ቡጢ / የኢትዮጵያ ቦክስ ፌደሬሽን 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌደሬሽን 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በዛሬው ዕለት በኢንተርኮንቲነንታል አዲስ ሆቴል አድርጎ በስኬት አጠናቋል።

የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ እያሱ ወሰን በጉዞ ምክንያት ያልተገኙበትን የዛሬውን ጠቅላላ ጉባኤ ምዕላተ ጉባኤው መሟላቱ ከተረጋገጠ በኋላ እሳቸውን በመተካት የፅህፈት ቤት ሀላፊው አቶ ፓውሎስ ማዳ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር እንዲጀመር ተደርጓል።

ከዛም የ 15ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ ለተሳታፊዎች ቀርቦ በሙሉ ድምፅ የፀደቀ ሲሆን በመቀጠልም የ 2009 የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በፅህፈት ቤት ሀላፊው ቀርቦ በተመሳሳይ መልኩ በተሳታፊዎቹ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

በመቀጠል የፌደሬሽኑ የሂሳብ ሪፖርት በውጪ ኦዲተር እንዲቀርብ ተደርጎ በቀረበው የሂሳብ ሪፖርት ላይም አስተያየት ተሰጥቶበት ያለምንም ተቃውሞ በሙሉ ድምፅ የፀደቀ ሲሆን ከሻይ እረፍት መልስም የፌደሬሽኑ የ 2010 የስራ እቅድና የማስፈፀሚያ በጀት ለጉባኤው ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በ 2010 እቅድ ላይ ውይይትና ጥያቄዎች ከተስተናገዱ በኋላም የፅህፈት ቤት ሀላፊው ለተሳታፊዎች እቅዱን እንዲያፀድቁት አቅርበው ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ተቀብሎ አፅድቆታል።

በዉይይቱ ላይ የፅህፈት ቤት ሀላፊው የአዲስ አበባ ህዝብ የቦክስ ስፖርትን እንደተጠማ ነገርግን ፌደሬሽኑ ውድድሮችን ለማድረግ ትልቅ የቦታ እጥረት እንደገጠመው ገልፀው የዘንድሮውን የመጀመሪያ ዙር የቦክስ ውድድርም ቦታ በመጥፋቱ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ለማድረግ መታሰቡን አስረድተዋል።

አቶ ፓውሎስ ንግግራቸውን በመቀጠልም በቀጣይ ፌደሬሽኑ የራሱ የሆነ የመወዳደሪያ ስፍራ የመገንባት፣ ክለቦችን የማጠናከር፣ ፌደሬሽኑ በራሱ ገቢ እንዲተዳደር የማድረግ፣ ተተኪዎችን በተጠናከረ መልኩ የማፍራት፣ የሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ውድድሮችን ተሳትፎ የማሳደግ እና የወዳጅነት ጨዋታዎችን የማከናወን እቅድ መያዙን አስታውቀዋል። 

ክልሎችን እና የተለያዩ ክለቦችን ወክለው የመጡ የውይይቱ ተሳታፊዎችም የፌደሬሽኑ ወቅታዊ አመራር ጥሩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን እና ከቀደሙት አመራሮች በተሻለ እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ ምስክርነታችን ሰጥተው ነገርግን ከትጥቅ ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉና የፌደሬሽኑ አመራር ትኩረት እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።

የአማራ ክልልም የፌደሬሽኑ የወቅቱ አመራር እየፈፀመ ያለው ተግባር አመርቂና የሚበረታታ እንደሆነ በመግለፅ በተወካዩ አማካኝነት ለፅህፈት ቤቱ ሀላፊ የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማትን አበርክቷል።  

ከዛም የተጫዋቾችን ዝውውር የተመለከተ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ በሙሉ ድምፅ ምላዕተ ጉባኤው ያፀደቀው ሲሆን በፌደሬሽኑ ሶስት የተጓደሉ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምትክም ምርጫ ተደርጓል። 

በዚህም መሰረት አቶ ሰለሞን ታደሰ ከኦሮሚያ በስምንት ድምፅ፣ አቶ ወገኔ ታደሰ ከአማራ በሰባት ድምፅ እና ወ/ሮ ውባየው አማረ ከአፋር በአምስት ድምፅ ለተጓደሉት የስራ አስፈፃሚ አባላት ተተኪ ሆነው ሲገቡ አቶ ሰይፈ በርሄ ከአዲስ አበባ በአራት ድምፅ በተቀዳሚ ተጠባባቂነት እንዲያዙ ተደርገዋል።

በመጨረሻም መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው በአቶ ፓውሎስ የመዝጊያ ንግግር በተሳካ ሁኔታ ፍፃሜውን አግኝቷል።

Advertisements