የቪላሪያሉ አጥቂ ሲድሪክ ባካምቡ ወደ ቻይና ሱፐር ሊግ እንደሚያቀና አሰልጣኙ አሳወቁ

የዲሞክራቲክ ኮንጎው እንዲሁም የቪላሪያሉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ የሆነው ሲድሪክ ባካምቡ በአስገራሚ ሁኔታ ወደ ቻይናው ሱፐርሊግ እንደሚቀላቀል የክለቡ አሰልጣኝ አረጋገጡ።

በፈረንጆቹ አዲሱ አመት ጥር 1 ላይ የተከፈተው የቻይና ሱፐርሊግ የዝውውር መስኮት የመጀመሪያውን ስም ያለው ተጫዋች ለማዘዋወር መቃረባቸው ታውቋል።

በቪላሪያል ድንቅ ቆይታ እያደረገ የሚገኘው ባካምቡ ለ ቤጂንግ ግዋን ለሚባል ክለብ ዝውውሩን በቀጣዮቹ ሰአታት እንደሚያጠናቅቅ ይጠበቃል።

የተጫዋቹ ያልታሰበ ዝውውር እውነታውን ቢያጠራጠርም የክለቡ አሰልጣኝ የሆኑት ሀቭየር ካሌሀ ማረጋገጫ መስጠታቸው ተከትሎ ዝውውሩ ሳይጠናቀቅ አስገራሚ አድርጎታል።

ለሙንዶ ዲፖርቲቮ የተናገሩት ሀቭየር ካሌሀ “ባካምቡ ወደ ቻይና ሱፐርሊግ የሚያደርገው ዝውውር ተጠናቋል ማለት ይቻላል።ለኛ ጥሩ ነገር አይደለም ነገርግን በዝውውሩ የተሳተፉት በሙሉ ተጠቃሚ ያደርጋል።የውል ማፍረሻውን የሚከፍል ክለብ ተገኝቷል፣ስለዚህ እኛ ብዙ የሰራነው ነገር የለም።”ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ዘገባዎች ከሆነ የቻይናው ክለብ ተጫዋቹን ለማዘዋወር 35.5 ሚሊየን ፓውንድ የውል ማፍረሻ እንደሚከፍል ነው።

ባካምቡ 2015 ላይ ከቱርኩ ቡርሳስፖር በ 6.5 ሚሊየን ፓውንድ ከተዛወረ በኋላ ለቪላሪያል 48 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።

በዘንድሮው የላሊጋ ውድድርም ዘጠኝ ጎል በማስቆጠር ለክለቡ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን በሚገባ ማስመስከር ችሏል።

ቪላሪያል በላሊጋው ከባርሴሎና በ 18 ነጥብ አንሶ በስድስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በዩሮፓ ሊግ የጥሎማለፍ ጨዋታ ደግሞ ከሊዮን ጋር መደልደሉ ይታወቃል።

Advertisements