​ሁዋን ማታ / ፍሬ ማፍራት የጀመረው ትኩረት ሳቢው የበጎ ተግባር ተምሳሌቱ ቀያይ ሴይጣን የእግር ኳሱ አለም አበይት የለውጥ ዘመቻ 


 

ደቃቃው ስፔናዊ በእግር ኳስ ውስጥ ካሉና በስፖርቱ መድረክ ያላቸውን እውቅና ለበጎ ተግባር ማዋል ከሚፈልጉ ጥቂት ከዋክብት አንዱ ነው። ቀጣዩ የሚኪያስ በቀለ ዘገባም የቀያይ ሴጣኖቹ ብልህ አማካኝ በሳለፍነው ክረምት ከጀመረው የበጎ ተግባር ጀምሮ ወደኋላ በምልሰት እስከ ልጅነት ጊዜው ድረስ የነበረውን ስኬትና ፈተና በማስመልከት የሰጠውን ቃል ከተያያዥ ጉዳዮች ጋር አስተሳስሮ እንደሚከተለው በዝርዝር ይነግረናል።


“ለእኔ ጥሩ እግር ኳስ ማለት ምን ያህል ብቃት አሳየህ ወይም ምን ያህል ተጫዋቾችን በልጠህ ተገኘህ ማለት አይደለም።” ሲል ስፔናዊው ብልህ አማካኝ ንግግሩን ጀመረ።

ማታ ንግግሩን በመቀጠል “ያ ማለት ኳስ በቁጥጥርህ ስር ሳለ ምን ያህል ትክክለኛ ውሳኔ አሳለፍክ ማለት ነው። ኢኔሽታና ዣቪን የመሰሉ መቶ በመቶ ትክክለኛ ውሳኔ የሚያሳልፉ ተጫዋቾች አሉ። ነገርግን ሌሎች ጥሩ የእንግሊዝ ምሳሌ ተጫዋቾችም አሉ። ስኮልሰ፣ ላምፓርድ እና ጄራርድ ከተሳሳተ ውሳኔ ይልቅ ብዙ ትክክለኛ ውሳኔን የሚያሳልፉ ናቸው።

“ብዙ የአካል ብቃት ጥራት ያላቸው ተጫዋቾችን ትመለከታለህ። እነሱ ፈጣንና ጠንካራ ናቸው። ነገርግን ትክክለኛ ውሳኔን አይወስኑም። ለእኔ አስፈላጊው ነገር በዚህን ወቅት ጨዋታው የሚጠይቅህን ነገር መፈፀም ነው። ምንም እንኳን ስለመከላከል ሀላፊነት እና ቅርፅ ብትጨነቅም አንዴ ሜዳ ላይ ከገባህ በኋላ አዕምሮህ ንፁህ መሆን አለበት።” በማለት የኦልትራፎርዱ ኮከብ ከአንድ የእግር ኳስ ተጫዋች የሚጠበቅበትን ሀላፊነት በዝርዝር ያስረዳል።

ይህ እግር ኳሰኞች ከሜዳ ውጪ ሊያደርጉት የሚችሉትን ተግባራት የሚገልፀው የነፃ አስተሳሰብና ርህራሄ የማሳየት አቅም ማታ ባሳለፍነው ነሀሴ የጀመረውን ወሳኝ ፕሮጀክት በሚገባ ይገልፀዋል። የአለም እና የአውሮፓ ዋንጫን እንዲሁም ደግሞ የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ያነሳው ስፔናዊ ኮከብ እና ሌሎች እግር ኳሰኞች ከገቢያቸው ላይ አንድ በመቶ መዋጮን ለእርዳታ መስጠታቸው በአለም ዙሪያ የሚገኙ የእግር ኳስ እርዳታ ስራዎችን ለማገዝ ትልቅ ጥቅም እንደሚኖረውም ይገመታል።

የማታ ትልቁ ህልሙ በቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ሀይል ያለው የእግር ኳስ ኢንዱስትሪ አንድ በመቶ አቅሙን ለእርዳታ ሲያውል ማየት ነው። ስፔናዊው አማካኝ ለጉዳዩ አፅንኦት በመስጠት”ይህ ነገር እኔን የተመለከተ አይደለም። የሆነ ሰው ጀመረውና እኔም አረኩት። ነገርግን ብዙዎቻችን ለፕሮጀክቱ ስኬት ታማኝ እንሆናለን። የእቅዱ የመጨረሻ ግብ ሚዲያና ደጋፊን ጨምሮ እያንዳንዱ ከእግር ኳስ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት በተለያየ መንገድ እገዛ እንዲያደርጉ ነው። 

“እዚህ ላይ ምርጡ ነገር ከተጫዋቾች መጀመር ነው። ምክንያቱም እኛ ትልቅ ትኩረት እንስባለን። ከገቢያችን ላይ የአንድ በመቶ እገዛ ስለማድረግ የምናወራው ሌሎቹን ለማነሳሳት የሚቀል በመሆኑ ነው። የእኔ አንድ በመቶ እገዛ ብዙ ትርጉም የሚሰጥ አይደለም። ነገርግን አንድ ቀን የመላው ፕሮፌሽናል እግር ኳስን ገቢ አንድ በመቶ የመስጠት ደረጃ ላይ እንደርሳለን። ሰዎች በገንዘብ ደረጃ እገዛ ለማድረግ ጥሩ ሁኔታ ላይ ባይገኙ እንኳን አላማውን በማሰራጨት እገዛ ማድረግ ይችላሉ።”

ማታ እገዛ ለማድረግ የተነሳሳው እግር ኳስ ህብረተሰቡን ለመቀየር እንደሚጠቅም በማለም ከሆነ የእሱ ተግባር በጣም ግላዊ እንደሆነ ማሳያ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘም ከአስር ወራት በፊት ወንድ አያቱን በሞት ማጣቱ እድለኛ ያልሆኑ ህይወቶችን ለማሻሻል ጥረት እንዲያደርግ መነሳሳት እንደፈጠረለት ስምንት ቁጥር ለባሹ ቀያይ ሴጣን ያስታውሳል። “በጣም አሳዛኝ ቀን ነበር።” በማለት የአያቱ ሞት የፈጠረበትን ሁኔታ ያስረዳል።

“እሱ ወደልምምድ ሜዳ ይወስደኝ ሁሉንም ጨዋታዎቼንም ይመለከት ነበር። እግር ኳስ ፍላጎቱ የነበረ ሲሆን በእግር ኳስ ውስጥ ያለ የልጅ ልጅ ስለነበረው በጣም ደስተኛ ነበር። በወቅቱ የአለም ዋንጫ ፍፃሜን (ስፔን ድል ያደረገችበትን የ 2010 ውድድር) እና አንዳንድ የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎችን ለመከታተል ይመጣል።

“በእውነቱ ከሆነ ጥሩ ስጫወትና ዋንጫ ሳነሳ ለእራሴ ደስታ ይሰማኛል። ነገርግን ከእኔ በላይ ለቤተሰቤ ደስተኛ እሆናለሁ። ምክንያቱም ነገሮች በጥሩ መንገድ ሳይጓዙ ሲቀሩ ምን ያህል እንደሚጎዱ አውቃለሁ። እነሱ ከእኔ በላይ በነገሮች ይጎዳሉ። ነገሮች በጥሩ መንገድ ሲሄዱ ደግሞ ከእኔ በላይ ይደሰታሉ።

“እሱ ከመሞቱ አንድ ቀን በፊት ከሴንት ኢትየን ጋር ተጫወትንና ጨዋታውን ያሸነፍንበትን ግብ ለማኪቴሪያን ያቀበልኩት እኔ ነበርኩ። ዕለቱ ሀሙስ ሲሆን ከካፒታል ዋንጫ ፍፃሜ በኋላ እሁድ ምሽት ላይ እንደማየው ተስፋ አድርጌ ነበር። ነገርግን እሱ አርብ ዕለት በመሞቱ በማግስቱ ቅዳሜ ወደስፔን ሄድኩና ለፍፃሜው ተመለስኩ። ከሴንት ኢቴን ጨዋታ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ አንዴ አውርተናል።

“በወቅቱ ደክሞ የነበረ ቢሆንም አሪፍ የግብ ኳስ እንዳቀበልኩ ነግሮኛል። በህይወት ዘመኔ ሙሉ ሳስታውሰው የምኖረው ኳስ ይመስለኛል። እሱ በእግር ኳስ የብዙ ሰዎችን ደስታ ለመፍጠር እንዳስብ በማድረግ ለእኔ በጣም ወሳኝ ሰው ነው።

“ሌሎችን ለመርዳት የራሴን የእርዳታ ተቋም ማቋቋም አስብ ነበር። ነገርግን እህቴም ታበረታታኝ ነበር። እሷ አሁን በአይስላንድ ስትገኝ ትልቅ ስብዕናና ኑሮ አላት። እሷ ተጓዥ፣ ነፃ መንፈስ ያላትና አናኗራን የምወድላት ናት። ስለዚህ ቤተሰቦቼ እግር ኳስን በተለየ መንገድ እንድመለከት ትክክለኛውን አስተሳሰብ ፈጥረውልኛል። ከዛም ከጀርገን ግሪስቤክ (የስትሪት ፉትቦል መስራችና የአሁኑ የኮመን ጎል እርዳታ ድርጅት አስተዳዳሪ) ጋር ተገናኘሁ።

“ጀርገን ለ 15 አመታት በእግር ኳስ ውስጥ የሰራና ስራውን የጀመረው በ 1994 አለም ዋንጫ ኤስኮባር እራሱ ላይ ግብ ካስቆጠረና በኋላ ላይም ወደ ሀገሩ ኮሎምቢያ ሲመለስ ከተገደለ በኋላ ነው። ከዛም እግር ኳስን በጋራ በማምጣት ሌሎችን እንዲረዳ የሚል ሀሳብ አመጣን። ሀሳቡ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንዳይሆን ነው። አላማ አድርገን የተሰራነው የእግር ኳስ ቅርፅ ውስጥ የአንድ በመቶ እርዳታ እንዲኖር ነው።

“ሀሳቡን እውን ለማድረግ ቀላል አልነበረም። ነገርግን የጀርገን ልምድ እና እኔ ደግሞ እምነትና የእግር ኳስ አቅም ትልቅ እንደሆነ መልዕክት ማስተላለፊያ መንገዱ ነበረኝ። በየሄድኩበት ቦታ ሁላ ልጆች ኳስ ሲጫወቱ እመለከታለሁ። ሜዳው ሳር ባይኖረው እንኳን በሹራብ ልብስ በተሰራ ግብ በመጠቀም የሚደረግ ጨዋታን በመመልከት ሰዎች ለእግር ኳስ ያላቸውን ፍቅር ትመለከታለህ።” በማለት ማታ የእግር ኳስን ተፅዕኖ ያስረዳል።

እስከ አሁን ድረስ ማት ሀምልስ፣ ጆርጂዮ ቺሊኒ፣ ሰርጅ ግናብሪ፣ ዴኒስ ኦጎ፣ አሌክስ ቦርስኪው እና ሁለት የአሜሪካ ሴት ተጫዋቾችን ጨምሮ ሰባት ሌሎች ተጫዋቾች ማታን ተቀላቅለው የደሞወዛቸውን አንድ በመቶ ለእርዳታ ድርጅቱ ለመለገስ ተስማምተዋል። 

ማታም “ደረጃ በደረጃ ይፋ የሚሆኑና የሚቀላቀሉን ተጫዋቾች አሉ። ይፋ የማድረጉን ነገር ጊዜያዊ ሳይሆን ረጅም ጊዜ የሚቆይ ለማድረግ ፍላጎት አለኝ። እኛ አለም አቀፍ ፕሮጀክት እንደሆነ ለማሳየት ከአምስት ክፍለ አህጉራት ተጫዋቾች አሉን።

“ከጋዜጠኞች፣ ከደጋፊዎች፣ ከቡድን አጋሮቼ እና ሌሎች ፕሮፌሽናሎች ጀምሮ በሁሉም ዘንድ ያለው ምላሽ ትልቅ ነው። አንዳንድ ጊዜ እኛ እግር ኳስ ተጫዋቾች ግፊት እንፈልጋለን። ነገርግን ስንነግራቸው ነገሩን ይረዱናል። የእኛ ግብ ነገሩን ቀላል፣ ውጤታማ እና ግልፅ ማድረግ ነው። ከአንዳንድ የእግር ኳስ ውሳኔ አሳላፊ ሰዎች ጋርም በንግግር ደረጃ ቃል ተግባብተናል። እነሱ ከእኛ ጋር ይህንን ለመስራት እንደሚቀላቀሉ ስሜት አለኝ።” ሲል ሁኔታው የሰጠውን እርካታ ይገልፃል። 

ነገሩ አመታትን ቢፈጅም የያዙት አላማ እንደሚሳካ ማታ እምነት ይኖረው ይሆን? “ምንም ያህል ረጅም ጊዜ ቢወስድ ችግር የለውም። በቅርቡ ወይም ወደፊት ይሳካል።” ሲል የኦልትራፎርዱ ስምንት ቁጥር እምነቱን ያስቀምጣል።

ነገርግን ማታ እየሰራ ያለውን ነገር ከሞውሪንሆ ጋር እስካሁን አልተነጋገረበትም። “የተወሰኑ ጊዜ ከተለመደው ለጨዋታ መዘጋጀት መርሀ ግብር በመውጣት እንደዚህ አይነት ነገሮችን ማውራት አስቸጋሪ ነው። ስለዚህም የውድድር ዘመኑ እረፍት ላይ ርዕስ የሚሆን ነገር ነው። ከየትኛውም ሰው ጋር ለመግባባት አስፈላጊው ነገር ትክክለኛውን ወቅት ማግኘት ብቻ ነው።” ሲል ለዩናይትዱ አለቃ እቅዱን ለመናገር ጊዜ እየጠበቀ መሆኑን ይገልፃል።

በቼልሲ ቤት ማታ በሞውሪንሆ ተገፍቶ ከነበረበት ጊዜ በኋላ ነገሮች በአስደናቂ መልኩ ነገሮች ተቀያይረዋል። ሞውሪንሆ በቅርቡ ሽግግር ላይ ያለውን ቡድናቸውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ “የማታን አዕምሮ እፈልገዋለሁ።” በማለት በስፔናዊው ዙሪያ ትልቅ የአቋም ለውጥ ማድረጋቸውን ይበልጥ ያሳየ መግለጫን መስጠታቸው ይታወሳል። 

ማታ በበኩሉ “እኔ ወደዚህ ከመጣሁ ጀምሮ (ጥር 2014) እንደ ቡድን በአሁን ሰአት በተሻለ የራስ መተማመን መንፈስ እና በጥንካሬ እየተጫወትን እንገኛለን። ከሰር አሌክስ በኋላ ሶስት አሰልጣኞችና 15 አዳዲስ ተጫዋቾች የመጡበት አስቸጋሪ ጊዜ ነበር። ነገርግን ወደምንፈልገው ወጥነት ለመግባት ተቃርበናል። 

“የዩናይትድ ደጋፊዎች አስደሳች እግር ኳስ እንደሚፈልጉ የምናውቅ ሲሆን በተለይ በኦልትራፎርድ ብዙ ግቦችን አስቆጥረናል። በግል ደረጃም እኔ በጣም በጥሩ ወቅት ላይ ነኝ። አሁን በእርግጥም በእግር ኳስ ህይወቴ ሁለተኛ ክፍል በሆነው 29ኛ አመቴ ላይ እንደምገኝ ግልፅ ነው። ነገርግን ላበረክተው የምችለው ብዙ ጥሩ ጥሩ ነገሮች እንዳሉ ይሰማኛል።” ይላል።

አሁን ማታ ሙሉ ለሙሉ በተለየ ሁኔታ ውስጥ ከሞውሪንሆ ጋር እየሰራ ከመሆኑ አንፃር አሰልጣኙን ምን ይገልፃቸዋል? “ለማሸነፍ ያለው ረሀብ” ይላል ማታ። “የሚፈልገውን በተመለከተ ንፁህ ምስል አለው። ሰዎች ላይስማሙ ቢችሉም እሱ ግን ነገሮች እንዴት መሰራት እንዳለባቸው ያውቃል። እሱ ጠንካራ ስብዕና አለው። ነገርግን እሱን ለማድነቅ እሱን ማወቅ አለብህ። እሱ ወደ ዩናይትድ ከመጣ ወዲህ በጣም የተቀራረብን ሲሆን መፎካከርና ትልልቅ ጨዋታዎችን ማሸነፍን እንደሚፈልግ አውቃለሁ።”

ማታ ለሁለት አመታት የክለቡ የአመቱ ምርጥ ተጫዋችነት ክብርን በቼልሲ ቤት ካገኘ በኋላ በሞውሪንሆ ስር ያሳለፈውን አስቸጋሪ ጊዜም በሚገባ ያስታውሰዋል። “እሱ የተለየ የአጨዋወት መንገድ ለመከተል በጣም ፍላጎት የነበረው ሲሆን ነገሩም ጥሩ የሚባል ነው። 

“ነገርግን የቻምፒዮንስ ሊግ፣ የኢሮፓ ሊግን ካሸነፍኩና የአመቱ ኮከብ ተጫዋች ተብዬ ከተመረጥኩ በኋላ የተከሰተ በመሆኑ ለእኔ አስቸጋሪ ነበር። የእኛ የመጨረሻ ግብ የመወደድ እና የመፈለግ ስሜትን ማግኘት በመሆኑ ነገሩ የስነልቦና ፈተና ነበር። ነፃ አልነበርኩም። ነገርግን እንደዛ አይነት ወቅት ሲገጥምህ ዝም ብለህ በቃ ኳሱን አንሳና ተጫወት። ሁኔታው በእዛ መልክ እንዲጓዝ አድርግ።” በማለት አስቸጋሪውን ጊዜ ያለፈበትን መንገድ ባማሩ ቃላት ለመግለፅ ሞክሯል። 

በወቅቱ በስታምፎርድ ብሪጅ ፍሰቱን ከማጣቱ ጋር በተያያዘስ ማታ ሁኔታውን ከሞውሪንሆ ጋር አውርቶበት ያውቅ ይሆን?  “አይ! ስለነገሩ ምንም አላወራንም። መቼም አልተከራከርንም። ነገርግን ለእኔ ከጊዜ ወደጊዜ ሁኔታው አስቸጋሪ እየሆነ መጣ። 

“ከዛም ለማንኛውም ሰው አሪፍ አማራጭ የሆነውን ማንችስተር ዩናይትድን ተቀላቀልኩ። አሁን ለእኔ በድጋሚ አንድ ሆነን ማየቴ አሪፍ ነገር ነው። ብዙ ሰዎች በእኛ መሀከል ግላዊ ችግር እንዳለ ይጠረጥራሉ። ነገርግን ጉዳዩ እንደዛ አይደለም። ለቡድኑ ወሳኝ እንደሆንኩ እየተሰማኝ ሲሆን በሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጪ ከጆሴ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ።” 

ሌላኛው ነገር ደግሞ ከ 16 ወራት በፊት ሞውሪንሆ ወደ ኦልትራፎርድ እንደሚመጡ ሲሰማ የማታ መንፈስ መውረዱ የማይቀር የነበር መሆኑ ላይ ነው። “ያ ሌላ ፈተና ነበር። ነገርግን የእኔ ፕሮፌሽናሊዝም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አልነበረም። 

“እሱን እንደሚወደው አውቃለሁ። የእኔ የአጨዋወት መንገድ ለቡድናችን ጥሩ ነገር እንደሚጨምር አሰብኩ። ስለዚህም ‘እሺ! እስቲ በድጋሚ እንሞክረው። እሱ ከእኔ የሚፈልገውን ለቡድኔ ላበርክት።’ የሚል እምነት አሳደርኩ።” ሲል ማታ ጉዳዩን ያስረዳል።

በወቅቱ ዩናይትድ በሞውሪንሆ ስር ባደረገው የመጀመሪያ የፉክክር ጨዋታ ማታ በኮሚኒቲ ሺልድ ዋንጫ ተቀይሮ ወደ ሜዳ እንዲገባ ተደረገ። “ነገርግን ምንም አልመሰለኝም። እኔን ያስጨነቀኝ የተወሰኑ ሰዎች በወቅቱ ሁኔታውን አግዝፈው ለመመልከት ጥረት ማድረጋቸው ነው። እሱ እንዴት እንዳሰበ ማወቅ አለብህ። እኔ አውቃለሁ።

“ጨዋታው ስድስት ተቀያሪዎችን የያዘበት ነበር። ወደሜዳ (በ 63ኛው ደቂቃ) ገብቻለሁ። ጨዋታውን ያሸነፍን ሲሆን በመጨረሻው ሁለት ደቂቃዎች ደግሞ ሞውሪንሆ ‘አንድ ተጨማሪ ተጫዋች የመቀየር እድል (ማኪቴሪያን) አለኝ። ለምን አልጠቀምበትም’ በማለት አሰበ። ረጅሙን ሰው የተጠቀመበት ምክንያት እሱ በተግባር የሚያምን በመሆኑ ነው። ሁኔታውን ግላዊ አድርጌ አልተመለኩትም።” ይላል።

የማታ አባት በማንችስተር ከተማ “ታፒኦ እና ወይን” የተሰኘ የስፔን ሬስቶራንት ስላላቸው እሱና ጋርዲዮላ የስፔን ተወዳጅ ምግብ ታፓስ እየተመገቡ ተጨዋውተዋል ብሎ ማሰቡ ተገቢ ይመስላል። “እሱ ወደዛ ይሄዳል” ሲልም ስፔናዊው ኮከብ በኢትሀዱ አለቃ ዙሪያ ምሰክርነቱን ይሰጣል።

ማታ ንግግሩን ቀጠል ያረግናም “ሞውሪንሆ እንዲሁም የተወሰኑ የቡድን አጋሮቼና የሲቲ ተጫዋቾችም ወደዛ ይሄዳሉ። በምግብ ቤቱ ሚካኤል አርቴታን የመሰሉ አንዳንድ የፔፕ (ጋርዲዮላ) ምክትል አሰልጣኞችን እመለከታለሁ። ነገርግን ፈፅሞ ከፔፕ ጋር ቀርቤ አላውቅም።” ይላል።

ማታ የካታሎንያ ግዛት ነፃነት አቀንቃኞች በፖሊስ የደረሰባቸውን ትንኮሳ በተመለከተ ርዕስ ሲነሳ በዝርዝር ለማውራት እምቢታውን ያሳየ ሲሆን በጣም ጭፍግግ ባለ ስሜት ውስጥም ገባ። “ግጭቶችን መመልከት ጥሩ አይደለም። እኔ አሳዛኝና አስፈሪ ስሜት ነበረኝ። ነገርግን ሁኔታው ያለምንም ብጥብጥ በጥሩ ሁኔታ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ። በንግግርና በሁለቱ አካላት መልካም ፈቃድ የሆነ መፍትሔ ላይ እንደሚደረስ ተስፋ አለኝ።

ከመገንጠል ጥያቄው ውጥንቅጥ ጋር በተያያዘም ባርሴሎና በዝግ ስታዲየም ላስ ፓልማስን ከገጠመበት ጨዋታ ወዲህ ጄራርድ ፒኪዌን አናግሮት ይሆን? “አይ! ነገርግን እግር ኳስ በስፔንና በካታሎንያ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ከዚህ በተሻለ አንድ የማድረግ አቅም አለው።” ሲል ማታ ሀገሩ የካታሎንያን ችግር በሰላም መፈታት ያለበትን መሆኑን በተስፈኛነት መንፈስ ውስጥ ሆኖ የሚሰማውን ያስረዳል።

ብልሁ አማካኝ ባለፉት ሁለት የአለም ዋንጫዎች በተጫወተላት ሀገሩ የ 2018 ስብስብ ውስጥ እንደሚካተትም ተስፋ አድርጓል። “አዲስ ትውልድ፣ አዲስ አሰልጣኝና አዲስ ጥራት ያለው ነው። ነገርግን እራሴን የማየው የዛ አካል አድርጌ ነው። እኔ በትልቅ ክለብ ውስጥ ከሳምንት ሳምንት በጥሩ ብቃት የምጫወት ነኝ። ስለዚህም በራሴ ላይ እምነት አለኝ።” ይላል።

ዩናይትድ ከሪያል ማድሪድና ባርሴሎና ጋር ለመፎካከር ዝግጁ ነውን? ስትሉት ደግሞ “በቻምፒዮንስ ሊግ ነገሩ የተለየ ነው። ምክንያቱም በጥሎ ማለፉ በፕሪምየር ሊግ ላይ የሚጠበቅብህን ወጥነት ማሳየት አያስፈልግም። የሚያስፈልግህ በሁለቱ ጨዋታዎች (በደርሶ መልሱ) ጥሩ መሆን ብቻ ነው። 

“በቼልሲ (በሮበርቶ ዲማቲዮ ጊዜያዊ አሰልጣኝነት) ቤት ከባርሴሎና ጋር በግማሽ ፍፃሜ መጫወቴን አስታውሳለሁ። ሌላኛው ግማሽ ፍፃሜ ባየርን እና ሪያል የተገናኙበት ነበር። ሁሉም ሰው የሚያስበው የነበረው ፍፃሜው ሪያል ከ ባርሴሎና እንደሚሆን ነበር። ነገርግን በፍፃሜው ቼልሲ ባየርን አሸነፈ። እኛ በወቅቱ ግምት አልተሰጠንም ነበር።

“በቻምፒዮንስ ሊጉ መጠነኛ እድል ያስፈልግሀል። ነገርግን የማቲች፣ የሉካኩ እና ቪክተር ሊንድሎፍ መምጣት ወሳኝ ነው። ማቲች ታላቅ ሲሆን በኳስ ላይ ያለው የሰውነት አቋምና ጥራት ትልቅ እገዛ አድርጎለታል። ቪክቶር በመከላከሉ ላይ ወጣትነትና ጥራትን ጨምሯል። ሉካኩ ብዙ ግቦችን እያስቆጠረ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ኢብራሂሞቪች ሲጨመርበት የተረጋጋ ስብስብ ይኖረናል። በመልበሻ ቤት ጥሩ ሰዎች እና ጥሩ አስተሳሰብ አለ። ይህን ሁኔታ ልዩ ወደሆነ ነገር እንቀይረው።” 

ማታ ከብዙ ትልልቅ ተጫዋቾች ጋር በጋራ ተጫውቷል። ነገርግን “አብሬ ከተጫወትኳቸው እግር ኳሰኞች ምርጡ የምለው ያንያህል ፈጣን፣ ጠንካራና ረጅም ያልሆነውን ኢኔሽታን ነው። ለስፔን በምንጫወትበት ወቅት ሁሌም ኳስን የሚያሻግርልህ በትክክለኛው ወቅት ነው። 

“እሱ ሁሌም የተሻለ ያደርግሀል። ከዚዳን ጋር ተመሳሳይ ነው። የእሱ ግላዊ ክህሎት አስገራሚ ነው። የሪያል ማድሪድ ተጠባባቂ ስብስብ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት ከዚዳን፣ ሮናልዶ፣ ቤካምና ራውል ጋር ልምምድ እሰራ ነበር። ሁሉም ትልልቅ ተጫዋቾች ነበሩ። ዚዳን ግን እያንዳንዱን የተሻለ ያደርግ ነበር።” ይላል።

በመጨረሻም ማታ ንግግሩን በመቀጠል “በስፔን ከጥሩ ቤተሰብ በመወለዴ እድለኛ ነኝ። ነገርግን አንዳንድ የቡድን አጋሮቼ ተመሳሳይ ደረጃ ላይ የደረሱት ከአስቸጋሪ ህይወት በመነሳት ነው። እግር ኳስ እኩል ስለሆነ ከየትም ብትመጣ ችግር የለውም። 

“ኤሪክ ቤሊና ማርከስ ሮሆ ከእኔ ሙሉ ለሙሉ ተቃራኒ ከሆነ የህይወት መነሻ የመጡ ናቸው። አንዱ ከኮትዲቯር አንዱ ደግሞ ከአርጀንቲና የተገኙ ናቸው። እነሱ በኢኮኖሚ ደከም ካለ ቤተሰብ የተገኙ ናቸው። ከጓደኞቻቸው ጋር ኳስ ይጫወቱ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ በማንችስተር ዩናይትድ ይገኛሉ። ይሄ ትልቅ ቦታ ለመድረስ ላልቻሉ ትልቅ ምሳሌ ነው።” ሲል ንግግሩን ቋጨ።

ከቃለ-ምልልሱ መጠናቀቅ በኋላ ማታ ስልኩ ጮኸ። ደዋዩ የቡድን አጋሩ አንደር ሄሬራ ሲሆን ከውጭ ሆኖ ወደከሰአት ልምምድ እንዲሄዱ ከተለመደው ሰአት ቀደም ብሎ ማታን እየጠበቀ ነበር። ማታ በሁኔታው በመጠኑ ጭንቀት ውስጥ ገባ።

ማታ ለልምምድ ለመዘግየት ያለው ፕሮፌሽናልነት ባይፈቅድለትም ለፎቶ መነሳት ስነስርዓቱ መጠነኛ ጊዜ መስጠት እንዳለበት ተረድቷል። “ብዙ ሰአት ጠብቀሀል።” ሲል ማታ ለፎቶግራፍ አንሺው ተናገረ። ከዛም ለሄሬራ ሁኔታውን ገልፆ ለፎቶው ትኩረት ለመስጠት መጠነኛ ጊዜ እንዲሰጠው ጠየቀ።

በሁኔታው በማታ ዙሪያ የነበረው እያንዳንዱ ሰው ደስተኛ ሆነ። ልዩ የሆነ የእርዳታ ተግባርን የጀመረው ስፔናዊው አማካኝም የመጨረሻ ተጨማሪ መልዕክቱን ለማስተላለፍ ክፍተት አገኘ። 

“አንዳንድ ሰዎች እግር ኳስ ተጫዋቾችን ለምን ራስ ወዳድ አድርገው እንደሚያስቡ ተረድቻለሁ። ነገርግን ሰዎች እግር ኳስን የሚያስቡት አውርደው ነው። ጥሩ ነገሮች ከእሱ ሲወጡ ፍትሀዊ ስፖርት ይሆናል። ተሰጥኦውና ፍላጎቱ ካለህ ከየትም ብትመጣ ትልቅ ነገር ማድረግ ትችላለህ። 

“በእዛ መልክ እግር ኳስም እንደ ቡጢ (ቦክስ) ስፖርት ተመሳሳይ ነው። ለብዙ ሰዎች ተስፋን ይሰጣል። እግር ኳስ ህይወትን ለመቀየር የሚችልበት መንገድ አስገራሚ ነው።” ሲል እቅዱ ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ ያስገነዘበበትን ንግግር አደረገ። 

ማታ ይሄን ቃሉን ከሰጠ ከአንድ ወር በላይ አስቆጥሯል። ነገርግን እቅዱ ፍሬ ማፍራት መጀመሩን  እና ትልቅ ትኩረት ማግኘቱን ባሳበቀ መልኩ የእንግሊዙ ተከባሪና ታማኝ ጋዜጣ ‘ዘጋርዲያን’ በስፖርቱ አለም ምሳሌያዊ የሚሆን ስራ ለሰሩ የስፖርቱ አለም ሰዎች የሚሰጠውን የአመቱ በጎ ሰው ሽልማትን በትናንትናው ዕለት ማግኘት ችሏል። ስፔናዊው ደቃቃም የእርዳታ ተግባሩን በጀመረ ከአምስት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥም በ 17 ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ሌሎች 35 የእግር ኳሱ አለም ሰዎች 1 በመቶ ገቢያቸውን ለእርዳታ ድርጅቱ ማበርከት ጀምረዋል። 

እድሜ ይስጠን እንጂ በቀጣይ ደግሞ እልፍ አእላፍ የእግር ኳሱ አለም ፈርጦች የማታን አበይት የእግር ኳሱ አለም አበይት የበጎ ተግባር ዘመቻ መቀላቀላቸው የማይቀር ይመስላል። 

የህዳግ ማስታወሻ : ይህ ፅሁፍ በኢትዮአዲስ ስፖርት የህዳር ወር ወርሀዊ መፅሄት ላይ የወጣና ጥቂት ማሻሻያ ተደርጎበት የቀረበ ነው።

Advertisements