ዌስትብሮም ግብፃዊው አህመድ ሄጋዚን በቋሚነት ማስፈረሙን አሳወቀ


​የፕሪምየርሊጉ ተሳታፊ ዌስትብሮሚች አልቢዮን ከአል አህሊ በውሰት አምጥቶ ሲጠቀምበት የነበረውን ግብፃዊው ተጫዋች አህመድ ሄጋዚን በቋሚነት መስፈረሙን አሳወቀ።

የ አህሊው ተከላካይ ከባለፈው ሀምሌ ወር ጀምሮ በዌስት ብሮም በውሰት ሲጫወት ከቆየ በኋላ በነበረው መልካም ቆይታ ክለቡ የውሰት ውሉን ወደ ቋሚነት ቀይሮታል።

የእንግሊዙ ክለብ ተጫዋቹን ከ አህሊ በውሰት ሲወስድ ወደ ቋሚነት የመቀየር አማራጭን በስምምነቱ ላይ አካቶ የነበረ ሲሆን አሁን የቋሚ ዝውውሩን አማራጭ ተጠቅሞ የውል ማፍረሻውን ከፍሎ የግሉ አድርጎታል።

ሄጋዚን የቀድሞ የክለቡ አሰልጣኝ ቶኒ ፑሊስ ቢያመጡትም አለን ፓርዲው ክለቡን ከያዙ በኋላ ተጫዋቹን በመውደዳቸው ዝውውሩ ወደ ቋሚነት እንዲቀየር ትልቅ ሚና መጫወታቸው ታውቋል።

ፓርዲው ለክለቡ ድረገፅ “ይህ ለክለቡ ትልቅ ዜና ነው።እኔ ወደ ክለቡ ከመጣው በኋላ እሱ ለኔ አስደናቂ ነው።እርግጠኛ ነኝ ለወደፊቱም ከሱ ብዙ ነገር እንመለከታለን።

“ክለቡ ለወደፊት በነሱ ላይ ሊገነባበት ከሚያስባቸው ተጫዋቾች አንዱ ነው። ወደፊትም ትልቅ ሚና የሚጫወት በመሆኑ በክለቡ እና በተጫዋቹ መካከል የነበረውን ግኑኝነት ወደ ቋሚነት በመለወጡ ለሁለቱም ጥሩ ነገር ነው።ደጋፊዎቹን የሚፈልጉት ነገር መሆኑን እርግጠኛ ነኝ።”ሲሉ ተናግረዋል።

ተጫዋቹ ለ አራት አመት ከግማሽ በመፈረም እስከ 2022 ድረስ ከዌስትብሮም ጋር የሚቆይ ሲሆን በአዲሱ ስምምነቱም ደስተኛ መሆኑን አሳውቋል።

“በክለቡ እና በዚህ የቡድን ስብስብ አባል በመሆኔ ደስተኛ ነኝ።አሁን እያስመዘገብን ያለነው ውጤት የምንፈልገው ውጤት እንዳልሆነ አውቃለው ነገርግን እዚህ ትልቅ መነቃቃት በመኖሩ ብዙም ሳይርቅ የምንፈልገውን ውጤት እንደምናስመዘግብ አስባለው።”ሲል ሀሳቡን ሰጥቷል።

ሄጋዚ ወደ ዌስትብሮም ካቀና በኋላ በመጀመሪያው የፕሪምየርሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ላይ በመጀመሪያው ጨዋታ ቦርንማውዝ ላይ ጎል ማስቆጠሩ ይታወሳል።

Advertisements