ጆሴ ሞሪንሆ ስለ ሉካኩ እና ዝላታን የጉዳት ሁኔታ ተናገሩ


ሞሪንሆ ማንችስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድትራፎርድ ከሳውዝሀምፕተን ጋር 0-0 ከተለያየ በኋላ በጨዋታው ጉዳት ስላጋጠመው ሮሜሉ ሉካኩ እንዲሁም ከጨዋታው ውጪ ስለነበረው ዝላታን ኢብራሂሞቪች ሁኔታ ተናግረዋል።

ዩናይትዶች ዘንድሮ በሜዳቸው ካደረጓቸው ጨዋታዎች ውስጥ ደካማ እንቅስቃሴ ባደረጉበት ጨዋታ ከሳውዝሀምፕተን ጋር ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል።

አጀማመራቸው በሜዳቸው የማይነኩ አስመስሏቸው የነበረ ቢሆንም ጎረቤታቸው ማን ሲቲዎች ካሸነፏቸው በኋላ በሜዳቸው በተከታታይ ነጥብ እየጣሉ ይገኛሉ።

ባለፈው ማክሰኞም በተመሳሳይ በግዙፉ ሜዳቸው በርንሌ ከመሸነፍ የዳኑት ሊንጋርድ ባስቆጠረው የመጨረሻ ደቂቃ ጎል እንደነበር ይታወሳል።

ጆሴ ባለፈው ሳምንት ሲቲዎች ከፍተኛ የዝውውር ወጪ በማውጣታቸው ሌሎች ክለቦች እነሱን ሊፎካከር እንዳልቻለ በመናገር የቡድናቸውን ድክመት ለመሸፈን ቢሞክሩም የቀድሞ የሊቨርፑል ተጫዋች የነበረው ጂሚ ካራገር በበኩሉ ይኸው የጆሴ ቡድን ፔፕ ጓርዲዮላ ቢይዘው የዋንጫ ባለቤት እንደሚያደርገው በመናገር የጆሴ አስተያየትን አጣጥሏል።

የቡድኑ ደጋፊዎችም በክለቡ ወቅታዊ አጨዋወት እና የአቋም መውረድ ምክንያት ተቃውሟቸውን ማሰማት የጀመሩ ሲሆን ትናንት ምሽትም ባልተለመደ ሁኔታ የተቃውሞ ድምፆች ጠንክረው ተሰምተዋል።

ጆሴ ከተቃውሞ በተጨማሪ ሌላ ፈተና ከፊታቸው የተደቀነ ይመስላል።ለሳቸው የማይነካ አድርገው በየጫወታው በቋሚነት ሲያጫውቱት የነበሩት ሮሜሉ ሉካኩ ጉዳት አጋጥሞት በሜዳ ላይ ሰፊ የህክምና ክትትል ከተደረገለት በኋላ በቃሬዛ ወጥቷል።

ተጫዋቹ ኳስ አየር ላይ ለመግጨት በሚዘልበት ወቅት ሌላ የሳውዝሀምፕተን ተከላካይ ከኋላው ጭንቅላቱን ከገጨው በኋላ በህክምና ቡድን እርዳታ ክትትል ሜዳውን ለመልቀቅ ተገዷል።

የተጫዋቹ ጉዳት ጠንካራ መስሎ የነበረ ቢሆንም የህክምና ቡድኑ ያደረገለት የመጀመሪያ ህክምና በቂ ሆኖ ወደ ሆስፒታል ሳይወሰድ ቀርቷል።

ከጨዋታው በኋላ በሉካኩ እና በሳውዝሀምፕተኑ ጨዋታ ውጪ ተደርጎ የነበረው ዝላታን ኢብራሂሞቪች ዙሪያ የተናገሩት ሞሪንሆ ሁለቱን አጥቂዎቻቸው በቀጣዩ ጥቂት ጨዋታዎች ላይ እንደማያገኟቸው አረጋግጠዋል።

ጠንካራ የጉልበት ጉዳት አጋጥሞት ለረጅም ወራት ከጨዋታ ውጪ ከሆነ በኋላ ወደ ሜዳ የተመለሰው ዝላታን በሙሉ የጨዋታ ቅርፅ ላይ እንዳልሆነ ባለፉት ያደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ መመልከት ተችሏል።

ጆሴም በተመሳሳይ የጉልበት ጉዳት በቀጣዮቹ አንድ ወራት ዝላታን ወደ ሜዳ እንደማይመለስ ሲያሳውቁ ስለ ሉካኩ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ እርግጠኛ ባይሆኑም ቢያንስ ከሁለት ጨዋታዎች ውጪ እንደሚሆን አረጋግጠዋል።

ይህ ደግሞ ዩናይትዶች በቀጣይ ከኤቨርተን ጋር በሚያደርጉት የጉዲሰን ፓርክ ጨዋታ ሉካኩ ወደ ቀድሞ ክለቡ ሜዳ ተመልሶ ከሚያደርገው ጨዋታ ውጪ ያደርገዋል።

ዩናይትዶች በተከታታይ በጣሏቸው ነጥቦች ምክንያት ከዋንጫ ፉክክር ውጪ የሆኑ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በፊት በሰባት ነጥብ ይመሩት ከነበሩት ቼልሲም ተቀድመው በሶስተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገደዋል።

Advertisements