አትሌቲኮ ማድሪድ ከግሪዝማንም በላይ ዲያጎ ሲሞኒን ማጣቱ ከባድ እንደሚሆንበት ጂል ማሪን ተናገሩ 

እንደአትሌቲኮ ማድሪድ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚጉዌል ኤንጀል ጂል ማርቲን ሃሳብ ከሆነ የማድሪዱ ክለብ ኮከቡን አጥቂ አንቱዋን ግሪዝማን ከማጣትም በላይ አሰልጣኙን ዲያጎ ሲሞኒን ማጣት በእጅጉ ከባድ ነው።

ባርሴሎናና እና ማንችስተር ዩናይትድ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ በፊፋ ተጫዋች እንዳያዛውር እገዳ የተጠለበት መሆኑን ተከትሎ የውድድር ዘመኑ ከመጀመሩ በፊት ክለቡን የመልቀቅ ኃሳቡን ለመተው ውሳኔ ላይ የደረሰውን ፈረንሳያዊውን የፊት ተጫዋች ለማዛወር የዝውውር ዋጋ አቅርበዋል በሚል ስማቸው ከተጫዋቹ ጋር በሰፊው ተያይዞ ቆይቶ ነበር።

ጂል ማሪን የውድድር ዘመኑ ከማብቃቱ በፊት ግሪዝማንን ለመሸጥ ምንም እይነት ድርድር እንደማያደርጉ ግልፅ ያደረጉ ሲሆን፣ ክለቡም ከተጫዋቹ ጋር ህጋዊ ያልሆነ ግንኙነት ፈፅሟል ብሎ በማሰቡ ባርሴሎናን ለዓለም አቀፉ የእግርኳስ አመራር አካል አቤቱታ ለማቅረብ ስለማሰቡ ዘገባዎች አመልክተው ነበር።

ይሁን እንጂ ዋና ስራ አስፈፃሚው ከዋንዳ ሜትሮፓሊታኖው ክለብ ጋር እስከ2020 ድረስ የሚዘልቅ የኮንትራት ስምምናት ያላቸው ሲሞኒ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከማንኛውም ተጫዋች በላይ ፋይዳ እንዳለው ያምናሉ። 

“ሲሞኒን ማጣት ከአንቶዋን ግሪዝማንም በላይ የከፋ ጉዳይ መሆኑ ፈፅሞ አይጠረጠርም።” ሲሉ የሃገሪቱ ሚዲያ ለሆነው ኦንዳ ሴሮ ተናግረዋል።

“ሲሞኒ ባለው ፋይዳ፣ ስራ እና የአጨዋወት ስልቱ ክለቡን ይወክላል። እሱ እግርኳስ ቡድኑን ሲወክል የትኛውም ተጫዋች ግን ቡድኑን አይወክልም።” ብለዋል

ጂል ማርቲ  አክለውም “በግሪዝማን ጉዳይ ባርሴሎናን እንዲቀጣ ለፊፋ ጥያቄ አላቀረብንም። ነገር ግን በተለይም ዳይሬክተሩ ጉሌርሞ አሞር የክለቡ ፕሬዝዳንት የሆኑት ጆሴፍ ማሪያ ባርቶሚዩ ከፊት ተጫዋቹ ቤተሰቦች ጋር ስለመነጋገራቸው በመግለፃቸው ክለቡ በላ ሊጋ ተቀናቃኞቹ “ክብር” እንዲሰጠው እንደሚፈልግ አሳይቷል። 

“ከባርሳ ጋር ያለን ግንኙነት በጣም ጥሩ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው ማድረግ የማይገባውን ነገር ሲያደረግ እኛ ደግሞ ራሳችንን እንከላከላልን።” ሲሉ ተናግረዋል።

“ጉሌርሞ አሞር ከሰጡት አስተያየት ባሻገር ከባርሳው ስራ አስፈፃሚ ጋር ተነጋግሬያለሁ። ከወኪሎቹ እና ከግሪዝማን ቤተሰቦችም ጋር ተነጋግሬያለሁ። ግንኙነት መደረጉ ግን ግልፅ ነው።

“በባርሳ ላይ ቅጣት እንዲጣል እያደረግን አይደለም። ክብር እንዲሰጠን ግን እያደረግን ነው።” ሲሉ ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።

አትሌቲኮ ማድሪድ በስፔኑ ላ ሊጋ በደረጃ ሳንጠረዡ አናት ላይ ከሚገኘው ባርሴሎና በዘጠኝ ነጥቦች ዝቅ ብሎ በ36 ነጥብ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።