ክብር / ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለአምስተኛ ጊዜ የባለንዶር አሸናፊ ሆነ 

ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለአምስተኛ ጊዜ በፈረንሳዩ የእግር ኳስ መፅሄት ፍራንስ ፉትቦል የሚዘጋጀው የባለንዶር ሽልማት አሸናፊ ሆኗል።

በዘንድሮው የአለም ኮከብ ተጫዋችነት ፉክክር አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ሁለተኛነትን ሲያገኝ ብራዚላዊው የቀድሞ የባርሴሎና ተጫዋች ኔይማር ሶስተኛ ደረጃን ተጎናፅፏል።

ሮናልዶ ከሽልማቱ በኋላ “ይሄ በየአመቱ የምፈልገው ነገር ነው። ምስጋና ለሪያል ማድሪድ ጓደኞቼ እና እዚህ እንድደርስ ላገዙኝ በሙሉ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ።” በማለት የተሰማውን ስሜት ገልጿል።

ፍራንስ ፉትቦል ከዚህ ቀደም ከፊፋ ጋር በጥምረት ይሰጥ ከነበረበት ጊዜ በተቃራኒው ለሁለተኛ ተከታታይ አመት ብቻውን ሽልማቱን በሰጠበት የዘንድሮ መርሀ ግብር የጁቬንቱስ የግብ ዘብ ጂያንሉጂ ቡፎን በአራተኛነት ፉክክሩን ፈፅሟል። 

በምሽቱ ስነስርዓት የማድሪዶቹ ሉካ ሞድሪችና ሰርጂዮ ራሞስ በአምስተኛና ስድስተኛ ተከታትለው ሲቀመጡ የፒኤስጂው ታዳጊ ምባፔ እና የቼልሲው አማካኝ ንጎሉ ካንቴ ሰባተኛና ስምንተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በዚህ ሮናልዶ በግል ጀቱ ወደ ፓሪስ ባመራበት የምሽቱ የሽልማት ስነስርዓት እንግሊዛዊው የቶትነሀም ኮከብ ሀሪ ኬን 10ኛ ሆኖ ማጠናቀቁ አስገራሚ ሆኗል።

Advertisements