የማሩዋን ፌላኒ የጉዳት ምስጢር

ማንችስተር ዩናይትድ ማሩዋን ፌላኒን ከጨዋታ የራቀውን የጉልበት ህመም ጉዳት ሚስጥር ምን እንደሆነ ለማወቅ ተቸግሮ እንደሚገኝ ኢኤስፒኤን ዘግቧል።

አማካኙ በመስከረም ወር መጨረሻ ቤልጂየም ቦስኒያን በገጠመችበት ጨዋታ የጉልበት ስር መሳሳብ ህመም ገጥሞት ነበር። ስድስት ጨዋታዎች ካመለጡት በኋላም በህዳር ወር ወደሜዳ ተመልሶ ለዩናይትድ በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ እና ህዳር 12 ባሰልን በሻምፒዮንስ ሊግ 1ለ0 መርታት በቻሉበት ጨዋታ 90 ደቂቃዎችን ተሠልፎ ተጫውቷል። ነገር ግን የ30 ዓመቱ ተጫዋች ህዳር 25 በኦልትራፎርድ ከብራይተን ጋር በተደረገው ጨዋታ ማብቂያ ላይ ተቀይሮ በመግባት ከተጫወተ በኋላ ዳግም ወደሜዳ ተመልሶ አልተጫወተም።

ሆዜ ሞሪንሆ ፌላኒ በማንችስተር ደርቢ ጨዋታ ላይ ተመልሶ እንደሚጫወት ተስፋ አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን ቤልጂየማዊው ተጫዋች ጨዋታው ከመጀመሩ 24 ሰዓታት ቀድም ብሎ በመጨረሻው የልምምድ ወቅት በጉልበቱ ላይ የህመም ስሜት እንዳለበትና በጨዋታው ላይ እንደማይሰለፍ ተገልፅዋል።

የህመሙን የችግር ምንጭ ለማግኘት ተጨማሪ የህክምና ምርመራዎችም ተደርገውለታል። ሆኖም እስካሁን ድረስ የጉዳቱ ሚስጥር ሊታወቅ አልቻለም። ይህም ሞሪንሆና የዩናይትድ የህክምና ቡድን አባላት ተጫዋቹ ወደሜዳ የሚመለስበትን ጊዜ አስቀድመው እንዲያስቀምጡ ማድረግ አላስቻላቸውም።

ይህም በእንዲህ እንዳለም ዩናይትድ አሁንም ደረስ ፌላኒን አዲስ ኮንትራት ሊያስፈርመው እንደሚችል ተስፋ አለው። የተጫዋቹ ከክለቡ ጋር ያለው ወቅታዊ ኮንትራት በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ይጠናቀቃል። እናም ጥር 1 ደርሶ ተጫዋቹ በሌሎች ክለቦች አይን ውስጥ ከመግባቱ በፊት በሃሳብ ደረጃ ከተጫዋቹ ጋር ቅድመ ኮንትራት ድርድር ሊያደርግ ይችላል። 

ዩናይትድ ምንም እንኳ የቀድሞውን የኤቨርተን ተጫዋች በክረምቱ በነፃ ሊያጣው ቢችልም እንኳ በጥር ወር የዝውውር መስኮት ወቅት የመሸጥ ፍላጎት የለውም። 

ከቱርክ፣ ጣሊያንና እና ቻይና ክለቦች ጋር ስሙ የተቆራኘው ፌላኒ በመስከረም ወር ከዩናይትድ የቀረበለትን አዲስ የኮንታራት ጥያቄ ውድቅ አድርጓል። በመሆኑም ኢኤስፒኤን የውስጥ ምንጮቼ ገለፁልኝ ብሎ እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ ተጫዋቹ አሁን በጠረጴዛ ላይ ከቀረበለትም በላይ ዘለግ ያለ ስምምነት ይፈልጋል።

Advertisements