ሴካፋ 2017/ ኬንያ ዛንዚባርን በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆነች

በኬንያ አስተናጋጅነት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ሲደረግ የነበረው የ2017 የሴካፋ ውድድር በአዘጋጇ ኬንያ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።

“ሀራምቤ ስታርስ”እየተባሉ የሚጠሩት የኬንያ ብሔራዊ ቡድን ብሩንዲን በማሸነፍ ዛንዚባር ደግሞ ውድድሩን በተደጋጋሚ ጊዜ በማሸነፍ የምትታወቀዋን ዩጋንዳን በማሸነፍ ለፍፃሜ ተገናኝተዋል።

አዘጋጆቹ ጨዋታውን ማሸነፍ የሚችሉ ከሆኑ 6 ሚሊየን ሽልንግ እንደሚሰጣቸው የሀገሪቷ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የሆኑት ኒክ ምዌንዳ አሳውቀው ተጫዋቾቹ እንዲነቃቁ አድርገዋል።

ኬንያ እና ዛንዚባር በማቻኮስ ኬኒያታ ስታድየም ባለፈው ሳምንት በምድብ ጨዋታ ላይ ተገናኝተው አቻ ተለያይተው የነበረ ሲሆን አሸናፊው የግድ መለየት በነበረበት የዛሬው የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ግን በባለሜዳዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀራምቤ ስታርሶቹ እስከ 87ኛ ደቂቃ ድረስ ባስቆጠሩት ግብ መምራት ችለው የነበረ ቢሆንም ዛንዚባሮች ዘግይተው ባስቆጠሩት ጎል ጨዋታውን 1-1 በማጠናቀቅ ወደ ጭማሪ ሰአት አቅንተዋል።

የማሱድ ጁማ የ98ኛ ደቂቃ ጎል ባለሜዳዎቹ በድጋሚ መሪ እንዲሆኑ ያገዘ ቢሆንም ብዙም ሳይቆዩ ማካሜ በድጋሜ ያስቆጠራት ጎል ጨዋታው 2-2 ሊጠናቀቅ ችሏል።

ወደ መለያ ምት ያቀናው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ግብ ጠባቂው ፓትሪክ ማታሲ ሶስት ኳሶችን በመመለስ ሀራምቤ ስታርሶቹ 3-2 በማሸነፍ ለሰባተኛ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ እንዲሆኑ አድርጓል።

ለቡድኑ አዲሱ አሰልጣኝ ፖል ፑትም ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ብዙም ሳይቆዩ በመጀመሪያ ሙከራቸው የሴካፋን ዋንጫን ማሸነፍ ችለዋል።

ከዛሬ የፍፃሜ ጨዋታ በፊት የሶስተኛ ደረጃን ለማግኘት በተደረገው ጨዋታ ዩጋንዳ ከኋላ በመነሳት ብሩንዲን 2-1 ማሸነፍ ችላለች።

Advertisements