ጆርጅ ዊሃ| የዓመታት ልፋቱን ለማሳካት ከጫፍ የደረስው የቀድሞው የሜዳ ላይ ኮከብ 

ጆርጅ ዊሃ ከፍ ያለ ስኬት ያገኘበትን ጊዜ ጨምሮ አልጋ በአልጋ የሆነ ህይወት አሳልፏል። የቀድሞው የሞናኮ፣ ፒኤስጂ፣ ኤሲ ሚላን እና ቼልሲ ተጫዋቹ እ.ኤ.አ. በ1995 በአንድ የውድድር ዘመን የአፍሪካ፣ የአውሮፓ እና የዓለም እግርኳስ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች በመባል ከዓለማችን ታሪካዊ የእግርኳስ ተጫዋቾች ተርታ መሰፍ የቻለ ብቸኛው አፍሪካዊ ተጫዋችም ነው።

 ነገር ግን የዓለማችን ቁንጮ ተብሎ ለተመረጠው ብቸኛው የ51 ዓመቱ አፍሪካዊ ይህ ብቻውን በቂ አይደለም። በእንደዚህ ዓይነቱ የተከበረ የእግርኳስ ህይወት የትዝታ ድባብ ውስጥ ብቻ ለመኖርም አይሻም። ይልቁንስ ለ12 ዓመታት የዘለቀውን የላይቤሪያ ፕሬዘደንት የመሆን ከፍ ያለ መሻቱን ለማሳካት የህይወቱን ትልቅ ፍልሚያ ተጋፍጦ የላይቤሪያ 25ኛው ፕሬዝዳንት ለመሆን የተደረገውን ምርጫ በአብላጫ ድምፅ አሸንፏል።

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ሽልማትን፣ የፈረንሳይ ዋንጫን፣ ሊግ 1ን፣ የፈረንሳይ ሊግ ዋንጫን፣ የሴሪ ኣ እና የእንግሊዝ ኤፍኤ ዋንጫዎችን ጭምር ማሸነፍ የቻለው ዊሃ ለፕሬዝዳንትነት መመረጡ በይፋ ባይገለፅም በይፋዊ ትዊተር ገፁ የሚከተለውን ሃሳብ አስቀድሞ አስፍሯል።

“ለቤተሰቦች፣ ለጓደኞቼ እና በእዚህ እጅግ የተራዘመ የምርጫ ወቅት ለፉክክሩ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ላበረከቱ ታማኝ ደጋፊዎቼ የተሰማኝን ጥልቅ ምስጋና አቀርባለሁ።”

ዊሃ ከወቅታዊው የሃገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ከሆኑት ጆሴፍ ቡአካይ ጋር ለፕሬዝዳንትነት ምርጫው አንገት ለአንገት ተናንቆ የመጀመሪያውን ዙር ማሸነፍ ቢችልምና የፕሬዝዳንትነቱ መንበር ለመረከብ ማግኘት የሚገባውን 50 በመቶ ድምፅ ለማግኘት ታህሳስ 17 በሃገሪቱ የመጨረሻ ዙር የድምፅ አሰጣጥ እንደሚካሄድ ቢጠበቅም በቀድሞዋ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሲርሊፍ ህጋዊ ጥያቄ መሰረት የምርጫው ቀን እንዲራዘም ተደርጓል። ይሁን እንጂ ዊሃ ማሸነፉን በርካታ የመገናኛ ብዛሃን ገልፀዋል። የምርጫ ውጤቱም ዛሬ [ሃሙስ] ታህሳስ 19 በይፋ ይገለፃል ተብሎ ይጠበቃል።

ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር እ.ኤ.አ. ከ1990 አንስቶ ካሳለፈችበት የእርስበርስ ጦርናት ድባብ እስካሁን ሳትላቀቅ በ2014 እና 2016 ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን በኢቦላ ቫይረስ አጥታ ኢኮኖሚዋ በእጅጉ ተዳክሟል። 

“የሃገሬ እና የህዝቦቿ ፍቅር ሃገሬን እንዳገለግል ጥሪ አቅርቦልኛል።” ሲል ዊሃ በሞኖሮቪያው የፓርቲው የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ተናግሯል።

“በጣም ብዙ ሰዎች አንድ የቀድሞ እግርኳስ ተጫዋች የሃገሩ ፕሬዝደንት ለመሆን ለምን ፍላጎት እንዳደረበት ሊገርማቸው እንደሚችል አውቃለሁ። ነገር ግን አንድ ጠበቃ ወይም የንግድ ሰው ይህን ቢያደርግ ማንም ጥያቄውን አያነሳም።” ሲል ዊሃ የቀድሞዋ የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ኢኮኖሚስት እና የ2011 የኖቤል ተሸላሚዋ ኤለን ጆንስ እንኳ የተወሳሰበውን የላይቤሪያ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳዮች ለመቅረፍ የፕሬዝዳንትነቱ ስራ ታላቅ ተግዳሮት ሆኖባት እንደነበር እና እሱ ልምድ እንደሌለው ጠቅሰው በሚተቹት ላይ ያለውን ግልፅ ቅሬታ ገልፅዋል።

ዊሃ እ.ኤ.አ. በ2005 ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድሮ በኤለን ጆንሰን ሲርሊፍ ሽንፈት ገጥሞታል። ያ ሽንፈት እና በ2014 ለላይቤሪያ ምክር ቤት የሃገሪቱን ትልቅ የምክር ቤት ማቀመጫ ያለውን ግዛት መወከሉ እሱ እንዳለው “ጠቃሚ ትምህርታዊ ተመክሮ” ሆኖታል።

“በጣም ብዙ ሰዎች [በ2005] ተሸንፌ ፕሬዝዳንት ባለመሆኔ ስሜታቸው ተነክቷል። ነገር ግን ለእኔ ጥሩ ስሜት ነበረው። ያን ተመክሮም አሁን እያደረግኩት ላለሁት ነገር እንደመዘጋጃ አድርጌ ቆጥሬዋለሁ። ከበርካታ ዓመታት በፊት ከኔልሰን ማንዴላ ጋር ባደረግኩት ውይይት ሃገሬን ለማገልገል ጥሪ ከቀረበልኝ የግድ ትክክለኛውን ነገር ማድረግ እንደሚገባኝ ነግሮኛል። ተግባራዊ እያደረግኩ ያለሁትም ያንን ምክር ነው።” በማለት ዊሃ ገልፅዋል።

በ2005 ምርጫ ከፖሊቲካ ልሂቃኑ ይሰነዘርበት ከነበረው አብይ አሉታዊ ትችቶች መካከል አንዱ የነበረው የዊሃ በቂ የሆነ የመደበኛ ትምህርት እጥረት ነበር። ይሁን እንጂ የቀድሞው ተጫዋች በ40 ዓመት ዕድሜው በ2006 የሁለተኛ ደረጃ ትምህረቱን በማጠናቀቅ ባለፉት ስድስት ዓመታት ወደፍሎሪዳው ደቭሪ ዩኒቨርስቲ አምርቶ በ2011 የመጀመሪያ ዲግሪውን በቢዝነስ አመራር ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ በህዝብ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪውን ይዟል።

ዊሃ የስፖርት ኮሚቴ ኃላፊ ለመሆን ድምፅ ያገኘበት መንገድና እና በምክር ቤት ውስጥ በነበረው ሙግት ላይ በነበረው ደካማ አስተዋፅኦ በእንዳንድ ላይቤሪያውያን ትችት ቢሰነዘርበትም “የእኔ ኃላፊነት ስለህዝቦቼ መናገር እና ስለፍላጎታቸው መመያየት ነበር። …በዚህም ከፍ ያለ ስኬት አግኝቻለሁ። የስራዬ ውጤት በዚያ አለ። ስራዬንም ህዝቦቼ ያውቁታል።” ሲል ዊሃ የመከላከያ ሃሳብ ያቀርባል።

“ወደሞንቴ ካርሎ ሳመራ [እ.ኤ.አ. በ1988 ከካሜሮኑ ክለብ ቶኔሬ ያውንዴ ለሞናኮ ለመጫወት] ለስድስት ወራት አልተጫወትኩም ነበር። ነገር ግን ክህሎቴን ለማሳየት፣ ወደአውሮፓ መምጣቴ ጊዜ ለማባከን እንደሆነ ለሚያስቡት የሃገሬ ሰዎች ጥሩ ተጫዋች እና ብቁ እንደነበርኩ ብቃቴን ለማሳየት ቁርጠኛ ነበርኩ።” ሲል ገልፅዋል።

አርሰን ቬንገር በሞናኮ የዊሃ አሰልጣኝ ነበሩ። በሁለቱ መካከል የነበረው ግንኙነትም ከተለመደውም በላይ ከፍ ያለ ነበር።

“እሱ ለእኔ አባታዊ ስብዕና ነበርው። እንደልጁም ይቆጥረኝ ነበር። ዘረኝነት ጫፍ በደረሰበት ወቅት ፍቅር ያሳየኝ እሱ ነበር። በየቀኑም የእኔን ጫፍ መድረስ ይፈልግ ነበር። 

“በልምምድ ተዳክሜ በነበረበት አንድ ቀን እራሴን እንዳመመኝ ነገርኩት። እሱም “ጆርጅ ከባድ መሆኑን አውቃለሁ። ነገር ግን ጠንክረህ መስራት አለብህ። አንተ ባለህ ክህሎት የዓለማችን ምርጡ ተጫዋች ልትሆን እንደምትችል አምናለሁ።” ሲል ነገርኝ።

“እናም ምክሩን አዳምጬ ልምምዴን ቀጠልኩ። ከፈጣሪ ቀጥሎ ያለአርሰን በአውሮፓ ልቆይ የምችልበት መንገድ አልበረም።” ይላል ዊሃ ስለፈረንሳዊው አሰልጣኝ ያለውን ስሜት ሲገልፅ።

ዊሃ ጊዜን የሚሻው የፓለቲካ ህይወት በሞኖሮቪያ በሚሆንበት ጊዜ አልፋ ኦልድ ታየመርስ ለተስሰኘው የጤና ቡድን ዘወትር ቅዳሜ የሚወደውን እግርኳስ ጨርሶ እንዳይጫወት አላደረገውም። 

በምክር ቤቱ በነበረነት ወቅት የቀርበበት ትችት የላይቤሪያ ወጣቶች ለዊሃ ያላቸውን ከፍ ያለ ድጋፍ እንዲነፍጉትም አላደረጋቸውም። “ወጣቶች እንደዘመናችን መሲህ ይመለከቱታል።” ሲል የቀድሞው የአርሰናል አጥቂ እና የዊሃ ዘመድ የሆነው ክሪስቶፎር ሪህ ተናግሮ “ባለፉት 12 ዓመታት ሃገራችንን የመሩት ሰዎች አልበጁንም። ለዊሃ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት የመሆኛው ጊዜ አሁን መሆኑን አልጠራጠርም።” በማለትም ጨምሮ ተናግሯል።

ይሁን እንጂ እንደ ጄምስ ደባህ ያሉ ሌሎች የራሱ የቤተሰብ አባላት ግን የዊሃን ያለፈ ጊዜ ዝነኛ የእግርኳስ ስብዕና ለዊሃ የፕሬዝዳንትነት ስኬት ተግዳሮት እንደሚሆን ይሞግታሉ። “እሱን ብመርጥ በጣም ኢሚዛናዊናት እንደፈፅምኩ እቆጥረዋለሁ።” ሲል የቀድሞው የኒስ እና የፒኤስጂ ተጫዋች እ.ኤ.አ. በነሃሴ 2005 ተናግሮ “ምክኒያቴ ደግሞ ሊኖር የሚገባው የመንግስት አስተዳደር ልምድ እሱ የሌለው መሆኑ ነው። ወደአደባባይ የወጣው ውስብስብ የሆነው ፓለቲካን ሳይረዳ በየዋህነት ነው።” ሲል ገልፅዋል።

በሁለተኛው የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ላይ ለዊሃ ድጋፉን ይሰጥ እንደሆን የተጠየቀው ደቦሃ የሚጠቀማቸውን ቃላት በጥንቃቄ በመምረጥ “ጆርጅ በተለይም ከወጣቶቹ ሰፊ የሆነ ተከታይ እንዳለው አይጠረጠርም። ስለሆነም ትልቅ ዕድል አለው።

“ጆርጅ በእግርኳስ በርካታ ስኬቶችን አግኝቷል። በዚህም ሰዎች ይወዱታል። ነገር ግን የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ከሆነ ሰዎች በእግርኳስ ሜዳ ላይ የነበረውን ብቃት ይረሱትና በቢሮ ውስጥ በሚያሳካው ነገር የሚመዝኑት ይሆናል። ያን ካላሳካ ደግሞ ሰዎች ፊታቸውን ያዞሩነበታል። እናም የገባው ትልቅ አደጋ ውስጥ ነው። እኔም መልካሙን እመኝለታለሁ።” ብሏል።

ዊሃ ፕሬዝዳንታዊ የስራ ሚና ለበርካቶች አስቸጋሪ እንደሆነ በመረዳት “ማድረግ የማልችለውን ነገር ለህዝብ ቃል አልገባም። ነገር ግን አንዳች ፋይዳ ትቼ ማለፌ ግን እርግጥ ነው። ህዝብ እንድትመራው ስልጣኑን ከሰጠህ ትልቅ ነገር ይጥቅብቅብሃል።” ሲል ተናግሮ “ዕድሎችን እንድታመቻችላቸው ሃገር እንድትገነባ ይሻሉ። ያን የማታሳካ ከሆነ አንተን ከቢሮ ለማስወገድ ማንኛውም መብት አላቸው። ነገር ግን እኔ ፈፅም በህዝቤ እምነት ላይ ክህደት አልፈፅምም።” ሲል ዊሃ የማረጋገጫ ቃሉን ሰጥቷል።

Advertisements