ስኬት / መሀመድ ሳላ የቢቢሲ የአፍሪካ የአመቱ ምርጥ ተጫዋችነትን ክብር ተቀዳጀ

የሊቨርፑሉ ኮከብ መሀመድ ሳላ የቢቢሲ የአፍሪካ የአመቱ ምርጥ ተጫዋችነትን ክብር ተቀዳጅቷል። 

ከዚህ ቀደም አብዲ ፔሌ፣ ጆርጅ ዊሀ እና ጄጄ ኦካቻን የመሰሉ የቀድሞ የአፍሪካ ከዋክብት ያገኙትን ክብር የተጋራው ሳላ ከሀገሩ ልጆች ከሙሀመድ ባራካት (2005) እና ከዝነኛው አቡትሪካ (2008) ቀጥሎ ሽልማቱን የወሰደ ሶስተኛው ግብፃዊ ሆኗል።

የ 25 አመቱ ግብፃዊ የፊት መስመር ተጫዋች የጋቦኑን ፒር ኤምሪክ ኦቦምያንግ እና ጊኒያዊውን አማካኝ ናቢ ኬይታን እንዲሁም ናይጄሪያዊውን ተመላላሽ ቪክተር ሞሰስን አስከትሎ በቀዳሚነት ፉክክሩን ፈፅሟል።

በሊቨርፑል ክብረ ወሰን የ 36.9 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ ባሳለፍነው ክረምት መርሲሳይድ የደረሰው ሳላህ ባለፉት አራት ወራት ቆይታው በ 24 ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ 19 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። 

ሳላህ ከሽልማቱ በኋላ “ይህን ክብር በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ። የሆነ ነገርን ማሸነፍ ሁሌም ልዩ ስሜት አለው። ትልቅ የውድድር ዘመን እንደነበረኝ ስለተሰማኝ በጣም ደስተኛ ነኝ።

“የምንግዜውም የግብፅ ምርጥ ተጫዋች ለመሆን ስለምፈልግ ጠንክሬ እሰራለሁ። ሁሌም የራሴን መንገድ መከተል የምፈልግ ሲሆን በግብፅ የሚገኝ ማንኛውም ሰው የእኔን መንገድ እንዲከተል አፈልጋለሁ።” በማለት በሽልማቱ የተማውን እርካታ ገልጿል።

ከሮማ ከመጣ ወዲህ በቀዮቹ ቤት የክለቡ የወሩ ኮከብ ተጫዋችነትን ክብርን ባሰለፍነው ነሀሴና መስከረም ያገኘው ሳላ የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋችነትን ክብር በማግኘቱ መደሰታቸውን የክለቡ ጀርመናዊ አለቃ የርገን ክሎፕ ገልፀዋል።

ክሎፕ በንግግራቸው “ይገባዋል! እኔ እድለኛ ሰው ነኝ። ከጥቂት አስደናቂ ብቃት ካላቸው ተጫዋቾች ጋር ሰርቻለሁ። አሁንም ከሞ ጋር እየሰራሁ ነው።

“ጥሩው ነገር እሱ ወጣት፣ ለመሻሻል ክፍተት ያለው እና ልንሰራበት የምንችለው አቅም የታደለ ነው። .. እውነቱን ለመናገር ከእሱ ጋር መስራት ትልቅ ደስታ ነው።” በማለት ኮከባቸውን አሞካሽተዋል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪነትን እየመራ የሚገኘው ሳላ ሀገሩን ለአለም ዋንጫ ያበቃ የፈርኦኖቹ ወሳኙ ተጫዋች  ነው። 

Advertisements