ጋርዲዮላ፣ ባርሴሎና በመሲ ምክኒያት የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ የማንሳት የተሻለ ዕድል እንዳለው ገለፁ

የማንችስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ባርሴሎና በሊዮኔል መሲ ምክኒያት የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ የማንሳት የተሻለ ዕድል እንዳለው ገልፅዋል።

 ማንችስተር ሲቲ ረቡዕ ምሽት ኒውካሰልን 1ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ 18ኛ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቦ በ15 ነጥቦች ልዩነት የደረጃ ሰንጠረዡን በቀዳሚነት መምራት ችሏል።  

ማንችስተር ሲቲ በዚህ የውድድር ዘመን ለአራት ዋንጫ የሚፋለም ሲሆን 16 ክለቦች በቀሩት የሻምፒዮንስ ሊጉ የጥሎ ማለፍ ዙርም ከባሰል ጋር ለመጫወት ተደልድሏል። ነገር ግን ሲቲ የውድድሩ አሸናፊ የመሆን የተሻለ ዕድል ይኖረው እንደሆነ ጥያቄ የቀረባቸው ጋርዲዮላ ቀላል መልስ ሰጥተዋል።

“[ሊዮኔል] መሲ ለማን ነው የሚጫወተው?” በማለት ጋርዲዮላ ጠይቀው “ባርሴሎና።” ሲሉ ለራሳቸው ጥያቄ ምላሹን ራሳቸው ሰጥተዋል።

“ስለዚህ እነሱ [ባርሴሎናዎች] የተሻለ ዕድል አላቸው።” ሲሉም ተናግረዋል።

ጋርዲዮላ በጥር ወር በ75 ሚሊዮን ፓውንድ ወደአንፊልድ ለመዛወር የተስማማው የሳውዛምፕተኑ ሆላንዳዊ ተከላካይ ቪርጅል ቫንዳይክ ላይ ማንችስተር ሲቲ ፈፅሞ ፍላጎት እንዳልነበረውም ተናግረዋል።

ራሂም ስተርሊንግ በሴንት ጀምስ ፓርክ የሲቲን የማሸነፊያ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ቫን ዳይክ በጥር ወር ለማዛወር የሚፈልጉት ተጫዋች እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ስፔናዊው አሰልጣኝ “አይደለም፤ አይደለም፤ አይደለም፤ አይደለም።” ሲሉ ቁርጥ ያለ መልስ ሰጥተዋል።

Advertisements