“በጭንላቱ ውስጥ ያለውን ነገር የምረዳ የስነልቡና ባለሙያ አይደለሁም።” – ቬንገር ስለሳንቼዝ

አሌክሲ ሳንቼዝ ወደማንችስተር ሲቲ የመዛወር ፍላጎት እንዳለው የሚገልፁ ዘገባዎች እየወጡ በሚገኙበት በዚህ ወቅት አርሰን ቬንገር የቺሊያዊውን አጥቂ የወደፊት እጣ ፈንታ “የማይታመን” በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

በዚህ ሳምንት የወጡ ዘገባዎች እንዳመለከቱት የ29 ዓመቱ ተጫዋች ምንም እንኳ ከአርሰናል ጋር ያለው ኮንትራት የሚጠናቀቀው በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ቢሆንም ተጫዋቹ ግን ከወዲህ በጥር ወር ወደኢትሃድ ስታዲየም የማምራት ፍላጎት አለው። 

እንደእንግሊዙ ጋዜጣ ዘጋርዲያን ዘገባ ከሆነም ባለፈው ወር አርሰናል በበርንሌይ 1ለ0 በሆነ ውጤት ከተሸነፈ በኋላ በመልበሻ ክፍሉ ውስጥ ለተፈጠረው አለመግባባትና ግጭት አሌክሲ ሳንቼዝ ዋናኛው ተዋናይ ነበር። የክለቡ ታሪካዊ ተጫዋች ቴሪ ሆነሪም መድፈኞቹ  ክሪስታል ፓለስን ባሸነፉበት ጨዋታ ግብ ሲያስቆጥሩ ባሳዩት የደስታ መግለጫ በተጫዋቾቹ ላይ መከፋፈል እንደነበር የሚያሳዩ ምልክቶችን ጠቁሞ ነበር።

ቬንገር አርሰናልን በአሰልጣኝነት ከተረከቡ በኋላ በፕሪሚየር ሊጉ የሰር አሌክስ ፈርጉሰንን የቁጥር ክብረወስን በልጠው 811ኛ ጨዋታቸውን ለማድረግ ዛሬ (እሁድ) ወደዌስት ብሮም ያቀናሉ። ይህን ተከትሎም ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በሳንቼዝ ጉዳይ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

“ጥሩ ሲጫወት ችግር አለው። ችግርስ ከሌለ? ያ የማይታመን ነገር ነው።

“እናንተ አንድን ተጫዋች የምትዳኙት ጥሩ ተጫወተ ወይም አልተጫወተም ብላችሁ ነው። ከዚያ በኋላም በዚያ ላይ አስተያየታችሁን ትሰጣላችሁ።

“ለረጅም ጊዜ ይቆይ አሊያም ለአጭር ጊዜ በጭንቅላቱ ውስጥ ያለውን ነገር የምረዳ የስነልቡና ባለሙያ አይደለሁም። 

“እናንተ ለዚህ ጉዳይ አጨዋወትን ትመለከታላችሁ። ከዚያም ጥሩ ተጫወተ ወይስ አልተጫወተም ብላችሁ [ስለቆይታው] ፍርድ ትሰጣላችሁ።” ሲሉ ፈረንሳያዊው አሰልጣኝ ተናግረዋል።

ሳንቼዝ ከባርሴሎና አርሰናልን ከተቀላቀለበት 2014 አንስቶ በሁሉም ውድድሮች ላይ ተሰልፎ በተጫወተባቸው 120 ጨዋታዎች 60 ግቦች ከመረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።

Advertisements