ማን ሲቲዎች በውድድር አመቱ ሊያሻሽሏቸው የሚችሏቸው 12 ሪከርዶች

የፕሪምየርሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በተረጋጋ መልኩ ከአናት ተቀምጠው እየመሩ የሚገኙት ማንችስተር ሲቲዎች ይህን አስደናቂ አቋማቸውን ይዘው መቀጠል የሚችሉ ከሆነ  12 ሪከርዶች ሊሰብሩ ይችላሉ።

በፔፕ ጓርዲዮላ አሰልጣኝነት የሚመሩት ማንችስተር ሲቲዎች በዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ አስደናቂ አቋም ማሳየታቸውን ቀጥለዋል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ብዛት ያላቸውን ተጫዋቾች ለቆ በምትካቸው ሌሎች ተጫዋቾችን ማዘዋወር የቻሉት ሲቲዎች ቡድናቸውን ለማዋሀድ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ቢነገርም ግምቶችን ወደ ኋላ አስቀርቶ በአስገራሚ እንቅስቃሴ ከተፎካካሪዎቹ ተለይቶ ሊጉን እየመራ ይገኛል።

ሊጉ ከተጀመረ ባለፈው ነሀሴ በኋላ አንድ ጨዋታ ብቻ በአቻ ውጤት ከመለያየታቸው ባሻገር ቀሪዎቹን 18 ጨዋታዎች ማሸነፍ ችለዋል።

ብቸኛ ነጥብ የጣሉበት ጨዋታም ኤቨርተንን በሜዳቸው ያስተናገዱበት ጨዋታ ሲሆን በእለቱም ከ 45 ደቂቃ በላይ አንድ ተጫዋች በቀይ ወጥቶባቸው ከኋላ በመነሳት ጎል አስቆጥረው አቻ መውጣት የቻሉበት እንደነበር ይታወሳል።

ሲቲዎች የዘንድሮው ውጤታማ ጉዟቸው አዳዲስ ሪከርዶችን እንዲያሻሽሉ እየረዳቸው ይገኛል።ከወዲሁ በ 17 ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ አዲስ ሪከርድ ያስመዘገቡ ሲሆን ይህን አቋማቸውን ማስቀጠል ከቻሉ ደግሞ ከፊታቸው ሌሎች 12 ሪከርዶች ይጠብቃቸዋል።ለመሆኑ እነዚህ ሪከርዶች እነማን ናቸው?


1) በአንድ የውድድር አመት ብዙ ነጥብ ማስመዝገብ

ይህን ሪከርድ የያዘው ቼልሲ ሲሆን ወቅቱም በ 2004/2005 ነበር።በወቅቱ ቼልሲዎች ሰብስበውት የነበሩት ነጥብ 95 ነበር።ሲቲዎች ከ 19 ጨዋታዎች በኋላ መሰብሰብ የቻሉት 55 ነጥብ ሲሆን በቀሪዎቹ 19 ጨዋታዎች ከ 40 ነጥብ በላይ ተጨማሪ መሰብሰብ ከቻሉ ሪከርዱን የግላቸው ማድረግ ይችላሉ።


2) በውድድር አመቱ ዝቅተኛ ሽንፈት

የዚህ ሪከርድ ባለቤት 2003/2004 ላይ ሽንፈት ሳይቀምስ ዋንጫ ማንሳት የቻለው አርሰናል ነው።”የማይነኩት” ተብለው የነበሩት መድፈኞቹ የሰሩትን ታሪክ ሲቲዎች ለመድገም ከባድ ፈተና ቢሆንባቸውም አስካሁን ግን በ19 ጨዋታዎች  ያለሽንፈት ተጉዘዋል።


3) በውድድር አመቱ ብዙ ጊዜ ያሸነፈ

2016/2017 ላይ አሸናፊ የነበሩት ቼልሲዎች በአንቶኒዮ ኮንቴ እየተመሩ በ 30 የፕሪምየርሊጉ ጨዋታዎች ላይ በማሸነፍ ሪከርድ ይዘዋል።ሲቲዎች ከወዲሁ 18 ጨዋታዎች ያሸነፉ ሲሆን ይህን የቼልሲ ሪከርድ ለማሻሻል ከቀሪዎቹ 19 ጨዋታዎች ውስጥ ከ 12 በላይ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ይገባቸዋል።


4) በአንድ የውድድር አመት ብዙ የጎል ልዩነት ማስመዝገብ

ይህንንም በሪከርድነት የያዘው ቼልሲ ሲሆን ወቅቱ 2009/2010 ነበር።የለንደኑ ቡድን በወቅቱ + 71 የጎል ልዩነቶችን ይዞ ማጠናቀቅ ችሎ እንደነበር ይታወሳል።ይህን ሪከርድ ለመስበር አንድ ቡድን ብዙ ጎሎችን ማስቆጠር እንዲሁም ጥቂት ጎሎችን ማስተናገድ ይጠበቅበታል።

ከወዲሁ 48 ንፁህ ጎሎችን መሰብሰብ የቻሉት ሲቲዎች በሰፊ ጎል ማሸነፋቸው የሚቀጥሉ ከሆነ ይህን ሪከርድ ያሻሽላሉ ተብሎ ይጠበቃል።


5) በውድድር አመቱ ከሜዳ ውጪ ብዙ ጊዜ ማሸነፍ

ከሜዳ ውጪ ማሸነፍ ከባድ ፈተና የሆነበት የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ ሲቲዎች ያገኟቸውን ቡድኖች በሙሉ በሜዳቸው አሳፍረዋቸው ተመልሰዋል።

 የቅርብ ተፎካካሪያቸው የሆኑት ዩናይትድ እና ቼልሲ በሜዳቸው በፔፕ ጓርዲዮላ የተደቆሱ ቡድኖች ውስጥ መካተታቸው ሲታይ ሲቲዎች ቼልሲዎች በ 2004/2005 ላይ 15 ከሜዳቸው ውጪ ድል የተቀዳጁበት የሪከርድ አመት ለመድገም ቀጣይ 7 ከሜዳቸው ውጪ ጨዋታዎችን ብቻ ማሸነፍ በቂያቸው ነው።


6) ብዙ ጎል በውድድር አመቱ ማስቆጠር

የብዙ ሪከርዶች ባለቤት የሆነው ቼልሲ 2009/2010 ላይ 103 ጎሎችን በተጋጣሚው መረብ ላይ በማሳረፍ ሪከርድ ይዘዋል።ይኸው ሪከርዳቸው ለመስበር ሲቲዎች ምን ያህል እንደሚሳካላቸው ባይታወቅም ከወዲሁ ግን 60 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል። 


7) በጥቂት ጨዋታዎች አቻ የወጣ

የዚህም ሪከርድ ባለቤት ቼልሲ ሲሆን ሰመያዊዎቹ በ 1997/1998 በ 3 ጨዋታዎች ብቻ አቻ በመውጣት የውድድር አመቱን አጠናቀው ነበር።እስካሁን አንድ ጊዜ ብቻ አቻ የወጡት ሲቲዎች ይህን ሪከርድ ያሻሽሉ ይሆን?


8) ከሜዳ ውጪ በጥቂት ጨዋታዎች አቻ የወጣ

ከሜዳ ውጪ አንድ ጊዜ ብቻ አቻ በመውጣት በሪከርድነት የተጋሩት 12 ቡድኖች ናቸው።ሲቲዎችም እስካሁን ከሜዳቸው ውጪ ሙሉ ነጥብ ከማስመዝገብ ውጪ አቻ አልወጡም።


9) ከሜዳ ውጪ በተከታታይ ማሸነፍ

በ 17 ተከታታይ ጨዋታዎች[በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ] ያሸነፉት ሲቲዎች ከሜዳቸው ውጪ በተከታታይ ያሸነፉት በ 9 ጨዋታዎች ነው።ይህ ደግሞ ቼልሲ 2008 ላይ ይዞት የነበረውን ሪከርድ ለመስበር በ 3 ቀጣይ ተከታታይ ከሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ማሸነፍ በቂያቸው ነው።


10) በሜዳቸው ጥቂት ጊዜ የተሸነፉ

ብዙዎቹ በሜዳቸው ጠንካራ በመሆናቸው በአመቱ በሜዳቸው የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ጥቂት ጊዜ ብቻ ሲሸነፉ ይታያሉ።በፕሪምየርሊጉ ታሪክ ግን ስድስት ቡድኖች በሜዳቸው ሽንፈት ሳይገጥማቸው ማጠናቀቅ ችለዋል።እስካሁን በሜዳቸው ያልተሸነፉት ሲቲዎችስ ከነዚህ ቡድኖች ጋር ሪከርዱን ለመጋራት አመቱን በሜዳቸው ከሽንፈት ነፃ መሆን ይጠበቅባቸዋል።


11) ከሜዳ ውጪ ብዙ ጎል ማስቆጠር

2013/2014 ላይ ሊቨርፑሎች ከሜዳቸው ውጪ ጎል ማስቆጠር ቀሏቸው ነበር።ቡድኑ 48 ጎሎችን በማስቆጠር ባለ ሪከርድ ነው።ሲቲዎችም እስካሁን 24 ጎሎችን ከሜዳቸው ውጪ አስቆጥረዋል።


12) በጊዜ የፕሪምየርሊጉን ዋንጫ አሸናፊነትን ማረጋገጥ

2000/2001 ላይ የነበረው የሰር አሌክስ ፈርጉሰኑ ማንችስተር ዩናይትድ የሊጉ አሸናፊ መሆኑን ያወጀው 5 ጨዋታዎች ሲቀሩ ነበር።ይህ የቀያይ ሰይጣኖቹ ሪከርድ በጎረቤታቸው ማን ሲቲ ሊሰበር የሚችል የሚመስል ሌላው ሪከርድ ሆኗል።

የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ የውድድሩ አጋማሽ ላይ በመሆኑ በቀጣይ የሚደረጉ 19 ጨዋታዎች ላለመውረድ ከሚደረጉ ብርቱ ፉክክሮች ጨምሮ እያንዳንዱ ጨዋታዎች ማሸነፍ ከባድ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

የፔፕ ጓርዲዮላው ቡድንም በመጀመሪያው ዙር ያሳየው ለፍፁምነት የቀረበው ውጤታማ ጉዞ በቀሪዎቹ ጨዋታዎች ማስቀጠል መቻሉ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ከላይ የተጠቀሱትን ሪከርዶች የሚያሻሽሏቸው እንደማይጠፉ ግን መገመት ይቸላል።የትኞቹ ሪከርዶች?  የሚለውን ለመመለስ ግን የውድድር አመቱ መጠናቅ መጠበቅ የተሻለ ይሆናል።

Advertisements