ቬንገር፣ ሞሪንሆ ላቀረቡት የዝውውር ወጪ ማነስ ቅሬታ ምክራቸውን ለገሱ

አርሰን ቬንገር  ለ21 ዓመታት በአርሰናል በአሰልጣኝነት ያሳለፉት ዋንጫ ለማንሳት እንደሚፎካከሯቸው ክለቦች ወጪ ማድረግ ሳይችሉ እንደነሆነ ለጆዜ ሞሪንሆ ምክር አዘል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የማንችስተሩ አለቃ ሆዜ ሞሪንሆ በማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝነት ዘመናቸው 300 ሚሊዮን ፓውንድ የሚጠጋ ገንዘብ ለዝውውር ወጪ አድርገዋል። ነገር ይህ የዝውውር ወጪ ከማንችስተር ሲቲ ጋር ለመፎካከር በቂ እንዳልሆነ ተናግረው ነበር።

ነገር ግን ቬንገር፣ የሞሪንሆ አስተያየት ሲነገራቸው በነገሩ ፈገግ በማለት እርሳቸው አሁንም ድረስ ቢሆን እንኳ በገንዘብ ገዳይ ሁልጊዜም የበታች እንደሆኑ ገልፀዋል።

የመድፈኞቹ አለቃ ስለጉዳዩ ሲናገሩም “ለ21 ዓመታት በዚያ ሁኔታ ላይ ነበርኩ። እናም አሁን በእዚያ ላይ ቅሬታ ላቀርብ አልችልም። ሁልጊዜም በሃብት ከእኛ በላይ ሁለት ወይም አራት ክለቦች ነበሩ። ያን መጋፈጡን በሚገባ ተምሬያለሁ።

“እኛ የምንችለውን ያህል ባለንበትን ሁኔታ አቻችለን እንዘልቃለን። ማንችስተር ሲቲ፣ ቼልሲ እና ማንችስተር ዩናይትድ ከእኛ በላይ ሃብታም ናቸው። ስኬታማ ለመሆን የሆነ መንገድ መፈለግ ይኖርብሃል።” ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቬንገር ለአሌክሲ ሳንቼዝ የዝውውር ጥያቄ እንዳልቀረበና ከዝውውር መስኮቱም ባሻገር በክለቡ ይቆያል ብለው እንደሚጠብቁ ገልፃዋል።

“ማንም ጥያቄ ያቀረበልን የለም። ከዚያ ውጪ አቋሜ ከዚህ በፊት የተናገርኩት ነው።” በማለት ቬንገር ተናግረዋል።

ቬንገር አክለውም “በዝውውር መስኮቱ ተግቼ እንቀሳቀሳለሁ። ክለቦች ተጫዋቾችን ለመግዛትና በውሰት ለመውሰድ ከእኛ ጋር ግንኙነት ያደርጋሉ። እኔም ቡድናችንን ለማጠናከር ማንኛውንም ዕድሎች ለመጠቀም ዝግጁ ነኝ።” ሲሉ ገልፀዋል።

ቬንገር ጃክ ዊልሼር አዲስ ኮንትራት ይፈርማል ብለው የሚጠብቁ ቢሆንም፣ ነገር ግን ስድስት ሳምንታት በጉዳት በሚርቀው ኦልቪዬ ዥሩ፣ እስከጥር ወር መጀመሪያ ድረስ በማይመለሰው አሮን ራምሴ እንዲሁም ለአስር ቀናት ከጨዋታ በሚርቀው ናቾ ሞንሪል የጉዳት ዜና ውጥረት ውስጥ ይገኛሉ።

ቬንገር ስለዚህ ጉዳይ ሲናገሩም “ሞንሪል፣ ዥሩና ራምሴ [ከጨዋታ] ውጪ ናቸው። ናቾ ለአስር ቀን፣ ዥሩ ከአራት እስከስድስት ሳምንታት ይርቃሉ። ነገር ግን ራምሴ ቶሎ የሚያገግም ተጫዋች በመሆኑ በጥር ወር መጀመሪያ መጫወት ይጀምራል።

“ዥሩም በጥር ወር መጀመሪያ ይመለሳል። ጉዳቱ የገጠመው በታህሳስ ወር መጀመሪያ ነው። ስለዚህ ከአራት እስከስድስት ሳምንት ማለት ደግሞ [እ.ኤ.አ] ከጥር 10-15 ነው።

“ከጃክ ጋር ቁጭ ብዬ እነጋገራለሁ። በገንዘብ ጉዳይ ላይ ከስምምነት መድረስ የምንችል ከሆነ በክለቡ መቆየት ይፈልጋል ብዬ አምናለሁ።” በማለት ተናግረዋል።

Advertisements