ቡጢ / የኢትዮጵያ ቦክስ ፌደሬሽን የ 2010 አንደኛ ዙር ሀገር አቀፍ የክለቦች ውድድር ተጀመረ

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌደሬሽን የ 2010 አንደኛ ዙር ሀገር አቀፍ የክለቦች ሻምፒዮና ውድድር በትንሿ ስታዲየም በተለያዩ ኪሎ ግራሞች በተደረጉ ግጥሚያዎች ዛሬ ቀትር ላይ ተጀምሯል።

ይህ በሴትና በወንድ ዘርፍ በአጠቃላይ ስምንት ግጥሚያዎችን ያስተናገደው የመጀመሪያው ቀን ውሎ በደጋፊዎች ዝማሬ የታጀበና ደማቅ እንዲሁም ደግሞ ልብ አንጠልጣይ ግጥሚያዎች የተስተዋሉበት ነበር።

በመክፈቻው ግጥሚያም በ 49 ኪ.ግ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚው ዳዊት ከበደ የፌደራል ፓሊሱን ፈይሰል መሀመድ መርታት ሲችል በተመሳሳይ ኪ.ግ የድሬድዋ ከነማውን ኖሌ መሀመድን ያስተናገደው እንደሻው አልዩ ሽንፈት አስተናግዷል።

በዕለቱ ሶስተኛ ግጥሚያ በ 52 ኪ.ግ የማራቶኑ ታምራት አበበ ከፌደራል ፓሊሱ ገዛኸኝ ፍቃዱ ተጋጥሞ ሲሸነፍ በተመሳሳይ ኪ.ግ ከኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚው ዳግም ሰለሞን ጋር የተፋለመው የማረሚያ ቤቶቹ ያቆብ በለጠ ተጋጣሚው እጁ ወልቆ ውድድሩን በማቋረጡ ፍልሚያውን በድል ተወጥቶ ለግማሽ ፍፃሜው መብቃት ችሏል።

አከራካሪና በነበረው፣ ትልቅ ፉክክር ባስተናገደውና የተለያዩ ሁነቶች በተስተዋሉበት የዕለቱ አምስተኛው ግጥሚያ በ 56 ኪ.ግ የማራቶኑ ፍቅረማሪያም ያዴሳና የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚው አብዱልሰላም አቡበከር ተገናኝተው ፍቅረማርያም አፍንጫው በመድማቱና ደሙ ሊቆም አልቻለም በሚል በዳኛ ውሳኔ አብዱልሰላም እንዲያሸንፍ ተደርጓል።

በዚህ በተፋፋመውና ከባባድ ምቶች በተሰነዘሩበት ትንቅንቅ ላይ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሰከንዶች በቀሩበት ወቅት ጨዋታው ተቋርጦ የአካዳሚ ተወካዩ አብዱልሰላም እንዲያሸንፍ መደረጉ በተሸናፊው ደጋፊዎች ዘንድ ቅሬታንና መጠነኛ ውሳኔውን የመቃወም ትዕይንት አስከትሎ ታይቷል።

በጨዋታዎቹ መሀከል የቀትሩ ፀሀይ ሳይበግረው በውድድሩ ስፍራ ተገኝቶ ተጋጣሚዎቹን ላበረታታው ደጋፊ ማነቃቂያ የሚሆኑ የካርድ ሽልማቶች በነበሩት የመክፈቻው መርሀ ግብር የዕለቱ ስድስተኛ ግጥሚያ በ 60 ኪ.ግ እዮብ ነጋሽ ከኤፍሬም ደቻሳ ተገናኝተው የድሬደዋ ተወካዩ እዮብ ድል ማድረግ ችሏል።

በሌላኛው የወንዶች መርሀ ግብር ደግሞ በተመሳሳይ የ 60 ኪ.ግ ግጥሚያ የፌደራል ፖሊሱ ዳዊት ፍቃዱ የማራቶኑን አሳስበው ከበደ ባስተናገደበት ጨዋታ በአማተር የቦክስ ጨዋታ ህግ በአንድ ዙር ሶስት ጊዜ ጥፋት ስለተቆጠረበት በዳኛ ውሳኔ ሽንፈት ደርሶበት ከውድድሩ ውጪ ሆኗል።

በመጨረሻም በሴቶች ዘርፍ በተደረገው መርሀ ግብር የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኗ ሀና ደረጄ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚዋን ቤተልሄም ገዛኸኝ አስተናግዳ ተጋጣሚዋን በመርታት ወደግማሽ ፍፃሜው መቀላቀል ችላለች።

ይህ ዛሬ የተጀመረው የአንደኛ ዙር መርሀ ግብር እስከ መጪው አርብ የሚቀጥልና በነገው ዕለት መርሀ ግብሩ በወንዶች ዘርፍ 23 በሴቶች ደግሞ ሁለት ግጥሚያዎችን የሚያስተናግድ ሲሆን የስፖርት አፍቃሪውም በትንሿ ስታዲየም በመገኘት ውድድሩን በነፃ መከታተል እና ተጋጣሚዎችን ማበረታታች እንደሚችል ታውቋል።

Advertisements