ዚዳን፣ ሪያል ማድሪድ የዓለም ክለቦች ዋንጫን ማሸነፍ እንደሚፈልግ ገለፀ

ዚነዲን ዚዳን፣ ሪያል ማድሪድ የላ ሊጋ እና የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ለማግኘት ከመፋለሙ በፊት የዓለም ክለቦች ዋንጫን በክለቡ የዋንጫ መደርደሪያ ላይ በተጨማሪነት ማከል እንደሚፈልግ ተናግሯል።

የዚህ ውድድር የሁለት ጊዜ ሻምፒዮኑ ማድሪድ የኤመራቲው ክለብ የሆነውን አልጀዚራን በግማሽ ፍፃሜው ረቡዕ በአቡ ዳቢው ዛየድ ስፖርትስ ሲቲ ስታዲየም ይገጥማል።

እናም በዚህ የውድድር ዘመን ከወዲሁ የአውሮፓ ሱፐር ካፕን እና የስፔን ሱፐር ካፕ ዋንጫዎችን ያነሳው ማድሪድ ይህን ዋንጫም ለሶስተኛ ጊዜ የማንሳት ከፍተኛ ፍላጎት አለው።

“ቀላል አይሆንም። ባለፈው ዓመት ይህን ውድድር ከማሸነፋችን በፊት በርካታ ችግሮች ነበሩብን።” ሲል ዚዳን ስለውድድሩ ተናግሮ “ቀላል የሚሆኑ ጨዋታዎች አይኖሩም። ሪያል ማድሪድ ስለሆንን ብቻም አናሸንፍም። ለጨዋታው የምንዘጋጅበት ጊዜ አለን። እናም ሰበብ የምናንደረድርበት ነገር አይኖርም።

“ይህ ማንንም እንግጠም ማንንም ማድረግ ያለብንን ነገር ማድረግ የሚገባን የውድድር ጊዜ ነው።

“በየውድድር ዘመኖች ላይ መውደቅና መነሳት የተለመደ ነገር ነው። ነገር ግን እስካሁን ያደረግናቸው ነገሮች አዎንታዊ ናቸው። ሁለት ዋንጫዎችን አሸንፈናል። ሶስተኛውንም ለማሸነፍ በሙከራ ላይ እንገኝለን።

“ከዚህ በኋላ ደግሞ ለላ ሊጋው፣ ለሻምፒዮንስ ሊጉና ለዋንጫው [ለስፔን የንጉስ ዋንጫ] የምንፋለምበት ቀሪ ስድስት ወራት ይኖሩናል።” ሲል ፈረንሳያዊው አሰልጣኝ ጨምሮ ገልፅዋል።

ሪያል ማድሪድ በ15 የላ ሊጋው ጨዋታዎች በሰበሰባቸው ነጥቦች ከመሪው ባርሴሎና በስምንት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሲገኝ፣ በሻምፒዮንስ ሊጉ ደግሞ 16 ክለቦች ተሳታፊ በሚሆኑበት የጥሎ ማለፍ ዙር ከፒኤስጂ ጋር ለመጫወት ተደልድሏል።

Advertisements