መረብ ኳስ / የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌደሬሽን 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ

ምስል : ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ የተገኘ

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌደሬሽን 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በዛሬው ዕለት በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል አድርጎ በስኬት አጠናቋል።

የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የተጀመረው መደበኛ ጉባኤ የዕለቱን አጀንዳዎች በጉባኤው ተሳታፊዎች አፅድቆ ወደተያዙት ጉዳዮች በቀጥታ ገብቷል።

በዚህም መሰረት የ 17ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ ለተሳታፊዎች ቀርቦ በሙሉ ድምፅ የፀደቀ ሲሆን በመቀጠልም የ 2009 የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በፅህፈት ቤት ሀላፊው አቶ መስፍን አበራ ቀርቦ በተሳታፊዎቹ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

በመቀጠል የፌደሬሽኑ የሂሳብ ሪፖርት በውጪ ኦዲተር እንዲቀርብ ተደርጎ በቀረበው የሂሳብ ሪፖርት ላይም አስተያየት ተሰጥቶበት ያለምንም ተቃውሞ በሙሉ ድምፅ የፀደቀ ሲሆን ከዛም የ 2009 የክልሎችና የአዲስ አበባ መስተዳድር ክንውን በተወካዩቻቸው ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ከእረፍት መልስ የ 2010 እቅድ በፅህፈት ቤት ሀላፊው ቀርቦ ውይይትና ጥያቄዎች ከተስተናገዱ በኋላም የፅህፈት ቤት ሀላፊው ለተሳታፊዎች እቅዱን እንዲያፀድቁት አቅርበው ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ተቀብሎ አፅድቆታል።

ከዛም የቮሊቦል ስትራቴጂ ዕቅድ ጥናት በአቶ አለማየሁ አማካኝነት ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን በመቀጠልም የተጫዋቾች ዝውውር መመሪያ በፅህፈት ቤት ሀላፊው ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት በሙሉ ድምፅ እንዲፀድቅ ተደርጓል።

በመቀጠል በጎደሉ የፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባላት ምትክም የሚሆኑ አዳዲስ አባላት እንዲቀርቡ የተደረገ ሲሆን በዚህ መሰረትም አቶ ኪሮስ ከአዲስ አበባ፣ አቶ ዳግም ምላሽ ከጋምቤላ፣ አቶ ክብሩይስፋ በሪሁን ከአማራ፣ አቶ አለምእሸት ሀይሉ ከኦሮሚያ በአንድ ድምፀተ አቅቦ ያለምንም ተቃውሞ በስራ አስፈፃሚነት ተሹመዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በቮሊቦል ዙሪያ ጥናት የሚሰሩት እና መደወላቡ ዩንቨርስቲን ወክለው የተገኙት ዶ/ር ስሜ ለአዲሶቹ የስራ አስፈፃሚ አባላት አጋዥ እንዲሆኑ ሀሳብ ቀርቦ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።

በመጨረሻም ብዙ ውሳኔዎች የተላለፉበት መደበኛ ጉባኤው በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ተወካይ የመዝጊያ ንግግር ፍፃሜውን አግኝቷል። 

Advertisements