ፔፕ ጋርዲዮላ ማንችስተር ሲቲ የድካም ችግር እንደሌለበት ገለፁ

የማንችስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ክለባቸው እያሳየ የሚገኘውን ከፍተኛ ብቃት እንዳይቀጥበት በስራ ብዛት የሚመጣ ድካም አሳሳቢ ጉዳይ ሊሆንባቸው እንደሚችል የሚሰጠውን አስተየያት ውድቅ አድርገዋል።

ሲቲ ከ19 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎቹ 18 ጨዋታ በማሸነፍ እና 60 ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ በ13 ነጥቦች ብልጫ ፕሪሚየር ሊጉን በቀዳሚነት በመምራት ላይ ይገኛል። 

ነገር ግን  ክለቡ በዚህ የውድድር ዘመን እያሳየ የሚገኘው ከፍተኛ ጉልበት እና ተጭኖ የማጥቃት ብቃቱ በተለይም በተጣበቡት የገና በዓል ሰሞን ጨዋታዎች በጋርዲዮላው ቡድን ላይ እንዳች ችግር ሊሆኑበት እንደሚችሉ እየተነገረ ይገኛል። በዚህ ላይ ግን ጋርዲዮላ አይስማሙም።

“ድካም አይመስለኝም። ሊከሰት ይችል ይሆናል። ነገር ግን በቂ የሆነ የቡድን ስብስብ አለን።” ሲሉ ስፔናዊው አሰልጣኝ ለእንግሊዝ ጋዜጦች ተናግረዋል።

“ጋብሬል [ኼሱስ] ከቦርንውዝ ጋር አልተጫወተም። ከሌስተር ጋር ደግሞ 120 ደቂቃዎችን ተጫውቷል፤ እናም እሱ በህይወቴ አይቼው የማላውቀውን በከፍተኛ ሁኔታ ተጭኖ በመጫወቱ ዘዴ ላይም ከፍተኛ ተፋላሚ ነው። ለእኛ የጋለ ስሜትም በከፍተኛ ሁኔታ እገዛ ያድረግልናል።

“ዳኒሎ፣ በርናርዶ [ሲልቫ]፣ [አይካይ] ጉንዶጋን በሙሉ ከቦርንማውዝ ጋር ባደረግነው ጨዋታ ረድተውናል። ያያ [ቱሬ]ም አለን። በመጨረሻ ባደረገው ጨዋታ [ኦሌክሳንደር] ዚኒቼንኮም የጨዋታው ኮከብ ነበር። በቦርንማውዙ ጨዋታ ላይም በቡድን ስብስቡ ውስጥ አልነበረም።

“እርግጥ ነው በዚህ ጊዜ ውስጥ አፈራርቀን እንጠቀማለን። በየአራት ቀናት ልዩነት ጨዋታዎች ይኖሩናል። ባለፉት ጊዜያት የተጫወቱት በሙሉ በቀጣዩ ጊዜም የሚጫወቱ ይሆናል።” ሲሉ አሰልጣኙ ገልፀዋል።

ክለባቸው ረቡዕ ወደኒውካሰል አምርቶ የሚጫወተው ጋርዲዮላ አስደናቂውን ብቃቱን የሚያስቀጥል ብቁ የሆነ የቡድን ስብስብ እንዳላቸውም ተናግረዋል።

“በባርሴሎናና በባየር ሙኒክም የነበረኝም ሆነ እሁን በእዚህ ያሉኝ ተጫዋቾች ይህንኑ ዓይነቱ ብቃት ያላቸው ናቸው።” ሲሉ ተናግረዋል።

“በኃይለኛ አጨዋወት፣ ያለኳስ  ወደፊት ለመጓዝ በምናደርገው እንቅስቃሴ ምን ያህል ጥሩ እንደሆን ማስመስከር እንችላለን። ምክኒያቱም ከዚያ በኋላ በፍጥነት እና ከኳስ ጋር ውሳኔ ላይ እንደርሳለን።”

Advertisements