ያልተጠበቁ ውድቀቶች ፦ ሊጋቸውን በሰፊ ነጥብ ከመምራት ዋንጫውን ወደመነጠቅ ያመሩ ክለቦች ትውስታ

ከሌሎች የአውሮፓ ሊጎች በተለየ ጠንከር ያለ ፉክክርን ያስተናግዳል የሚባልለት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው የውድድር ዘመን  ገና አጋማሹን በቅጡ ባያደርግም በፔፕ ጓርዲዮላ የሚመሩት ሰማያዊዎቹ ማንችስተሮች ዋነኛ ተቀናቃኞቻቸውን በአሳማኝ ሁኔታ በማሸነፍ ጭምር ሊጉን በ 11 ነጥብ ልዩነት መምራት ጀምረዋል ፤ ከወዲሁም በርካታ የእግር ኳስ ተንታኞችና የስፖርቱ ቤተሰቦች የ2017/18 የውድድር ዘመን የሊጉ ዕጣ ፈንታ የተበላ ዕቁብ መሆኑን መግለፃቸውን ተያይዘውታል፡፡

​እግር ኳስ እጅጉን ከእርግጠኝነት ከራቁ የስፖርት አይነቶች ግንባር ቀደሙ ነው ፤ስፖርቱ በባህሪው በመጨረሻ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ላይ የሚቆጠሩ ጎሎች እና በሚፈጠሩ ሁነቶች ያልተጠበቁ ውጤቶች ሲፈጠሩበት በተደጋጋሚ የታየ መሆኑ  ማንም ቀድሞ እርግጠኝነት ላይ እንዳይደርስ ያስገድደዋል፡፡

በጨዋታዎች ላይ በሰፊ የጎል ልዩነት እየመሩ የነበሩ ክለቦች በተቃራኒያቸው መልሶ ማንሰራራት ጉድ ሲሆኑ ብዙ ጊዜ የተመለከትን ሲሆን በተመሳሳይ ደግሞ ሊጋቸውን በሰፊ የነጥብ ልዩነት ይመሩ የነበሩና የማታ ማታ ተቀድመው የሊጉን ዋንጫ ያስረከቡ ክለቦችን መመልከት አዲስ አይደለም፡፡

ለዚህም ማሳያ ይሆነን ዘንድ በቅርብ አመታት የተከሰቱ እና ከኋላ ተነስቶ በቀደማቸው ቡድን ዋንጫ የተነጠቁ ክለቦችን እናወሳለን፡፡

ማንችስተር ዩናይትድ (እ.ኤ.አ 1998)

የሰር አሌክስ ፈርጉሰን አብዮት በእንግሊዝ እግር ኳስ ላይ እጅጉን በተፋፋመበት የ90ዎቹ ዘመን በአዲስ መልክ የተዋቀረው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አምስት ጊዜ ሲካሄድ አራቱን ዋንጫዎች ከፍ ማድረግ የቻለው የኦልድትራፎርዱ ክለብ ነበር፡፡ ታዳጊ ተጫዋቾቻቸውን ከፊት በማስቀደም በአገሪቱ እግር ኳስ ላይ ወረራን የፈፀሙት ስኮትላንዳዊ አዛውንት የ1997/98 ፕሪምየር ሊግን ከማሸነፍ የሚያግዳቸው አንዳችም ኃይል እንደሌለ የሁሉም እምነት የነበረ ሲሆን በወርሃ መጋቢት ላይም በሁለተኛ ደረጃ  ከሚከተላቸው የሰሜን ለንደን ክለብ አርሰናል በ 11 ነጥብ ብልጫ ነበራቸው፡፡ 

በዚሁ የውድድር ዘመን ከጃፓን ሊግ ወደለንደኑ ክለብ በመምጣት መድፈኞቹን መምራት የጀመሩት ፈረንሳያዊ አርሰን ዌንገር የሚመሩት አርሰናሎች በ11 ነጥብ ቢበለጡት በእጃቸው ላይ ሶስት ቀሪ ጨዋታዎች ነበሩ፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “የጨዋታ ፕሮግራሞች ከኛ ይልቅ ለዩናይትዶች የተመቸ ነው” የሚል ንግግርን ካደረጉ በኋላ “አርፎ ስራውን ቢሰራ ይሻለዋል ይህ የጃፓን ሊግ አይደለም ” የሚል ኃይለ ቃላዊ አፀፋን ከቆፍጣናው ባላንጣቸው ያገኙት ዌንገር በእጃቸው ላይ የነበሯቸውን ቀሪ ጨዋታዎች በሙሉ ማሸነፍ ከመቻላቸውም በላይ በመሃል ራሱ ዩናይትድን በማሸነፍ በሊጉ አናት ላይ የተቀመጡ ሲሆን ተከታታይ አስር ጨዋታዎችን ካሸነፉ በኋላ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ውጤት ቢያጡም የመጀመሪያውን የሊግ ዋንጫ ለመድፈኞቹ በማስገኘት ቀያይ ሰይጣኖቹን ጉድ ሰሩ፡፡

አርሰናል(እ.ኤ.አ 2003)

ወደእንግሊዝ እግር ኳስ ብቅ ካሉ በኋላ ስማቸው ጉልህ ለመሆን ጊዜ ያልፈጀበት አርሰን ዌንገር የ2002/03 የውድድር ዘመን ሲጀምር ክለቡን ከያዙ በኋላ ሶስተኛ የሊግ ዋንጫ እና ኤፍ ኤ ካፑን በማሸነፍ የራስ መተማመናቸውን በማሳደግ ነበር አዲሱን የውድድር አመት የጀመሩት፡፡ የተዋበ እና ማጥቃት ላይ ያተኮረ አጨዋወትን የሚከተለው ቡድናቸው ያገኘው ተቀባይነት ከፍ ያለ ሲሆን በተጠናቀቀው የውድድር አመትም በኮከብ አስቆጣሪው ቴሪ ሄንሪ 24 ጎሎች ታግዘው 85 ጎሎችን በማስቆጠር ክብረወሰን ማስመዝገብም ችለው ነበር፡፡

በወርሃ መጋቢት ወርም አርሰናል ከተከታዮቹ ማንችስተር ዩናይትድና ኒውካስትል ዩናይትድ በ 8 ነጥቦች በመብለጥ በምቾት ሊጉን ይመራ የነበረ ሲሆን ቡድኑ ባለተጠበቀ ሁኔታ አሽቆልቁሎ ዋንጫውን እስኪያጣ ድረስ ሁሉም ይሻምፒዮንነት ቅድሚያ ግምቱን ለመድፈኞቹ ሰጥቶ ነበር፡፡
የሆነው ሆኖ ቅዠት ቢሆን የሚመኙትን የአመቱን አፈፃፀም ያሳለፉት አርሰናሎች ከመጨረሻዎቹ 9 ጨዋታዎች አራቱን ብቻ በማሸነፍ በብላክበርን ሮቨርስና በሊድስ ዩናይትድ ሲሸነፉ ፣ ከአስቶን ቪላ ፣ ቦልተን ዎንደረርስ እና ከተቀናቃኛቸው አርሰናል ጋር በአቻ ውጤት አጠናቀው ዋንጫውን ለመነጠቅ ተገደዱ፡፡

በተቃራኒው ዩናይትድ በ2002 ቦክሲንግ ደይ ወቅት በሚድልስብራ ከተሸነፈ በኋላ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ምንም ሽንፈትን ሳያስተናግድ አመቱን ያጠናቀቀ ሲሆን በሂደቱም 15 ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ሶስቱን በአቻ ውጤት አጠናቋል፡፡ ለዚህ አስደናቂ የስኬት ጉዞውም የሰር አሌክሱ ስብስብ የሊጉን ዋንጫ ከፍ አድርጎ ማንሳት ችሏል፡፡

ኒውካስትል ዩናይትድ (እ.ኤ.አ 1996)

በኬቨን ኪገን ይመራ የነበረውና በማጥቃት ላይ በሚያተኩረው ውብ እግር ኳሱ የበርካቶችን ቀልብ መሳብ ችሎ የነበረው ኒውካስል ዩናይትድ በጥር ወር ላይ ሊጉን ከተከታዩ ማንችስተር ዩናይትድ በ 12 ነጥቦች በመብለጥ ይመራ የነበረ ሲሆን ከ 1927 በኋላ የመጀመሪያውን የአገሪቱን ሻምፒዮንነት ክብር ወደሴንት ጄምስ ፓርክ እንደሚያመጣ የእግር ኳሱ ዓለም እምነት ነበር፡፡

ተከታዩ የነበረው የሰር አሌክስ ፈርጉሰን ስብስብ በበኩሉ በርከት ያሉ ታዳጊዎችን ወደዋናው ቡድን ከማሳደጉ በተጨማሪ ቡድኑን በነሱ ጫንቃ ላይ መመስረቱ የወቅቱ መነጋገሪያ ሆኖ የነበረ ሲሆን በታዋቂው የስካይ ስፖርት ተንታኝ አለን ሃንሰንም “በእፃናት ምንም ነገር ማሸነፍ አትችልም” የሚል ዝነኛ የሰላ ትችት ደርሶበት ነበር፡፡

ሊጉን በ 11 ነጥብ እየመሩ የካቲትን ያገመሱት ማግፓይሶቹ ከየካቲት ጀምሮ እስከመጋቢት ወር ካደረጉት ስምንት ጨዋታዎች በስድስቱ ነጥብ በመጣል ወደውድቀት ያመሩ ሲሆን በአመቱ መጨረሻም በ”ህፃናቶቹ” ቀይ ለባሾች በአራት ነጥብ ብልጫ ተወስዶባቸው ከሊጉ ዋንጫ መገናኘት ሳይችሉ ቀሩ፡፡

ሪያል ማድሪድ (እ.ኤ.አ 2004)

በውድድር አመቱ ጅማሮ ዴቪድ ቤካምን ከማንችስተር ዩናይትድ በማስፈረም በነዚነዲን ዚዳን ፣ ‘ክስተቱ’ ሮናልዶ ፣ ሉዊስ ፊጎና ራኡል ጎንዛሌዝ መሰል ኮከቦች የተመሰረተውን ቡድናቸውን ይበልጥ ያጠናከሩት ሎስ ብላንኮዎች በየካቲት ወር ላይ ከተከታያቸው ዲፖርቲቮ ላካሩኛ የ12 ነጥብ ብልጫን በመውሰድ የሊጉ አናት ላይ ፊጥ ብለው ነበረና ያለችግር ላሊጋውን መሳም እንደሚችሉ የብዙሃን እምነት ነበር፡፡ 

ግና ከቀሯቸው 12 ጨዋታዎች ስምንቱን ማሸነፍ ለ30ኛ የሊግ ክብራቸው በቂ የነበረላቸው ነጮቹ ከመጨረሻ 8 ጨዋታዎች በሰባቱ ሽንፈትን በማስተናገድ በአሳፋሪ ሁኔታ አሽቆልቁለው ሊጉን በአራተኝነት ለመደምደም ተገደዱ፡፡

ባየርን ሙኒክ (እ.ኤ.አ 2012)


የቅርብ ጊዜ ትዝታ በሆነው ይህ የውድድር ዘመን ሙኒክ እጅግ ያልተጠበቀ ውድቀትን ያስተናገደበት ነበር፡፡ ዋነኛ ተፎካካሪው ከነበረው የየርገን ክሎፕ ስብስብ በ 8 ነጥብ ቀድሞ ይገኝ የነበረው ባየርን በጀርመን ዋንጫ ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ጋር ለፍፃሜ ፣ እንዲሁም ሪያል ማድሪድን በማሸነፍ ከቼልሲ ጋር ለአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ የቀረበ ሲሆን ሶስት ዋንጫዎች ጠራርጎ የማንሳት ቅድመ ግምትን አግኝቶ ነበር፡፡

ነገር ግን በየርገን ክሎፕ የሚመሩት ቢጫ ለባሾቹ ዶርትሙንዶች ቀስ በቀስ ባየርንን በመቅደም የቡንደስ ሊጋ ሻምፒዮን ከመሆናቸውም በላይ በጀርመን ዋንጫ ላይም ታላቁን ሙኒክን 5 ለ 2 በማሸነፍ ከሁለት ዋንጫዎች አደናቀፉት፡፡

ይባስ ብሎም ቡድኑ ከቼልሲ ጋር በነበረው የቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ጨዋታ መሪ ሆኖ እስከመጨረሻዋ ደቂቃ ቢቆይም ዲዲዬ ድሮግባ ባስቆጠራት ግብ አቻ ለመሆን ተገዶ በመለያ ምት ዋንጫውን ለለንደኑ ክለብ አስረከበ፤ ሶስት ዋንጫን ያለመው ክለብም ባዶ እጁን አመቱን አጠናቀቀ፡፡

Advertisements