ዩናይትድ ከ ሲቲ / በብዙ አውድ የተከበበና የውድድር ዘመኑን ማሳረጊያ በትልቁ ሊጠቁም የሚችል የመጨረሻው መጀመሪያ  

ማንችስተር ሲቲ ከተከታዩና ከምሽቱ ተጋጣሚ ባላንጣው ማንችስተር ዩናይትድ በስምንት ነጥቦች ብልጫ እየመራ ሲሆን ከሰሞነኛ ጥቂት መንገጫገጮች በቀር በዚህ መልክ እንደሚቀጥል ሲጠበቅ የማይሸነፍ ምሉዕ ስብስብ አድርጎ ለመመልከት ቢከብድም ብዙ የእግር ኳስ ተንታኞችም የከዚህ ቀደም የሊጉን ሪከርድ በሰበረ መልኩ የውድድር ዘመኑን ሊያጠናቅቅ እንደሚችል ገምተውለታል። ቀጣዩ የሚኪያስ በቀለ ፅሁፍም ሞውሪንሆ ከውድድር ዘመኑ ትልቁ ፈተናቸው ጋር የሚፋጠጡበትን፣ በውስጡ ብዙ ጉዳዮችን የሰነቀውን እና የውድድር ዘመኑን አጨራረስ በተመለከተ ትልቅ ጥቆማ ሰጪውን ትንቅንቅ ከተለያዩ አቅጣጫዎች አንፃር ፈትሾ በዝርዝር ሊነግረን ተዘጋጅቷል።


ሲቲ ካደረገው 15 የመክፈቻ ጨዋታ አንዱን በአቻ ውጤት ከመፈፀሙ በቀር 14 ያህሉን ማሸነፍ ችሏል። የፔፕ ጋርዲዮላው ስብስብ ካስመዘገበው ውጤት ጎን ለጎን ግን ያሳየው አስደናቂ አጨዋወት የብዙዎች መነጋገሪያ እንዲሆን አስችሎታል። 

የኢትሀዱ ክለብ በዘንድሮው የውድድር ዘመን የያዘውን ውጤት ይዞ መዝለቅ ከቻለም ንፅፅሩ ከተፎካካሪዎቹ ሌሎች የሊጉ ክለቦች ጋር መሆኑ ዋጋ ያጣና ንፅፅሩ ከአመታት በፊት በፕሪምየር ሊጉ ትልቅ ጀብዱን ከፈፀሙ የሊጉ አይረሴ ቡድኖች ጋር ይሆናል።

በአንድ የውድድር ዘመን ብዙ ነጥብ ያስመዘገበ ስብስብ : 95 – ቼልሲ 2004-05

በምዕራብ ለንደኑ ክለብ የመጀመሪያ የውድድር ዘመናቸው ላይ በነበሩት ጆሴ ሞውሪንሆ ይሰለጥን የነበረው የያኔው ቼልሲ ከተከታዩ አርሰናል የ 12 ነጥቦችን ብልጫ በመያዝ በ 50 አመት ውስጥ የመጀመሪያውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ማሳካቱ አይረሳም። 

ፍራንክ ላምፓርድና ጆን ቴሪን የመሰሉ ከዋክብት የያዘው የያኔው የሞውሪንሆ ስብስብ የፕሪምየር ሊግ ንግስናውን ሚያዝያ መጨረሻ ላይ ሲያረጋግጥ ገና ሶስት ያህል ጨዋታዎች ይቀሩት ነበር። 

በአንድ የውድድር ዘመን ብዙ ግቦች ያስቆጠረ ስብስብ : 103 – ቼልሲ 2009-10

በቼልሲ ቤት በመጀመሪያ የውድድር ዘመናቸው ክብረ ወሰን መጨበጥ የቻሉ ሌላኛው አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ ናቸው። 

ጣሊያናዊው አለቃ የኤፍኤ ዋንጫን ጨምሮ የሁለት ዋንጫ ድልን ባስመዘገቡበት የውድድር ዘመን ስብስባቸው በመጨረሻ ጨዋታው ዊጋንን 8-0 የረታበትን እና የሊግ አሸናፊነቱን ያረጋገጠበትን ጨዋታ ጨምሮ 103 ግብ አስቆጥሮ አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገቡ አይረሳም።

የአንቸሎቲው ስብስብ በመጨረሻ ሶስት ጨዋታው 17 ጎሎችን ሲያስቆጥር ዲድየር ድሮግባና ፍራንክ ላምፓርድ እያንዳንዳቸው 29 እና 22 ግቦችን በማስቆጠር የውድድር ዘመኑን በስኬት ማጠናቀቅ ችለዋል።

በአንድ የውድድር ዘመን ለረጅም ጊዜያት ሽንፈት ያልገጠመው ስብስብ : የአርሰናል አይበገሬው ስብስብ 2003-04

የአርሰናል የ 49 ጨዋታ ያለመሸነፍ ክብረ ወሰን በ 2002-03 የውድድር ዘመን ቡድኑ በመጨረሻ ሁለት ጨዋታ ሳይሸነፍ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ቢሆንም የአርሰን ቬንገር ስብስብ የአለመሸነፍ ጉዞውን በቀጣዩ አመት አጠናክሮ በመቀጠል ሚያዚያ አጋማሽ ከቶትነሀም ጋር በነበረው የደርቢ ትንቅንቅ የሊጉን ዋንጫ ያረጋገጠበትን አስደናቂ ውጤት አስመዘገበ። 

የቬንገር የወቅቱ ስብስብ ዋንጫውን ያረጋገጠበት እና 90 ነጥብን የረገጠበት የቶትነሀም ጨዋታ ግን አርሰናል በውድድር ዘመኑ ካስመዘገበው 12 የአቻ ውጤት አንዱ ነበር። 

የሲቲ የዘንድሮ ሂደት ከቀደሙ ክብረ ወሰኖች ጋር ሲነፃፀር ምን ይመስላል?

ማንችስተር ሲቲ 2017 : ተጫ 15 አሸ 14 1 ተሽ 0 አገ 46 10 ንግ +36 ነጥብ : 43

ቼልሲ 2009-10 : ተጫ 15 አሸ 12 0 ተሸ 3 አገ 37 ገባ 10 ንግ +27 ነጥብ : 36

አርሰናል 2003-04 : ተጫ 15 አሸ 10 5 ተሸ 0 አገ 29 ገባ 11 ንግ +18 ነጥብ : 35

ቼልሲ 2004-05 : ተጫ 15 አሸ 11 3 ተሸ 1 አገ 37 ገባ 6 ንግ +31 ነጥብ : 36

በዚህን ሰአት ሲቲ በ 2004-05 የሊጉን የምንግዜም ትልቅ ነጥብ ያስመዘገበው የቼልሲ ስብስብ በመጀመሪያዎቹ 15 ጨዋታዎቹ ከነበረው ነጥብ በሰባት ብልጫ ያለው ነጥብ ላይ ይገኛል። እናም የጋርዲዮላ ስብስብ የ 100 ነጥብ ክብረ ወሰንን መስበር ይችል ይሆን? 

በሌላ በኩል በግብ ደረጃ የ 2009-10 የአንቸሎቲ ስብስብ በመጀመሪያዎቹ 15 ጨዋታዎች ካስቆጠራቸው ግቦች በዘጠኝ ግብ ብልጫ ላይ መቀመጥ የቻለ ሲሆን በመከላከል በኩልም ደግሞ ከሞውሪንሆው ቼልሲ ስብስብ ጋር ብናነፃፅረው የተቆጠረበት ግብ በአራት ብልጫ ያለው ነው። 

የያኔው የሞውሪንሆ ስብስብ በጠንካራ የመከላከል ጥንካሬ ላይ ተመስርቶ የተገነባ መሆኑን ወደኋላ ተመልሰን ስናስታውስ ግን በንፁህና ክፍት እግር ኳሱ የተደነቀው የጋርዲዮላ ስብስብ ክብር ሊቸረው እንደሚገባ ያስገነዝበናል።

በተያያዘ መልኩ የያኔው የሞውሪንሆ ስብስብ በውድድር ዘመኑ 20 የሊግ ግቦችን የታከከ ስኬት ያለው ተጫዋች ያልነበረውና የቡድኑ የያኔው ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በውድድር ዘመኑ ሙሉ 13 ግቦችን ያስቆጠረው ላምፓርድ መሆኑን ስናስብ ገና ካሁኑ 46 ግቦችን ያስቆጠረውን የጋርዲዮላን ስብስብ ለማደነቅ እንገደዳለን። 

ከጎል ንፅፅር ምጣኔው ጋር በተያያዘ ግን 30 ግቦችን በውድድር ዘመኑ ያስቆጠረውን ቴሪ ሄነሪን የያዘውን የአይበገሬውን የያኔ የአርሰናል ስብስብ እና በአንቸሎቲ ስር 29 ግቦችን በአንድ የውድድር ዘመን ማስቆጠር የቻለውን ድሮግባን ያቀፈውን የቼልሲ ስብስብ መርሳት የማይቻል ነው።

ነገርግን የጋርዲዮላ ስብስብ በግብ ማምረት በኩል በአንድ ተጫዋች ላይ ጥገኛ አለመሆኑን ባሳየ እና የውድድር ዘመኑን ከ 20 በላይ ግብ የሚያስቆጥርለት ተጫዋች ሊያገኝ እንደሚችል ባስመሰከረ መልኩ ሰርጂዮ አግዌሮ እና ራሂም ስተርሊንግ በዘጠኝ ግብ ቀዳሚ ሲሆኑ ጋብሬል ጂሰስ በበኩሉ በአንድ አንሶ ስምንት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። 

ሊሮይ ሳኔ እና ዴብሩይ በጋራ ያስቆጠሩትን ትተን እንኳን የሲቲ ተከላካይ ክፍል በመጀመሪያ 15 ጨዋታዎች አምስት ግቦችን በማስቆጠር ምን ያህል ቡድኑ ከየትኛውም አቅጣጫ ግብ ማስቆጠር እንደሚችል ማስመስከር የቻለ ነው።

የዛሬ ምሽቱ ትንቅንቅ ደግሞ በሁለት ትልልቅ ፍፃሜዎች የተከበበ ነው። ምክንያቱም በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሊጉ ላይ የዩናይትድ በሜዳው ላይ የያዘው ያለመሸነፍ ሪከርድ ወይም የሲቲ በየትም ሜዳ ላይ እጅ ያለመስጠት ጉዞ የሚያከትምበት ነው። 

ለዩናይትድ ሽንፈት ሲቲን በ 11 ነጥቦች ርቀት ሽቅብ እንዲመለከት ሲያስገድደው አንድን ክለብ በያዙ በሁለተኛ አመት ላይ ዋንጫ ማንሳት ለለመዱት ሞውሪንሆ ነገሩን የሚያከብድ ይሆናል። በሌላ በኩል ቡድናቸው ድል ካደረገ ደግሞ የምንግዜም ባላንጣውን በቅርብ ርቀት መከተል የሚያስችለውን ውጤት ያስገኝለታል። 

ሞውሪንሆ የውድድር ዘመኑን ከባድ ፈተና በሚያስተናግዱበት በዚህ ዕለት ዩናይትድ ከ 1970 (ካደረጉት 83 ጨዋታ አራቱ ብቻ በፈረንጆቹ የመጨረሻ ወር በታህሳስ ቢደረግም) ወዲህ በታህሳስ ወራት ባደረገው ጨዋታ ለሲቲ እጅ አለመስጠቱ የፖርቹጋላዊውን አለቃ ስብስብ በራስ መተማመን በጥቂቱም ቢሆን የሚያሳድግ ይሆናል።

በዚህም ተባለ በዚያ ግን ሞውሪንሆ በሊጉ ላይ ልጓም አልገኝለት ያለውን የጋርዲዮላ ስብስብ እንዴት ያስቁሙት? የሚለው ትልቅ መልስ የሚፈልግ ጥያቄ ነው። 

ሲቲ ከዌስትሀም፣ ሳውዝአምፕተን እና ሀደርስፊልድ ያደረገውን ጨዋታ የፈፀመው በመጨረሻ ደቂቃ ግቦች በተመሳሳይ የ 2-1 ውጤት ነው። የግብ ክልል ውስጥ አፈግፍጎ መቀመጥ ለፈጣኖቹ ራሂም ስተርሊንግ እና ሊሮይ ሳኔ ቦታን የሚያጠብባቸው ሲሆን ኳስ ማሻገርን ለተካኑት ዴቪድ ሲልቫና ኬቨን ዴብሩይም ነገሮችን የሚያከብድ ጥሩ መላ ነው።

ምንም እንኳን ከኤቨርተን አቻ ውጤት ውጪ በመጨረሻ ሰአት በጠባብ መንገድ ከመሸነፍ የተረፈና ሲቲን መቋቋም የቻለ ክለብ የሌለ ቢሆንም የጋርዲዮላ ስብስብ ማቆም የማይቻል ተደርጎ የሚታይ አይደለም። 

ከትልልቅ ቡድኖች ጋር በተለይም ከሜዳቸው ውጪ አማካኙን በማጠር ወደኋላ አፈግፍጎ መጫወት እና ኳስን ለተቃራኒ መተው የሚያስደስታቸው ሞውሪንሆም ዛሬም በድጋሚ ይህን አጨዋወት ለመጠቀም እንደሚችሉም የሚጠበቅ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ጫና ላለበት ጨዋታ በቀላሉ እጅ የሚሰጠው የሲቲ የኋላ መስመር የሞውሪንሆ ስብስብ ተጭኖ ከተጫወተ ሰብሮት ሊገባ የሚችለው አይነት ነው። 

ነገርግን የምሽቱ ትንቅንቅ ሲቲ እንዴት ዩናይትድን ያቆመዋል በሚለው ላይ ሳይሆን ዩናይትድ የሲቲን ከባድ የማጥቃት ወጀብ መቋቋም ይችል ይሆን በሚለው ሙግት ላይ የሚያርፍ መሆኑና ለውድድር ዘመኑ ማሳረጊያ ቁልፍ ጥቆማ ሰጪ ከባድ ፍልሚያ መሆኑ እርግጥ ነው። 

Advertisements