የዩጋንዳ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለብሔራዊ ቡድኑ አዲስ አሰልጣኝ መቅጠሩ አሳወቀ

ፈረንሳዊው ሴባስቴይን ዲሳብሬ ስሪዶቪች ሙሉቲን ሚቾን በመተካት የክሬንሶቹ አዲሱ አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ።

ሚቾ ባለፈው ሀምሌ ወር ላይ ደሞዛቸው ስላልተከፈላቸው ከዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ሀላፊነታቸው በገዛ ፍቃዳቸው ኮንትራታቸውን ካቋረጡ በኋላ ተተኪ አሰልጣኝ ያልቀጠረው የዩጋንዳ እግርኳስ ፌዴሬሽን በመጨረሻም አዲስ አሰልጣኝ ቀጥሯል።

ከ 100 በላይ አሰልጣኞች ክሬንሶቹን ለማሰልጠን ፍላጎታቸውን ያሳዩ ቢሆኑም መስፈርቱን አልፈው ያሸነፉት የ41 አመቱ ፈረንሳዊው ሴባስቴይን ዲሳብሬ ሆነዋል።

ዲሳብሬ ለመጨረሻ እጩ ሆነው ከቀረቡት የክሬንሶቹ ጊዚያዊ አሰልጣኝ የነበሩት ሞሰስ ባሴና፣ኢሚሎ ፌሬራ እና ጆናታን ማክኪንስትሪን ጋር ተወዳድረው ቅድሚያ ተሰጥቷቸዋል።

በካሉሺያ ቡዋሊያ የሚመራው አምስት አባላት ያለው ቡድን አሰልጣኞቹን በመምረጥ ተሳትፎ እንዳደረገ ታውቋል።

አዲሱ አሰልጣኝ በክሬንሶቹ ለሶስት አመት ለመቆየት ፊርማቸውን የፈረሙ ሲሆን ወርሀዊ ደሞዛቸውም በወር እስከ 25ሺ ዶላር እንደሚደርስ ታውቋል።

የመጀመሪያ ስራቸውንም በቅርቡ የሚጀመረው የ 2018 የቻን ውድድር ላይ ጠንካራ ቡድን ይዞ መቅረብ ሲሆን ዝግጅታቸውንን በዚህ ሳምንት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።

አሰልጣኙ በግብፅ ፕሪምየርሊግ የሚወዳደረው ኢስማይሊ ሲያሰለጥኑ የቆዩ ሲሆን እሮብ ምሽትም ኤል ራጃን 5-0 ካሸነፉ በኋላ በይፋ መልቀቂያ በማስገባት ከክለቡ ጋር ተለያይተው ወደ ዩጋንዳ ማቅናታቸው እርግጥ ሆኗል።