የዋንጫ ፉክክሩ አብቅቶለት ቢሆን ኖሮ ብራዚል ነበርኩ – ሞሪንሆ

የማንችስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ ምንም እንኳ ቡድናቸው የፕሪሚየር ሊጉን ክብረወሰኖች በመሰባበር ላይ የሚገኘውን የማንችስተር ሲቲ ጭራ ለመያዝ ጥረት እያደረገ ቢገኝም አሁንም ድረስ ግን የፕሪሚየር ሊጉ የዋንጫ ፉክክር ገና ህያው እንደሆነ ገልፀዋል።

ትናንት (ረቡዕ) ምሽት ማንችስተር ዩናይትድ ቦርንማውዝን 1ለ0 በሆነ ብቸኛ ግብ ሲረታ፣ የፔል ጋርዲዮላው ቡድን ግን ስዋንሲ ሲቲን 4ለ0 በሆነ ውጤት በመርታት ተከታታይ 15 የሊግ ጨዋታዎችን በማሸነፍና አዲስ ክብረወሰን በማስመዘገብ የሊጉን የደጃ ሰንጠረዥ በቀዳሚነት መምራቱን ቀጥሏል።

ዩናይትድ ካለፈው የሳምንቱ መጨረሻ ቀን የደርቢ ሽንፈቱ በኋላ ቼሪዎቹን ለመርታት የሮሜሉ ሉካኩ ግብ ብቻዋን በቂ ነበረች። ይሁን እንጂ ከጨዋታው በኋላም ሞሪንሆ ተጫዋቾቻቸው የድካም ምልክት እንደነረባቸው አምነዋል።

ሆኖም ሞሪንሆ ዌስት ብሮምንና ሌስተር ሲቲን በሚገጥሙባቸው ቀጣይ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎቻቸው ከጋርዲዮላው ቡድን ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት የማጥበብ ተነሳስሽነት እንዳላቸው አስረግጠው ገልፀዋል።

ስለዋንጫ ፉክክሩ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄም “በጨዋታ ላይ ጨዋታ እያደረግን ነው። በቀጣዩ ጨዋታም ለማሸነፍ እንጥራለን። በዌስትብሮም አስቸጋሪ ነገር ገጥሞን ነበር። በየጨታዎቺ ላይ ግን ለማሸነፍ ጥረት እናደርጋለን።

“ጨዋታው የሚያበቃው ገና ግንቦት ነው። አሁን አልቆ ቢሆን ኖሮ ግን ለመዝናናት ወደብራዚል ወይም ወደሎሳንጀለስ እሄድ ነበር።” ሲሉ ፖርቱጋላዊው አሰልጣኝ መልሰዋል።

ቡድናቸው በማንችስተር ሲቲ 2ለ1 ከተሸነፈበት የዞረ ድምር አሁንም ስለመውጣት አለመውጣቱ ለቀረበማቸው ጥያቄም ሞሪንሆ “ድካም አዎ። ነገር ግን የዞረ ድምር አይደለም። 

“ጨዋታው ትልቅ ነበር። ሽንፈት ለማገገም አይረዳህም። ድል ግን ይረዳል።

“እነሱ [ቦርንማውዞች] አስቸጋሪ ተጋጣሚዎች እና አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነበሩ። ሁለተኛውን ግብ ብናስቆጥር ኖሮ ምሽቱ የተረጋጋ ይሆንልን ነበር።” በማለትም ምላሽ ሰጥተዋል።

ማንችስተር ዩናይትድ በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከመሪው ማንችስተር ሲቲ በ11 ነጥቦች ዝቅ ብሎ በ38 ነጥቦች በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

Advertisements