የግብፁ አል አህሊ ከስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር እንደሚጫወት አሳወቀ

ግብፁ ሀያል ቡድን የሆነው አል አህሊ በወሩ መጨረሻ ከስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እንደሚያደርግ አሳወቀ።

በስፔን ከመሪው ባርሴሎና በስድስት ነጥብ አንሶ በሶስተኝነት ደረጃ ላይ የተቀመጠው  አትሌቲኮ ማድሪድ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ግብፅ አቅንቶ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እንደሚያደርግ ታውቋል።

ቡድኑ 2011 ላይ የዛማሌክ የ 100 አመት የምስረታ ክብረ በአል ለማክበር በቀረበለት ጥሪ መሰረት ወደ ግብፅ አቅንቶ ዛማሌክን መግጠሙ ይታወሳል።

አሁን ደግሞ የግብፁን አህሊ በአቋም መፈተሻ ለመግጠም በፈረንጆቹ ታህሳስ 30 ላይ በአሌክሳንድሪያ ቦርጅ ኤል አረብ ስታድየም ቀጠሮ ይዟል።

የአል አህሊው ፕሬዝዳንት የሆኑት መሀሙድ ኤል ካሀቲብ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ “ከአሸባሪነት ይልቅ ሰላም” በሚል መርህ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል።

አትሌቲኮ ማድሪድም ከጨዋታው አንድ ቀን ቀደም ብሎ በግል አይሮፕላን ወደ ግብፅ እንደሚያቀና ታውቋል።

ደጋፊዎችም በነቂስ በስታድየሙ ተገኝተው ጨዋታውን እንዲከታተሉ የጥበቃ አካላት እንዳይከለከሉ የተደረገ ሲሆን በእለቱ የሚገኘው የትኬት ገቢም ለግብፅ ሰማእታት ቤተሰቦች ድጋፍ እንደሚደረግ ታውቋል።

አል አህሊ በግንቦት 2016 በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ሮማን ገጥሞ 4-3 ካሸነፈ በኋላ የአውሮፓ ቡድንን ለመግጠም ሲዘጋጅ ለመጀመሪያ ጊዜው ነው።

Advertisements