ቡጢ / የኢትዮጵያ ቦክስ ፌደሬሽን የ 2010 አንደኛ ዙር ሀገር አቀፍ የክለቦች ውድድር ፍፃሜውን አገኘ

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌደሬሽን ያዘጋጀውና ካሳለፍነው ረቡዕ አንስቶ ለሶስት ቀናት የቆየው የ 2010 አንደኛ ዙር ሀገር አቀፍ የክለቦች ሻምፒዮና በትናንትናው ዕለት ፍፃሜውን አግኝቷል።

በትንሿ ስታዲየም ሲካሄድ በቆየው የዙር ውድድር አምስት ክለቦች በሁለቱም ፆታዎች ከ 48 ኪ.ግ አንስቶ እስከ 91 ኪ.ግ በአስር የተለያዩ ዘርፎች ብዙ ታዳሚ በተገኙበት በድምቀት ውድድራቸውን አካሂደዋል።

በአጠቃላይ ውጤትም ፌደራል ፓሊስ ብዙ ሜዳሊያ በማግኘት በወንዶች ዘርፍ በቀዳሚነት ጨርሶ የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን በሴቶች ዘርፍ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የዋንጫ አሸናፊ መሆን ችሏል።

በፍፃሜው ውድድር ከባድ የብቃት ልዩነት በታየበት የ 81 ኪ.ግ እና 91 ኪ.ግ ፍልሚያ የድሬ ከነማው መንግስተክርስቶስ እፁብና የፌደራል ፓሊሱ ሙሉቀን መልኬ ተፎካካሪዎቻቸውን በዝረራ በመርታት ከባድ ተወዳዳሪ መሆናቸውን አስመስክረዋል። 

በሌላ በኩል በክለብ ደረጃ በወንዶች የድሬድዋ ከነማ በሴቶች ደግሞ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ተወዳዳሪዎች ትልቅ ብቃት በማሳየት በተመልካቹ ዘንድ አድናቆትን አግኝተዋል።

በውድድሩ ፍፃሜም ከአንድ እስከ ሶስት ለጨረሱ ተወዳዳሪዎች ከተደረገው የሜዳሊያ እና ለአሸናፊዎች ክለቦች ከተሰጠው የዋንጫ ሽልማት በተጨማሪ በውድድሩ ላይ ለተሳተፉ ክለቦች እያንዳንዳቸው የ 2,500 ብር የመወዳዳሪያ ጫማዎች፣ 10 የጥርስ መከላከያዎች እና ሰርተፍኬት ከፌደሬሽኑ በማበረታቻ መልክ ተበርክቶላቸዋል።

ከዙር ውድድሩ እና ከሽልማት አሰጣጥ ስነስርዓቱ በኋላም ከኢትዮአዲስ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፌደሬሽኑ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፓውሎስ ማንዳ ውድድሩ የመጀመሪያ ዙር እንደመሆኑ እና ተወዳዳሪዎች ከእረፍት በመምጣታቸው ከዚህ ቀደም በነበሩት ጊዜያት የነበረውን አይነት ጠንካራ ፉክክር ሊታይበት እንዳልቻለ ተናግረዋል።

ነገርግን ውድድሩ ለ 2010 ገና ጅምር በመሆኑ በቀጣይ ጥሩ ነገር እንደሚታይ ያላቸውን ተስፋ ገልፀው ጥሩ ዝግጅት አድርገው የመጡት የድሬድዋ ከነማና አካዳሚ ስፖርተኞች ጥሩ ብቃት ማሳየታቸውንና የፌደራል ፖሊስም በውድድሩ ላይ ጥሩ ብቃት ማስመዝገቡን አውስተዋል።

በሌላ በኩል በውድድሩ ላይ የታየውን የበዛ የብቃት ልዩነት በተመለከተም ፌደሬሽኑ ወደ ክለቦቹ በመሄድ ቅኝት በሚያደርግበት ወቅት ሁኔታውን ለክለቦቹ ከማሳወቅ ውጪ የመጡትን ተወዳዳሪዎች በቀጥታ ከማወዳደር ውጪ ልዩነቱን ለማጣጣም ምንም የሚሰራው ስራ እንደሌለ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ውድድሮቹ ቀትር ላይ በሚደረጉበት ወቅት በትንሿ ስታዲየም ያለው ፀሀያማ አየር የቦክስ ተወዳዳሪዎች ፀሀያማ አየር የማይመቻቸውና ቶሎ አፍንጫቸውን ለመድማት የሚያጋልጥ ከመሆኑ ጋር በተያያዘም ሲደሙና በህክምና ውሳኔ ሲሸነፉ ታይተዋል።

ከዚህ ሁኔታ ጋር በተያያዘም ጥያቄ የቀረበላቸው የፅህፈት ቤት ሀላፊው ከዚህ ቀደም ለውድድር ይጠቀሙበት የነበረው የወጣቶች አካዳሚው መወዳደሪያ ስፍራ ሌላ ውድድር እያስተናገደ በመሆኑ የሜዳ እጥረት መፈጠሩ እንዲሁም ደግሞ ትንሿ ስታዲየም የተለያዩ ፌደሬሽኖችን ውድድር የሚያስተናግድ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የውድድር መደራረብ ያለው መሆኑ መሆኑ ለውድድሩ በሞቃት ሰአት መደረግ እንደ ምክንያት አንስተው ምላሽ ሰጥተዋል።

ይህ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የቦክስ የዙር ሻምፒዮና በ 2010 ፌደሬሽኑ ከሚያዘጋጀው አራት የዙር ውድድር ቀዳሚው ሲሆን በቀጣይ በወራቶች ልዩነት ቀሪ ሶስት የዙር ፍልሚያዎች የሚካሄዱ ይሆናል።

Advertisements