“የሂሳብ መዝገባችን ለማስተካከል ብለን ፍሊፔ ኮቲንሆን አንሸጥም” – የርገን ክሎፕ

የርገን ክሎፕ ቨርጂል ቫንዳይክን ለማዘዋወር ያወጡት የክለባቸው ሪከርድ የዝውውር ሂሳብን ለማካካስ ሲሉ ፍሊፔ ኮቲንሆን መሸጥ እንደማይፈልጉ ተናገረዋል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ለጆሮ ካሰለቹ የዝውውር ሂደቶች መካከል አንዱ የነበረው የሆላንዳዊው ቨርጂል ቫንዳይክ ወደ ሊቨርፑል ሊያደርገው የነበረው ዝውውር ባይሳካም ሳይታሰብ የጥር የዝውውር መስኮት ከመከፈቱ አስቀድሞ ተጫዋቹ የቀዮቹ ንብረት መሆኑ ተረጋግጧል።

ሊቨርፑል ተጫዋቹን ለማዘዋወር 75 ሚሊየን ፓውንድ ወጪ ያደረገ ሲሆን ይህም የክለቡ ከፍተኛ የዝውውር ሪከርድ ሀኗል።

“ቅዱሳኖቹ” እየተባሉ የሚጠሩት ሳውዝሀምፕተኖችም አሁንም ተጫዋቾቻቸውን በየአመቱ መሸጣቸውን ቀጥለዋል።በተለይ ሊቨርፑል ባለፉት 8 አመታት ከዚሁ ክለብ ያዘዋወራቸው ተጫዋቾች በዝተዋል።

ሊቨርፑል ለሆላንዳዊው ተከላካይ ያወጣው የሂሳብ መዝገብ ለማካካስ ሲባል ፍሊፔ ኩቲንሆን ለባርሴሎና አሳልፎ መልቀቁ እንደማይቀር እየተነገረ ቢገኝም የክለቡ አሰልጣኝ የሆኑት የርገን ክሎፕ ግን ወሬውን አጣጥለውታል።

ባርሴሎና ተጫዋቹን ለማስፈረም ባለፈው የክረምቱ የዝውውር መስኮት 115 ሚሊየን ፓውንድ በማቅረብ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም በመጨረሻ ሳይሳካላት ቀርቶ እንደነበር ይታወሳል።

ለዚህ ምላሽ የሰጡት የርገን ክሎፕ “የሂሳብ መዝገባችን ለማስተካከል ብለን ኮቲንሆን መሸጥ አንፈልግም፣የቫንዳይክ ዝውውር በኮቲንሆ ቆይታ ላይ የሚፈጥረው ነገር የለም።”በማለት ምንም አይነት ተጫዋች መሸጥ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።

“ልናገር የምችለው ብቸኛ ነገር እንዲሁም ትኩረት የማደርገው ነገር ቢኖር አሁን ኮቲንሆ እንዴት እየተጫወተ እንዳለ ነው።ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ባሳየው አቋም እና በፈጠረው ተፅእኖ በጣም ደስተኛ ነኝ።

“በጨዋታ እና በልምምድ ላይ ከሱ መልካም ነገርን ተመልክቻለው።ያ ደግሞ እኔ ትኩረት የማደርግበት ነገር በመሆኑ ከዚህ ውጪ ያሉት ነገር ላይ ማውራት አልፈልግም።ምክንያቱም እኔ በሩን ከከፈትኩላችሁ እናንተ ሚዲያዎች ቀኑን ሙሉ ስታወሩት ትውላላችሁ።

“ክለቡ መናገር የሚፈልገው  ነገር ካለ ያኔ ታውቁታላችሁ።በኔ አመለካከት ምናልባት፣ሊሆን ይችላል .. የሚሉ አጠራጣሪ አነጋገሮች ምንም አይነት ትርጉም አልሰጣቸውም።ምክንያቱም ሁሉም 90% እውነት ያልሆነ ታሪክ ይወጣቸዋል።ስለዚህ ለምን እንደዛ እናደርጋለን?”ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።

Advertisements