“እኔ የችግሮቻችን ሁሉ ትንሹ ችግር ነኝ” – ጋቱሶ

የኤሲ ሚላኑ አሰልጣኝ ጄናሮ ጋቱሶ ክለቡ በሜዳው በአታላንታ የ2ለ0 ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ የእሱ የክለቡ ችግር መሆን ከክለቡ ችግሮች ሁሉ ትንሹ ችግር እንደሆነ በመግለፅ ክለቡን ሊለቅ እንደሆነ የሚሰጠውን አስተያየት አስተባብሏል።

ጋቱሶ የኤሲ ሚላን አሰልጣኝ ሆኖ የተሾመው ባለፈው ወር ክለቡን የተሰናበቱትን ቪንቼንዞ ሞንቴላን ተክቶ የነበረ ቢሆንም በሊጉ ክለቡን በአሰልጣኝነት መምራት ከቻለባቸው አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ቦሎኛን 2ለ1 በረታበት አንድ ጨዋታ ብቻ ነው።

ሮሶኔሪዎቹ ባለፈው ሳምንት በአስገራሚ ሁኔታ ድል በራቀው ክለብ ቬሮና 3ለ0 በሆነ ውጤት ተሸንፈዋል። ቅዳሜም በአታላንታ ዳግም የ2ለ0 ሽንፋት ገጥሟቸዋል።

ይሁን እንጂ ጋቱሶ ከወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ክለቡን ለቆ መሄድ መፍትሄ እንደማይሆን ለሚዲያ ሴት ፕሪሚየም ተናግሯል።

“ምንም እንኳ አጀማመራችን ጥሩ የነበረ ቢሆንም ብዙ ነገሮች ግን አልሰሩም። አንድ ጊዜ ወደኋላ ከተንሸራተትክ ደግሞ ትግሉ የዳገት ያህል የከበደ ይሆንብሃል።” በማለት ተናግሯል።

“ሁኔታው የተወሳሰበ ነው። ደጋፊው ተቃውሞ ላይ ነው። እኛም የውድድር ዘመኑን በዚህ መንገድ እንቀጥላለን ብለን ማሰብ አንችልም። ነገር ግን ሰዎቹ ወደኋላ አፈግፍገው የሚችሉትን ነገር ሳያደርጉ መቅረታቸውን አልተመለከትኩም። የተቻላቸውን ሁሉ ሲያደረጉ ተመልክቻለሁ። ሆኖም ቶሎ የምንፍረከረክ ሆነናል።

“እኔ ዛሬ የሚላን አሰልጣኝ ነኝ። ነገር ግን የችግሮቻችን ሁሉ ትንሹ ችግር ነኝ። ጉዳዩ ያለንበት የአቋም ድረጃ አይደለም። ችግሩ የስነልቡና ጉዳይ ነው። የምናደርገው ነገር በቂ ካልሆነ ደግሞ እንደቡድን የምንሰራቸውን ስህተቶች አነስተኛ ለማድረግ የግድ አንድ መሆን ይኖርብናል። 

“የክለቡ ችግር እኔ ነኝ ብዬ የማስብ ቢሆን ኖሮ በፍጥነት ክለቡን እለቅ ነበር። ተጫዋቾቹ ከበስተጀርባዬ ባይኖሩ ኖሮም እለቅ ነበር። ነገር ግን ሁኔታው እንደዚያ አይደለም።” በማለት የቀድሞው የክለቡ ታሪካዊ ተጫዋች ጋቱሶ ገልፅዋል።

ጋቱሶ በኤሲ ሚላን የተጫዋችነት ዘመኑ የሴሪ አውን እና የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫዎች ለሁለት ጊዜያት ያህል ማንሳት የቻለ ቢሆንም፣ የቀድሞው የጣሊያን ብሄራዊ ቡድን አማካኝ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ከክለቡ ጋር የነበረው ትውስታ አሁን ላለው የቡድን ስብስብ የፈየደው ነገር የለም።

“ቁርጠኝነት፣ ረሃብ እና ብርታት ጎሎናል።” በማለት ጋቱሶ ተናግሮ፣ አክሎም “ካለፈው ጊዜ ጋር የምናደርገውን ንፅፅር ማቆም እንዳለብንም አስባለሁ። አሁን ያለው የተለዩ ተጫዋቾች እና የተለየ ክለብ ነው።” ሲል ገልፅዋል።

Advertisements