ሊቨርፑል ቪርጅል ቫን ዳይክን በይፋ አስፈረመ

የዓለማችን ውድ ተከላካይ የሆነው ቪርጅል ቫን ዳይክ በዛሬው ዕለት በተከፈተው የጥር ወር የዝውውር መስኮት በይፋ የሊቨርፑል ተጫዋች ሆኗል።

የቀድሞው የሴልቲክ እና የሳውዛምፕተን ተጫዋች የሆነው ቫን ዳይክ በሊቨርፑል የመለያ ልብስ በክለቡ የልምምድ ሜዳ፣ ሜልዉድ ተገኝቶ ፊርማውን ማኖሩን የሚያሳዩ ምስሎች በክለቡ ይፋዊ ድረገፅ ተለቀዋል።

ሆላንዳዊው ተጫዋች ወደአንፊልድ እንደሚዘወር የተገለፀው ባለፈው ሳምንት የነበረ ቢሆንም፣ ዝውውሩ በይፋ ሊጠናቀቅ ይችል የነበረው የዝውውር መስኮት በይፋ በሚከፈትበት የፈረንጆቹ ጥር ወር [ከዛሬ አንስቶ] ነበር።

ቫን ዳይክ ሊቨርፑል ሌስተር ሲቲን 2ለ1 በረታበት ጨዋታ በአንፊልድ ኃላፊዎች የመቀመጫ ቦታ ተገኝቶ ጨዋታውን መመልከት ችሎም ነበር።

ተጫዋቹ ቀዮቹን መቀላቀሉን ተከትሎም ባክለቡ ይፋዊ ድረገፅ “እዚህ በመገኘቴ ደስተኛ ነኝ [ጨዋታ] ለመጀመርም መጠበቅ አልችልም። 

“ወሳኙ ነገር የክለቡ ዝና፣ የክለቡ ባህል፣ ተጫዋቾቹ፣ አሰልጣኙ እና ያላጥርጥርም ክለቡን ልዩ ያደረጉት ደጋፊዎቹ ናቸው። 

“በክለቡ ያለው ታሪክ እና በዙሪያው ያለ ነገር በሙሉ፣ የልምምድ ሜዳውና የስራ ባልደረቦቹ ሁሉ ፍፁም ልዩ ናቸው። ለእኔም ፍፁም ተስማሚ ናቸው። ለቤተሰቤም እንዲሁ ፍፁም የሚመጥኑ ናቸው።” ሲል ተናግሯል።

Advertisements