አሽሊ ያንግ የተጣለበት የሶስት ጨዋታ እግዳ ቅጣት እንዲፀናበት ተደረገ

የማንችስተር ዩናይትዱ ተጫዋች አሽሊ ያንግ የተከሰሰበትን ነውጠኛ የሜዳ ላይ ድርጊት ማመኑን ተከትሎ በእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር ተጥሎበት የነበረው የሶስት ጨዋታ ቅጣት እንዲፀና ሆኗል።

ያንግ ቅዳሜ ማንችስተር ዩናይትድ 0ለ0 በሆነ ውጤት ባጠናቀቀበት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የሳውዛምፕተኑን ቱሳን ታዲችን በክርኑ ሆዱ ላይ ሲመታ ታይቷል።

የ32 ዓመቱ ተጫዋች በእግርኳስ ማህበሩ የቀረበበትን ክስ ቢቀበልም፣ ነገር ግን የጨዋታ እገዳው ጊዜ በዝቷል በሚል ቢከራከርም በእግርኳስ ማህበሩ የስነስርዓት ኮሚቴ አቤቱታው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

“አሽሊ ያንግ በማንችስተር ዩናይትድ ቀጣይ ሶስት ጨዋታዎች ላይ እንዳይሰለፍ ታግዷል።” ሲል እግርኳስ ማህበሩ በመግለጫው ገልፅዋል።

ይህን ተከትሎም የዩናይትዱ አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ ከአሽሊ ያንግ በተጨማሪ ተመላላሽ ተጫዋቹ አንቶኒዮ ቫሌንሺያ፣ የክለቡ አምበል ማይክል ካሪክ፣ ክሪስ ስሞሊንግ፣ ኤሪክ ቤሊ፣ ማሩዋን ፌላይኒ፣ ዝላታን ኢብራሂሞቪችና ሮሜሉ ሉካኩ በጉዳት ምክኒያት በቡድናቸው ውስጥ የማይኖሩ ተጫዋች ይሆናሉ።

ዩናይትድ በቀጣይ ሶስት ጨዋታዎቹ የፊታችን አርብ በኤፍኤ ዋንጫ ደርቢ ካውንቲን ከመግጠማቸው በፊት ዛሬ (ሰኞ) ከኤቨርተን ጋር ሲጫወቱ እ.ኤ.አ. ጥር 15 ደግሞ ስቶክን የሚገጥሙ ይሆናል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእግርኳስ ማህበሩ ዋትፎርድ ስዋንሲን 2ለ1 በረታበት የቪካሬጅ ሮዱ ጨዋታ የስዋንሲ ሲቲው ተጫዋች ካይል ናውተን የዋትፎርዱን ስቴፋኖ ኦካካን በመራገጡ የሶስት ጨዋታዎች የእገዳ ቅጣት አስተላልፎበታል።

Advertisements