ሊቨርፑል ከ ኤቨርተን | የኤፍኤ ዋንጫ 3ኛው ዙር ጨዋታ ቅድመ ቅኝት

ሊቨርፑል ከ ኤቨርተን

አርብ ታህሳስ 27 |
የኤፍኤ ዋንጫ | አንፊልድ
ምሽት 4፡45 


የዚህ የውድድር ዘመን የኤመራትስ ኤፍኤ ዋንጫ ሶስተኛ ዙር አርብ ምሽት ሁለቱን የሊቨርፑል ከተማ ክለቦች በመርሲሳይድ ደርቢ በአንፊልድ ስታዲየም ያገናኛል።

ሊቨርፑል ይህን ጨዋታ የሚያደረገው ለመጨረሻ ጊዜ ያደረጋቸውን ያለፉት 16 ጨዋታዎችን ሳይሸነፍ እና ለመጨረሻ ጊዜ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ደግሞ አምስቱን በመርታት ይሆናል።

የየርገን ክሎፑ ቡድን 2018 ዓመትን በአስገራሚ ሁኔታ በመጨረሻ ሰዓት በተቆጠረ ግብ በርንሌይን 2ለ1 በማሸነፍ ጀምሯል።

በአንፃሩ ኤቨርተኖች ለመጨረሻ ጊዜ ያደረጓቸውን አራት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ባለመቻላቸው በዚህ ጨዋታ የተሰጣቸው ግምት አበስተኛ ነው።

ከዚህም በላይ ግን ቶፊሶቹ ለመጨረሻ ጊዜ ባደረጓቸው 15 የመርሲ ሳይድ ደርቢ ጨዋታዎች ላይ ማሸነፍ አልቻሉም። ከ1999 ወዲህም በየትኛውም ውድድር ላይ በአንፊልድ ድል ቀንቷቸው አያውቅም።

የሳም አላርዳይሱ ቡድን የፈረንጆቹን አዲስ ዓመት በማንችስተር ዩናይትድ በሜዳው 2ለ0 በመሸነፍ ጀምሯል።

ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ወር በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጉት ጨዋታም ሊቨርፑል በአንፊልድ ለማሸነፍ ዕድለኛ ባልነበረበት ጨዋታ 1ለ1 በሆነ ውጤት አጠናቀዋል።

ኤቨርተኖች በኤፍኤ ዋንጫ ውድድር ካለፉት ስድስት የውድድር ዘመኖቹ በሁለቱ ላይ እስከግማሽ ፍፃሜ መድረስ ችለው የነበረ ሲሆን፣ በ2008-09 የውድድር ዘመን ደግሞ በፍፃሜው በቼልሲ ተሸንፈዋል።

ሊቨርፑሎች ደግሞ በዚሁ ውድድር በ2006 ዋንጫውን ካነሱ በኋላ ዳግመኛ ዋንጫውን የማግኘት ዕድል እስከሁን አላገኙም።

የቡድን ዜናዎች

በታፋው ላይ በገጠመው ጉዳት ፊሊፔ ኮቲንሆ በዚህ ጨዋታ ላይ ለሊቨርፑል ይሰለፋል ተብሎ አይጠበቅም።

በሌላ በኩል ክሎፕ ከሌስተር ጋር ባዳረጉት ጨዋታ የብሽሽት ጉዳት የገጠመው እና ትናንት ምሽት የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን ለመቀበል ወደጋና ያቀናው መሐመድ ሳላህ በዚህ ጨዋታ ላይ ይሰለፋል ተብለው የማይጠበቅ ተጫዋቾች ናቸው።

ምንም እንኳ የርገን ክሎፕ የክለቡ ክብረ ወሰን በሆነ የዝውውር ዋጋ ያስፈረሙትን ቪርጂል ቫን ዳይክን በችኮላ ወደጨዋታ እንዲገባ እንደማያደረጉት ቢናገሩም የመጀማሪያ የሊቨርፑል ጨዋታውን ግን በዚህ ጨዋታ ይጀምራል ተብሎ ግን ይታሰባል።

ሊቨርፑል በሰኞ ምሽቱ ጨዋታ ሰባት ተጫዋቾችን ቀይሮ መግባቱ የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ምሽት ጨዋታም ተመሳሳይ ለውጥ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ማርክ ግሩጂች እና ዳንኤል ስተሪጅ ወደጫዋታ ሊመለሱ የሚችሉ ተጫዋቾች ሲሆኑ፣ ናትናኤል ክላይን፣ ጆርዳን ሄንደርሰን እና አልቤርቶ ሞሬኖ ግን አሁንም በጉዳት ምክኒያት በዚህ ጨዋታ ላይ አይሰለፉም።

እንደሊቨርፑል ሁሉ ኤቨርተኖችም ባለፈው ጨዋታቸው ሰባት ተጫዋቾችን ቀይረው ገብተዋል።

ለረጅም ጊዜያት ከሜዳ ርቆ የቆዩት ፉኔስ ሞሪ፣ ሲመስ ኮልማን እና ሌየተን ቤንስ አሁንም ከሜዳ እንደራቁ የሚቆዩ ሲሆን ሮዝ ባርክሌይ ግን ዳግም ወደጨዋታ ሊመለስ ይችላል።

ግምታዊ አሰላለፎች

የሊቨርፑል ግምታዊ አሰላለፍ

የኤቨርተን ግማዊ አሰላለፍ

አሰላጣኞቹ ምን አሉ?

የርገን ክሎፕ: “[ውጤቱን] እንፈልገዋለን። አንዳች ነገርን ለሚያልሙት ደጋፊዎቻችን ምን ማለት እንደሆነም እናውቃለን። በእንደዚህ አይነት ነገሮች ላይም ስስታሞች ነን። ነገር ግን ይህን የምናስመሰክረው በሜዳ ላይ መሆን አለበት። በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኤፍኤ ዋንጫውን ላሸንፍ አልችልም።”

ሳም አላርዳይስ: “ይህ የዋንጫ ጨዋታ ነው፤ ከፕሪሚየር ሊጉም ይለያል። ጫናው ዝቅ ያለ ነገር ግን የክብር ጨዋታ ነው። ክብር በመሻት ለማሸነፍ ጥረት የምታደረግበት ጨዋታ ነው። ማለፍ ካለብን ደግሞ ሊቨርፑልን ማሸነፍ ይኖርብናል። አቻ በቂ አይደለም።”

የጨዋታው ዳኞች

ዋና ዳኛ: ቦብ ማድሌ ረዳት ዳኞች: ማርክ ፔሪ፣ አድሪያን ሆልሜስ፣ አራተኛ ዳኛ: ጆናታን ሞስ


Advertisements