ሹም ሽር / ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ፒተር ቦዥን አሰናብቶ አዲስ አሰልጣኝ መቅጠሩን አሳወቀ

ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ለሰባት ወራት የዋና ቡድኑን አሰልጣኝ ሆነው ሲሰሩ የቆዩት እና በሁሉም ውድድሮች ላለፉት 12 ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻሉትን ሆላንዳዊው ፒተር ቦዥን ከሀላፊነታቸው አንስቶ በምትካቸው አዲስ አሰልጣኝ ቀጠረ።

ባለፈው አመት አያክስን በዩሮፓ ሊግ ለፍፃሜ ማብቃት የቻሉት ፒተር ቦዥ በክረምቱ ወደ ጀርመን አቅንተው የቦሩሲያ ዶርትሙንድ አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።

አሰልጣኙ ዶርትሙንድን ከያዙ በኋላ አጀማመራቸው ያማረ የነበረ ቢሆንም ቀስ በቀስ በሚያስገርም መልኩ የውጤት ቀውስ ውስጥ በመግባት በተደጋጋሚ መሸነፍ ችለዋል።

ትናንት በተደረገው የቡንደስሊጋ ጨዋታም በዎርደር ብሬመን 2-1 በመሸነፉቸው ባለፉት ሁለት ወራት አንዴም ሳያሸንፉ ደረጃቸው ወደ ሰባተኛ አሽቆልቁሏል።

በዩሮፓ ሊጉም በቶተንሀም እና በማድሪድ ተቀድመው ከምድባቸው ሶስተኛ ደረጃን በመያዛቸው ወደ ዩሮፓ ሊጉ መቀላቀል ግድ ብሏቸዋል።

በዚህም መሰረት ክለቡ ከአሰልጣኙ ጋር ከተነጋገረ በኋላ ከሀላፊነታቸው ማንሳቱ ይፋ አድርጓል።በምትካቸው ከኮሎኝ በቅርቡ ከሀላፊነታቸው የተሰናበቱት ፒተር ስቶገር እስከ አመቱ መጨረሻ ድረስ ቡድኑን እንዲያሰለጥኑ ተሹመዋል።

ስቶገር አራት አመት ያሰለጠኑት ኮሎኝን ወደ ቡንደስሊጋው እንዲያድግ ካደረጉ በኋላ ባለፈው አመት በቡንደስሊጋው አምስተኛ ደረጃ ይዘው ማጠናቀቅ ቢችሉም ዘንድሮ ግን ማሸነፍ እንኳን ከብዷቸው ሁለት ነጥብ ብቻ በማግኘት ቡድኑን ለውጤት ቀውስ በመዳረጋቸው ከሀላፊነታቸው መሰናታበታቸው ይታወሳል።

አሰልጣኙ ወደ ዶርትሙንድ ማቅናታቸው ካረጋገጡ በኋላ ” በህይወትህ የምታገኘው እድል” ሲሉ ደስታቸውን ገልፀዋል።የመጀመሪያ ስራቸውንም ዛሬ ቡድኑን በማሰልጠን እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።

የዶርትሙንድ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሀንስ ዩአኪም ዋዥኬም ሲናገሩ “ባለፈው ምሽት ከፒተር ቦዥ ጋር ባደረግነው ውይይት አሰልጣኙ ከሀላፊነቱ እንዲነሳ ወስነናል።በጥሩ መንገድም ውላችንን አፍርሰናል።በክለቡ ስምም ላመሰግናቸው እወዳለው።አሁንም ትልቅ አሰልጣኝ እና ስብእና እንዳለው እናስባለን።”ሲሉ ተናግረዋል።

Advertisements