ሪከርድ / በፔፕ ጓርዲዮላ የሚመሩት ማንችስተር ሲቲዎች አርሰናሎች ይዘውት የነበረውን ሪከርድ ሰበሩ

በዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ እጅግ አስገራሚ አቋም እያሳዩ የሚገኙት እና እስካሁን ድረስ የሚያቆማቸው የጠፋው የፔፕ ጓርዲዮላው ማንችስተር ሲቲዎች አርሰናሎች 2002 ላይ ይዘውት የነበረውን ሪከርድ መስበር ቻሉ።

አሁን እየታየ ያለው የማን ሲቲዎች ጠንካራ ጉዞ ማን ሊያቆም ይችላል?  የሚለው እስከ 17ኛ ሳምንት ድረስ ምላሽ ሳያገኝ ቀጥሏል።

ቡድኑ አጀማመሩ ላይ መጠነኛ መንገጫገጮች ታይተው ለማሸነፍ የተቸገረባቸው ጨዋታዎች የነበሩ ቢሆንም በችግር ውስጥም ቢሆን ሶስት ነጥብ ማሳካት አልከበደውም።

ይኸው የአመቱ ብቸኛ ሁለት ነጥብ የጣለበት አጋጣሚን የተፈጠረው በአመቱ ሁለተኛ ጨዋታ ላይ በሜዳው ኢትሀድ ኤቨርተንን ባስተናገደበት ጨዋታ ነው።

ብዙዎች ሳይጠበቅ ደካማ በሆነው በዘንድሮው ኤቨርተን እንዴት ነጥብ ሊጥል ቻለ? ብለው መጠየቃቸው አይቀርም።

እውነታው ግን ሲቲዎች ይህን ጨዋታ አቻ የወጡት ለ 45 ደቂቃ ዎከር በቀይ ካርድ ወጥቶ በጎዶሎ ተጫዋች ተጫውተው እና ቀድሞም አንድ ጎል ገብቶባቸው እንደነበረ ከታሰበ በዚሁ ጨዋታም መልካም ነጥብ እንዳገኙ መናገር ይቻላል።

ቡድኑ ከኋላው ያሉትን ሁለት ተከታዮቹን ሜዳቸው ድረስ ሄዶ ውድ ሶስት ነጥብ ነጥቋቸው ተመልሷል።ሊጉንም አሁንም በ 11 ነጥብ ተስፈንጥሮ መምራቱን ቀጥሏል።

ማን ሲቲ ባለፈው ሳምንት ባላንጣው ጎረቤቱን ማን ዩናይትድን ሲያሸንፍ አርሰናል 2002 ላይ ይዞት የነበረውን የ 14 ተከታታይ የፕሪምየርሊግ ጨዋታዎች የማሸነፍ ሪከርድ መጋራት ችሎ ነበር።

የ 17ኛው ሳምንት የፕሪምየርሊጉን ጨዋታ በድጋሜ ከሜዳው ውጪ ለመጫወት የተገደዱት ሲቲዎች ምሽት ላይ ወደ ደቡብ ዌልስ አቅንተው ስዋንሲን በማሸነፋቸው በተከታታይ ለ 15ኛ ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል።

ይህም ደሞ ባለፈው ሳምንት ከአርሰናል ጋር ተጋርተውት የነበረውን ሪከርድ በማሻሻል በፕሪምየርሊጉ ታሪክ ለ 15 ጨዋታዎች በተከታታይ በማሸነፍ አዲስ ሪከርድ ማፃፍ ችለዋል።ሪከርዱንም ብቻቸውን ተቆጣጥረውታል።

የምርጥ የግራ እግር ባለቤት የሆነው ዴቪድ ሲልቫ(ሁለት)፣ኬቨን ዴብሩይን እና ኩን አጉዌሮ ያስቆጠሯቸው ጎሎች እንግዳዎቹ የዌልሱን ቡድን 4 ለ 0 አሸንፈው ተመልሰዋል።

ተከታዩ ማን ዩናይትድም ቦርንማውዝን በቀዝቃዛው ኦልድትራፎርድ 1 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል።ጎሉን ለቀያይ ሰይጣኖች ያስቆጠረው በደርቢው ጨዋታ ላይ ጠንካራ ትችት ቀርቦበት የነበረው ሮሜሉ ሉካኩ ነበር።

ዩናይትዶች ከደርቢ ሽንፈታቸው በኋላ ወደ አሸናፊነታቸው ፈጥነው መመለሳቸው መልካም ቢሆንም ጨዋታው ግን ቀሏቸው ነበር ለማለት አያስደፍርም።

ቼልሲዎች እንዲሁ ማክሰኞ ምሽት ኸደርስፊልድን በማሸነፋቸው ወደ አሸናፊነታቸው ተመልሰው ሶስተኛ ደረጃቸውን ሲያስከብሩ ሊቨርፑል እና አርሰናል ግን ምን ነካቸው የሚያስብል ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ።

በተለይ አርሰናል ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ባለመቻሉ ደረጃው ከማሽቆልቆሉ ባለፈ ከመሪው ማን ሲቲ በ 19 ነጥቦች አንሶ ተቀምጧል።

ይህ የነጥብ ልዩነት[19] ደግሞ  ከሊጉ የመጨረሻ ቡድን ከሆነው ስዋንሲ ጋር አርሰናሎች ካላቸው ርቀት [18] ሁሉ የበለጠ መሆኑ መድፈኞቹ ከ 13 አመት በኋላም የፕሪምየርሊጉ ዋንጫ የማንሳት እድላቸው አክትሟል።

ፕሪምየርሊጉ በአዲስ መልክ ከተጀመረ በኋላ ለዋንጫ ተጠግተው እንጂ አንስተው የማያውቁት ሊቨርፑሎችም ዘንድሮም በተስፋ ጀምረው በጊዜ እጃቸውን ሰጥተው እንደ ቀድሞው አመታት በተመሳሳይ ሂደት ውስጥ ተገኝተዋል።

የርገን ክሎፕም ቢሆኑ የሊቨርፑል እስከ 28 አመት የሚገኙ ወጣት ደጋፊዎች ያላዩትን የፕሪምየርሊግ ዋንጫን አሳክተው በክብር መቀመጥ ባለመቻላቸው የአንፊልድ ወንበራቸው እያቃጠላቸው ይገኛል።

ቡድኑ ላይ አሁንም ሊጠቀስ የሚችል ትልቁ በሽታው ወጥ የሆነ አቋም እያሳየ መሄድ አለመቻሉ ነው።


ወቅታዊ የፕሪምየርሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ

1. ማን ሲቲ ..49 ነጥብ

2. ማን ዩናይ..38 ነጥብ

3. ቼልሲ …..35 ነጥብ

4. ቶተንሀም ..31 ነጥብ

5. ሊቨርፑል ..31 ነጥብ

6. በርንሌ ….31 ነጥብ

7. አርሰናል .. 30 ነጥብ [⇡19 ⇣18]

.

.

20. ስዋንሲ ..12 ነጥብ


አሁን የእግርኳስ ወዳጆች ለማን ሲቲ ውዳሴያቸውን አብዝተው እያቀረቡ ይገኛሉ።ቡድኑም በኮከብ ተጫዋቾቹ ታግዞ አዳዲስ ሪከርዶችንም ማስመዝገቡን ቀጥሏል።

የሚገርመው የቡድኑ ተጫዋቾች እየተፈራረቁ ጎልተው ድንቅ ብቃታቸውን እያሳዩ መሄዳቸው ነው።ወጣቱ ሊሮይ ሳኔ በአንድ ሰሞን ትኩረቶች በዝተውበት ነበር፣ዲብሩይን፣ስተርሊንግ .. አሁን ደግሞ ተረኛው ዴቪድ ሲልቫ ሆኗል።

ይህ ጥበበኛ ስፔናዊ ከቫሌንሺያ ከመጣ በኋላ እንደዚህ አመት ስኬታማ አጀማመር አላሳየም።ቀድሞ የተሳኩ ኳሶች ለጎል አመቻችቶ በማቀበል ይታወቅ የነበረው ተጫዋች ዘንድሮ ጎል ደጋግሞ አግቢ ሆኖ ተከስቷል።

እስካሁን ድረስ አምስት ጎሎችን ሲያስቆጥር ስምንት ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

በዘንድሮ የፕሪምየርሊግ ውድድር አምስት እና ከአምስት በላይ ጎሎችን በማስቆጠር እንዲሁም ከአምስት በላይ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችተው ማቀበል የቻሉ ሶስት ተጫዋቾች ናቸው።እነሱም


                     አገባ    ለጎል አቀበለ

ዴቪድ ሲልቫ ..5………….8

ኬቨን ዴብሩይን..5………..8

ሊሮይ ሳኔ …….6………..6            ናቸው።


ሶስቱም የሊጉ መሪ የማን ሲቲ ተጫዋቾች በመሆናቸው ቡድኑ ምን ያህል የጎል አግቢ አማራጮች እና የፈጣሪ ተጫዋቾች ችግር እንደሌለበት መመልከት ይቻላል።

ለዚህ ሁሉ ደግሞ ተጠቃሽ የሚሆነው የቡድኑ አሰልጣኙ ፔፕ ጓርዲዮላ ሲሆን በግሉ በስፔን እና በጀርመን ለረጅም ጨዋታዎች በማሸነፍ የተጓዘበት መንገድ በእንግሊዝም ደግሞታል።

ፔፕ ከባርሴሎና ጋር ለ 16 ተከታታይ ጨዋታዎች፣ከባየርሙኒክ ጋር ለ 19 ተከታታይ ጨዋታዎች እንዲሁም ከሲቲ ጋር ለ 15 ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ በግሉም አዲስ ታሪክ ፅፏል።

Advertisements