ዣን ማርክ ቦስማን- እግር ኳስን በእጅጉ የቀየረው የ”ቦስማን ህግ”

ቦስማንና ሁለቱ ጠበቆቹ

የዝውውር ወቅቶች በተቃረቡ ቁጥር ዘወትር በተደጋጋሚ ወደጆሮ ዘልቆ የሚገባ አንድ ቃል አለ፡፡ የቦስማን ህግ! ታላላቅ ተጫዋቾች ምንም አይነት ክፍያ ሳይፈፀምባቸው ወደፈለጉት ክለብ ተዘዋውረው የመጫወት መብትን ያጎናፀፈው ይህ የቦስማን ህግ እንዲሁ በዋዛ የፀደቀ ሳይሆን የአንድ ግለሰብን እልህ አስጨራሽ ትግል ያስከፈለ ነበር፡፡

ይህ ግለሰብ ዣን ማርክ ቦስማን ይባላል ፤ ቦስማን ቤልጅየማዊ እግር ኳስ ተጫዋች የነበረ ሲሆን በ1990 ከአገሩ ክለብ አር.ኤፍ.ሲ ሊየዥ ጋር የነበረው የውል ስምምነት ጊዜ በመጠናቀቁ ወደፈረንሳይ በማቅናት ለሁለተኛ ዲቪዚዮኑ ክለብ ደንዲርክ እንዲጫወት የሚያስችለው ዳጎስ ያለ ጥያቄ ይቀርብለታል፡፡ ሆኖም ባለቤት ክለቡ ሊየዥ የተጫዋቹ ውል ቢጠናቀቅም ክለቡን ለቆ እንዲሄድ አልፈቀደለትም፡፡

ይህም የሆነው በወቅቱ አንድ ተጫዋች ውሉ ቢጠናቀቅም ክለቡ  በነፃ እንዲሄድ ካልፈቀደለት በስተቀር ገዢ ክለብ ከባለቤት ክለቡ ጋር ተዳራድሮና በገንዘብ ተስማምቶ ተጫዋቹን ለመውሰድ የሚገደድበት አሰራር ስለነበር ነው፡፡

ውሉን ያጠናቀቀውን ቦስማንን ለመልቀቅ አሻፈረኝ ያለው ሊየዥ ይባስ ብሎም ተጫዋቹን ከቀድሞው ዝቅ ያለ የደመወዝ መጠን በማቅረብ ለመሄድ መሻቱን በቅጣት ሊገራው ፈለገ፡፡

በቦስማን ህግ ከሊቨርፑል ወደሪያልማድሪድ ያቀናው ማክማናማን

ይህ ያልተዋጠለት ቦስማን ግን የኋላ ኋላ በስሙ ለመጠራት የበቃውን ህግ ያስፀደቀበትን ክስ መሰረተ፡፡ ከጠበቆቹ ሉክ ሚሰን እና ዣን ሉዊስ ዲፖት ጋር በመጣመር ወደክስ ያመራው ቦስማን የሰራተኞችን ወደፈለጉት ቦታ ሔዶ የመስራት መብት የሚጋፋ በደል ተፈፅሞብኛል ሲል ለአውሮፓ ህብረት ፍርድ ቤት አቤቱታውን ሲያቀርብ ክለቡ ሌየዥን ፣ የቤልጅየም እግር ኳስ ማህበርንና የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበርን ከሰሰ፡፡ 

አምስት አመታትን የፈጀው የሸንጎ ፍርድ ሒደት እልህ አስጨራሽ የነበረ ቢሆንም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ታህሳስ 15 ቀን 1995 ዓ.ም ቦስማን ክሱን በማሸነፍ የታላላቅ የዓለማችን ተጫዋቾችን ህይወት መቀየር የቻለውን ህግ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የዝውውር ህግ አካል እንዲሆን ማስገደድ ቻለ፡፡ በዚህ መሰረትም አንድ ተጫዋች የኮንትራት ስምምነት ጊዜውን እስካጠናቀቀ ድረስ ክለቡን ከፍ ያለ ገንዘብ የሚጠይቅ ውል መጠየቅ እንዲችል ፣ ካልፈለገ ደግሞ ክለቡን ለቆ ወደፈለገበት ቦታ ሄዶ መጫወት የሚችልበትን መብት መጎናፀፍ ቻለ፡፡

የዚህ ህግ መፅደቅ ተጫዋቾች በተሻለ ጥቅም መደራደር የሚችሉበትን እድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ የተጫዋቾች ወኪሎች በዝውውር ላይ መጠነ ሰፊ ተሳትፎን በማድረግ ግዙፍ ሃብትን ማካበት የሚያስችልበትን አሰራር በእግር ኳሱ ዓለም ላይ አስፍኗል፡፡

ከቦስማን ህግ የተጠቀሙ ታላላቅ ተጫዋቾች

እጅግ በርካታ ተጫዋቾች የቦስማን ህግ  ተጠቅመው የተሻለ ጥቅም የሚያገኙበትን ዝውውር የፈፀሙ ሲሆን ታላላቅ የሚባሉትን እንመልከት፡፡ በሉዊ ቫንሃል እየተመራ 1995 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ከፍ ያደረገው በወጣቶች የተገነባው አያክስ አምስተርዳም ተጫዋቾች የነበሩት  ኤድጋርድ ዳቪድስና ፓትሪክ ክላይቨርት ወደኤሲ ሚላን የተዛወሩት በቦስማን ህግ ተጠቅመው በነፃ ዝውውር ነበር፡፡

በተጨማሪም ስቲቭ ማክማናማን በ 1999 ከሊቨርፑል ወደሪያል ማድሪድ ያደረገው ዝውውር ተጠቃሽ ሲሆን ብራያን ላውድሩፕ እንዲሁ ከሬንጀርስ ወደቼልሲ ያደረገው ዝውውርም የዚሁ ህግ ተግባራዊነት መገለጫ ነበር፡፡

ሚሸል ባላክ – የቦስማንን ህግ በመጠቀም ከሙኒክ ወደቼልሲ ተዘዋውሮ ነበር

በአነጋጋሪነቱ ዘወትር የሚወሳው የእንግሊዛዊው ሶል ካምፕቤል ከቶተንሐም ሆትስፐር ወደመሪር ተቀናቃኙ አርሰናል ያደረገው ዝውውርም በቦስማን ህግ መሰረት የተከወነ ሲሆን ከቅርብ ጊዜያት ዝውውሮች ውስጥም ሮበርት ሌዋንዶውስኪ ከዶርትሙንድ ወደባየርን ሙኒክ ፣ አንድሬያ ፒርሎ ከኤሲ ሚላን ወደጁቬንቱስ ፣ ሚሸል ባላክ ከባየርን ሙኒክ ወደቼልሲ እንዲሁም ዝላታን ኢብራሒሞቪች ከፓሪስ ሴንት ጀርሜይን ወደማንችስተር ዩናይትድ ያደረገው ዝውውርም ህጉ ተግባራዊ የሆነበት ነበር፡፡
ከቀናት በኋላ የሚገፈተው የጥሩ የዝውውር መስኮት ለበርካታ ታላላቅ ተጫዋቾች የኮንትራት ጊዜ መጠናቀቅ መቃረብን ማብሰሪያ ሲሆን ክለቦችም ከወዲሁ ተጫዋቾቻቸውን በተሻለ ጥቅም በማሰር ላይ ታች የሚሉበት ፣ አልያም በነፃ ዝውውር የሌላ ክለብ ተጫዋቾችን የግላቸው ለማድረግ ቅድመ ድርድር የሚጀምሩበት ጊዜ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

Advertisements