃነት ሳይበግረውም ትልልቅ ባለጋራዎቹን እየመከተ አስደማሚ ብቃቱን ማሳየት ሲያስችለው ከጠንካራ ምቶቹ ጀርባም ከፍተኛ ሀይል እንዳለው ማስመስከር ችሏል። 

ያገኘው ነጥብ : 7/10

የሮናልዶ የአካል ብቃት ደረጃ 

ሮናልዶ ያለው 1 ሜትር ከ 84 ሴ.ሜ ቁመት በአካል ብቃት ደረጃ ለዘመናዊ እግር ኳስ እጅጉን የቀረበ ሰው ያደርገዋል። በረጅም ቁመናውና በአስደናቂው ተክለ ሰውነቱ የበሬን ያህል ጥንካሬ በውስጥ የያዘ ጠጣር ተጫዋች መሆንም ችሏል። 

በአጠቃላይ ሲታይ ሜሲ ባለው ተፈጥራዊ አስደማሚ ክህሎት እና ዕይታ ሲነግስ ሮናልዶ በበኩሉ ያለው ጥንካሬ፣ ፍነጥነትና ሀይል የእግር ካሱ አለም ኮከብ እንዲሆን አስችሎታል። 

ያገኘው ነጥብ : 10/10

8. የቡድን ስራ አቅም ንፅፅር

ሜሲ ለቡድን ስራ ያለው አቅም

አርጀንቲናዊው ኮከብ ባለው ግላዊ ብቃትና በራሱ ጥረት ካስቆጠራቸው ግቦች ባሻገር ሜሲ በቡድን ተጫዋችነት ትልቅ ስም የሚሰጠውና ለብዙ ጊዜያት ኳስ እግሩ ስር ባለማቆየት የተመሰገነ ተጫዋች ነው።

እሱ ያለው የግብ ማግባት ክብረ ወሰን ከሮናልዶ ጋር የተቀራረበ ቢሆንም ለቡድን አጋሮቹ አመቻችቶ ያቀበለው ኳስ መጠን ከሮናልዶ እጅጉን የላቀና ከፍተኛ ነው። 

ባለፉት ሁለት አመታት ሜሲ ከኔይማርና ሱዋሬዝ ጋር በመጣመር ሶስቱም እኩል የነገሱበትን አይነት ከፍታ ያሳዩን ሲሆን ሜሲም ምንም አይነት ራስ ወዳድ ባህሪ እንደሌለውና የቡድን ተጫዋች መሆኑን ባስመሰከረ መልኩ በራሱ ሊያስቆጥራቸው የሚችሉትን ቀላል የጎል እድሎች ለቡድን አጋሮቹ ወደጎልነት እንዲቆይሩ አመቻችቶ ከማቀበል ጀምሮ የፍፁም ቅጣት ምቶችን ለቡድን አጋሮቹ ሲለቅ አይተናል።

ያገኘው ነጥብ : 9/10

ሮናልዶ ለቡድን ስራ ያለው አቅም

ከሜሲ ጋር ሲነፃፀር ሮናልዶ የቡድን አጋሮቹ ከእሱ የተሻለ የጎል ማግባት አማራጭ ላይ ሆነው እራሱ ግቦችን ለማስቆጠር ሲደክም የሚታይበት መንገድ ብዙ ጊዜያት የክለቡን ደጋፊዎች፣ የቡድን አባላትንና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሲከት የተስተዋለ ሲሆን ጥረቱ ሳይሳካ ሲቀርም እሱ እራሱን ጥፋተኛ ሲያደርግ ታይቷል። 

ከዚህ በተጨማሪም እሱ ግብ ሳያስቆጥር ቀርቶ የቡድን ጓደኞቹ ግብ በሚያስቆጥሩበት ወቅት ሲከፋ የታየበት አጋጣሚ መኖሩም የማይካድ ነው። 

ከነዚህ ሁሉ ነገሮች በተጓዳኝ ግን የሮናልዶ ለጎል የሚሆን ኳስ አመቻችቶ የማቀበል ስኬት ከሜሲ ያነሰ ቢሆንም ጤናማ የሚባል አይነት ሲሆን ባሳለፍነው የ 2016/17 የውድድር ዘመንም ቡድኑ የላሊጋውን ዋንጫ በተጣበበ መርሀ ግብር ውስጥ በትግል ሲያነሳ ለትልልቅ ጨዋታዎች ተብሎ ፖርቹጋላዊው ኮከብ እንዲያርፍ ሲደረግ የላሊጋውን የወርቅ ጫማ ክብር ለማግኘት ከመሯሯጥ ይልቅ የአሰልጣኙን ውሳኔ በፀጋ መቀበሉ አይረሳም።

ያገኘው ነጥብ : 7/10

9. ስነምግባራዊ ንፅፅር

የሜሲ ስነምግባር 

ሜሲ ፈጣንና በክህሎት የዳበረ ተጫዋች ከመሆኑ አንፃር በእያንዳንዱ ጨዋታ ሊባል በሚችል ደረጃ የመጠለፍ እንዲሁም ደግሞ የተቃራኒ ተጫዋቾች ጉሽሚያ ዋነኛ ሰለባ መሆኑ ግልፅ ነው። 

ነገርግን አንዳንድ ተጫዋቾች በቀላሉ ለመውደቅና አጭበርብረው የቅጣት ምት ወይም የፍፁም ቅጣት ምት ለማግኘት በሚጥሩበት በዚህ ጊዜ ሜሲ የሚደርስበትን ጉንተላ ተቋቁሞ በቻለው መንገድ ላለመውደቅና ማጥቃቱን ለመቀጠል ጥረት ሲያደርግ ይታያል። 

በዚህ ሁሉ መሀከል ግን ሰውኛ ባህሪን የተላበሰ እንደመሆኑ ሜዳ ላይ ጉንተላውና አካላዊ ትንኮሳው ሲደጋገምበት የመናደድና ተስፋ የመቁረጥ ባህሪን በጣም በተወሰኑ አጋጣሚዎች ላይ ሲያሳይ ተስተውሏል። ነገርግን በአጠቃላይ ሲታይ ይሄ የመሲን ባህሪ የሚያሳይ ሳይሆን ከስንት ጊዜ አንዴ የሚፈጠር ድንገቴ አጋጣሚን የሚገልፅ ነው።

ወሳኝ ነጥብ : የሜሲን በቀላሉ ላለመውደቅና ጨዋታውን ለመቀጠል የሚያደርገውን ጥረት ለመመልከት ይሄን (Watch : Messi staying on his feet when he can) ቪዲዮ መመልከት በቂ ይመስላል።

ያገኘው ነጥብ : 9/10

የክርስቲያኖ ስነምግባር 

ሮናልዶ ብዙ ጊዜያት ከሚወቀስባቸው ነገሮቹ አንዱ ይሄ ሲሆን በቀላሉ ለመውደቅ ይጣጣራል ወይም ደግሞ ጉዳትን ላለማስተናገድ የበዛ ጥንቃቄን ይወስዳል በሚልም ይተቻል። 

በሌላ በኩል ግን ይህ ባህሪው ለጨዋታው ካለው ጥልቅ ፍላጎት እና ውሳኔዎች ከእሱ በተቃራኒው የመሄድ አጋጣሚ ካላቸው እሱን ለራሱና ለቡድኑ ጥቅም ባደላ መልኩ ለማስለወጥ የሚጓዝበት ብልጠት እንደሆነ ጠቅሰው የሚከራከሩለት ጥቂቶች አይጠፉም። 

ያገኘው ነጥብ : 7/10

10. የግል ክብሮችን ወይም ዋንጫዎችን የማሸነፍ ስኬት ንፅፅር የሜሲ የግል ክብሮችን ወይም ዋንጫዎችን የማሸነፍ ስኬት ንፅፅር

ሜሲ የእግር ኳስ ህይወቱ በግሉ ካገኛቸው ክብሮችና ሽልማቶች አንስቶ በክለብ ደረጃ የተንቆጠቆጠ የእግር ኳስ ህይወት ያለው ነው፡፡ 

የአለም ኮከብነትን ሽልማት ባለፉት አስር አመታት ለአምስት ጊዜያት መውሰድ የቻለ ሲሆን ከቻምፒዮንስ ሊግ አንስቶ እስከ ክለቦች አለም ዋንጫ ድረስ በአለም ላይ ያሉ የክለብ ነክ ዋንጫዎችን ጠራርጎ መውሰድ ችሏል፡፡

በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ግን አርጀንቲናዊው ኮከብ በባርሴሎና ያገኛቸውን ስኬቶች መድገም አለመቻሉ ቢያስቆጨውም በኒውካምፕ ያገኛቸው እልፍ አዕላፍ ስኬቶች የሀገሩን ቁጭት ማስረሻ ሆነውታል፡፡

ያገኘው ነጥብ : 9/10 

የሜሲ የግል ክብሮችን ወይም ዋንጫዎችን የማሸነፍ ስኬት ንፅፅር

ሜሲ በክለብ ደረጃ ያገኘውን የግል ክብርና የዋንጫ ስኬቶች ሮናልዶ ከኦልትራፎርድ ጀምሮ አሁን እስካለበት ማድሪድ ድረስ አሳክቶታል፡፡ ነገርግን ሮናልዶም በተመሳሳይ መልኩ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የተፎካካሪውን አርጀንቲናዊ ኮከብ አይነት ሂደት የተከተለና የብሔራዊ ቡድን ጉዞው ያማረ አይደለም፡፡ 

አምና ከሀገሩ ጋር ያገኘውን የአውሮፓ ዋንጫ ከሜሲ የተሻለ እንደሆነ ለማድረግ ብናነሳም ሜሲ ለአለም ዋንጫ ፍፃሜ በደረሰበት የ 2014 የብራዚል የአለም ዋንጫ ውድድር ፖርቹጋል በ 4-0 አሳፋሪ ውጤት በጀርመን የተረታችበትን እና ከምድቡ ማለፍ ያልቻለችበትን መጥፎ ታሪክ ስለምናገኝ ሮናልዶን በዋንጫ ስኬት ንፅፅሩ የበላይ የማድረግ እቅዳችንን እንድንሰርዝ ያስገድዳል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የዋንጫ ክብር ባይኖርበትም ሜሲ ለአለም ዋንጫው ለማለፍ ቸግሯት ቅርቃር ውስጥ ገብታ የነበረችውን ሀገሩን ከሳምንታተወ በፊት አድኖ ለሩሲያው አለም ዋንጫ ያበቃበትን አሰደማሚ ምሽት እንዴት ልንረሳው እንችላለን?! 

ያገኘው ነጥብ : 9/10 

የማጠቃለያ ምዘና

የሜሲ ማጠቃለያ ምዘና

የመጨረሻው የሁለቱ ኮከቦች አጠቃላይ ድምር ውጤት በሁለቱ መሀከል ያለው ትንቅንቅ የከረረ መሆኑን የሚያሳየንና ሁለቱ በአንድ ትውልድ መጫወታቸው የእግር ኳስ ተመልካቹ የሁለቱን ተጫዋቾች የፋክክር መንፈስ በማግኘቱ ያለውን እድለኝነት የሚያሳይ ነው።

ሜሲ ያለበት የሰውነት አቋም ውስንንነት በዋነኛነት በጭንቅላት ኳስ የማስቆጠር ብቃቱ ላይ፣ በጥንካሬ እና ባለው ሀይል ላይ በተደረጉ ምዘናዎች ነጥቦችን እንዲጥል ቢያደርገውም በኳስ ላይ ያለው ቴክኒካል ብቃት፣ የመጠቀ ዕይታው እና ለቡድን መንፈስ መጎልበት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከተቀናቃኙ የበለጠ ነጥብ እንዲያገኝ አስችሎታል።

እነዚህ ከላይ መጨረሻ ላይ የጠየቀስናቸው (በኳስ ላይ ያለው ቴክኒካል ብቃት፣ የመጠቀ ዕይታው እና ለቡድን መንፈስ መጎልበት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ) ሶስት መመዘኛዎችም የአርጀንቲናው ኮከብ አድናቂዎች መሲሀቸው በዋነኛነት ጎል ማስቆጠርን ስራዬ ብሎ ከያዘው ፖርቹጋላዊ ተቀናቃኙ በልጦ እንዲቀመጥ እንደሚያደርገው የሚከራከሩበት ዋነኛ ማጠንጠኛቸው ነው። 

ሜሲ ያገኘው አጠቃላይ ነጥብ : 87/100

የሮናልዶ ማጠቃለያ

ሮናልዶ ወደ ስፔን ከመጣ ወዲህ በሁለቱ ተጫዋቾች መሀከል ያለው ልዩነት ይበልጥ እየጠበበና ተቀናቃኝነታቸው እየከረረ መምጣቱ የማይካድ ሀቅ ነው። በዚህ ረገድ በተለይ ሁለቱ ኮከቦች ያስቆጠሩትን ግብ እንደ ማነፃፀሪያ ወሰደን ከተመለከትን በእኩል ደረጃ የሚያስቀምጣቸው ነው። 

ሮናልዶ የዘንድሮውን ጨምሮ በአለም እግር ኳስ ላይ ካለፋት አምስት አመታት በአራቱ የኮከብነት ክብርን በመውሰድ ከሜሲ እኩል መቀመጥ ችሏል። 

በአጠቃላይ ግን ውድ አንባቢያን በሁለቱ ዙሪያ ምንም ይሁን ምን አቋማችሁ በአሁን ሰአት እግር ኳስን እየተጫወቱ ከሚገኙ ሌሎች ተጫዋቾች በላይ ሁለቱ ተጫዋቾች ላይደረስባቸው ከፍ ብለው መቀመጣቸውን መካድ አይቻልም።

ሮናልዶ ያገኘው አጠቃላይ ነጥብ : 85/100

የህዳግ ማስታወሻ : ይህ ፅሁፍ ከጥቂት ማስተካከያ ውጪ በኢትዮአዲስ ስፖርት ወርሀዊ መፅሄት ላይ የወጣ ነው። እናም እነዚህን መሰል ጥልቅ ዘገባዎች ለማግኘት እንዲሁም ደግሞ ኢትዮአዲስ ስራዋን በተጠናከረ መልኩ እንድታካሂድ በገቢ ረገድ እገዛ ለማድረግ መፅሄቱን ከሎሚ የመተግበሪያ አፕሊኬሽን ላይ በመግዛት ያንብቡ።

Advertisements