ናይኪ ድረ ገፅ ለፊሊፕ  ኮቲንሆ የባርሴሎና ዝውውር ግልፅ ፍንጭ ሰጠ

ባለፈው ክረምት የዝውውር መስኮት ከካታላኑ ክለብ ጋር ስሙ በስፋት ሲያያዝ የከረመው ብራዚላዊ የሊቨርፑል ኮከብ ፊሊፕ  ኮቲንሆ ወደስፔን ማቅናቱ የማይቀር መሆኑን የሚያሳብቅ መረጃ የባርሴሎና ይፋዊ ትጥቅ አቅራቢ በሆነው ናይኪ ይፋዊ ድረ ገፅ ላይ ወጥቷል፡፡

በሊቨርፑል ቤት ድንቅ ብቃቱን ማሳየቱን የቀጠለው ኮቲንሆ ለባርሴሎና የመጫወት ፍላጎቱን ለማሳካት ከክለቡ አመራሮች ጋር እስጥ አገባ ውስጥ ገብቶ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ጠዋት የተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ይዘው እንደወጡት መረጃ ከሆነ የተጫዋቹ ፍላጎት በመጨረሻም እውን የሆነ ይመስላል፡፡

የ2017/18 የባርሴሎና ማልያን ሽያጭ የሚያስተዋውቅ ማስታወቂያን በድረ ገፁ ላይ የለቀቀው ክለቡ “ፊሊፕ ኮቲንሆ በኑውካምፕ ለማንፀባረቅ ተዘጋጅቷል ፤ የምትሃተኛው ተጫዋች ስም ያረፈበትን መለያ በፍጥነት ይግዙ ” የየምትል መግለጫ የተካተተበትን ማስታወቂያ በድረገፁ ከለቀቁ ከደቂቃዎች በኋላ መልሰው ቢያጠፉትም ወሬው የዜና አነፍናፊዎች ሲሳይ ከመሆን አልተረፈም፡፡

የቀድሞው የኢንተር ሚላን ኮከብ ከግብፃዊው መሃመድ ሳላህ ጋር በመጣመር አስደናቂ እንቅስቃሴን ለሊቨርፑል እያበረከተ ይገኛል፡፡

Advertisements