በፊፋ የአለም የክለቦች ውድድር የአፍሪካው ተወካይ ዊዳድ ካዛብላንካ ተሸነፈ

በ2017 የአለም የክለቦች ዋንጫ አፍሪካን የወከለው የካፍ ቻምፒየንስ ሊጉ አሸናፊ የሞሮኮው ዊዳድ ካዛብላንካ በሩብ ፍፃሜው በሜክሲኮው ፓቹካ ተሸንፈ።

ዊዳድ ካዛብላንካ በአለም የክለቦች ውድድር ላይ አል አህሊን በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፍ ሲችል የሜክሲኮው ፓቹካ በበኩሉ የኮንካፋ አሸናፊ በመሆኑ በውድድሩ ላይ ለአራተኛ ጊዜ መሳተፍ ችሏል።

በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የተጀመረው የፊፋ የአለም የክለቦች ሻምፒዮና ሁለቱን ክለቦች ያገናኘው የዛሬው ጨዋታ የአፍሪካው ተወካይ ዊዳድ ካዛብላንካ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

በአቡዳቢ ዚያድ ስፓርት ሲቲ ስታድየም በተደረገው ጨዋታ የመጀመሪያዉ ግማሽ ቀዝቃዛ ነበር።ጠንካራ ድጋፍ ያገኘው ዊዳድ ካዛብላንካ መልካም እንቅስቃሴ ቢያደርግም ግልፅ የሆነ የጎል እድል መፍጠር ሳይችል ቀርቷል። 

በሁለተኛው ግማሽ መልካም አጀማመር ያደረጉት ዊዳዶች ኢብራሂም ኤልሂዳድ በግራ መስመር ሰብሮ ገብቶ የመታው ኳስ ወደ ላይ ወጥቶበታል።

የሜክሲኮው ቡድንም ጠንካራ ሆኖ በታየበት የሁለተኛው ግማሽ በቀድሞ የሚላን አማካይ ኬሱኪ ሆንዳ እና በጉዝማን አማካኝነት ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለዋል።

ነገርግን ብራሂም ናካች 69ኛ ደቂቃ ላይ የተመለከተው ሁለተኛ ቢጫ ካርድ ዊዳዶች ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋች እንዲጫወቱ ተገደዋል።

ወደ ጭማሪ ሰአት ያመራው ጨዋታ 111ኛ ደቂቃ ላይ ግን ፓቹካዎች በቪክቶር ጉዝማን የጭንቅላት ኳስ አማካኝነት ጎል አስቆጥረው አሸናፊ መሆን ችለዋል።

በዚህም መሰረት ፓቹካ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፍ የቻለ ሲሆን በቀጣይ ማክሰኞም የደቡብ አሜሪካ አሸናፊ ከሆነው ከብራዚሉ ግሪሚዬ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል።

Advertisements