ስኬት / ቼልሲ የሮዝ ባርክሌይን ዝውውር አጠናቀቀ

ቼልሲ በ 15 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ ባሳለፍነው ክረምት የከሸፈበትን የኤቨርተኑን እንግሊዛዊ አማካኝ ሮዝ ባርክሌይ ዝውውር በስኬት ማጠናቀቅ ችሏል።

የ 24  አመቱ ኮከብ በምዕራብ ለንደኑ ክለብ የአምስት አመታት የውል ስምምነት መፈራረም የቻለ ሲሆን በሰማያዊዎቹ ቤትም ስምንት ቁጥር መለያን የሚለብስ ይሆናል።

ባርክሌይ ከስምምነቱ መጠናቀቅ በኋላም “በጣም ተደስቻለሁ። ወደፊት እየተመለከትኩኝና አዲስ ነገር ለመጀመር በጣም ጉጉት ላይ ነኝ። እንደቼልሲ ባለ አዲስ ቡድን ነገሮችን እንደአዲስ መጀመር ለእኔ የማይታመን ነው።

“በተጠናቀቀው (2017) አመት ያልጨረስኩትን ስራ ለመቀጠል፣ ለመሻሻል እና በማደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ብዙ ግቦችን ለመጨመር አስቤያለሁ።” በማለት በዝውውሩ መሳካት የተሰማውን የደስተኝነት ስሜት ገልጿል።

ባርክሌይ ገና በዚህ ለጋ እድሜው ለኤቨርተን 150 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን አድርጎ 22 ግቦችን ያስቆጠረና በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ደግሞ በአለም እና በአውሮፓ ዋንጫ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ መካተት የቻለ ባለብዙ ልምድ ተጫዋች ነው። 

አዲሱ የሰማያዊዎቹ ፈራሚ ካለው ልምድ በተጨማሪ በሁለገብ ተጫዋችነቱ የተነሳ ከአጥቂ ጀርባ፣ በመሀል አማካኝ እና በክንፍ ሚና ላይ መጫወት መቻሉ እንዲሁም ደግሞ ኳስን ለማግኘትና ለቡድን አጋሮቹ የግብ እድል ለማመቻቸት ያለው ጥንካሬ በቀጣይ ቼልሲን በትልቁ እንደሚጠቅመው ይጠበቃል።  

ባርክሌይ ባሳለፍነው ነሀሴ የገጠመው የጅማት ጉዳት ከጨዋታ ውጪ አድርጎት ከመቆየቱ ጋር በተያያዘም ወደሜዳ ሲመለስ ለአዲሱ ቡድኑ በአራቱም ውድድሮች ላይ ተሰልፎ መጫወት የሚችል መሆኑ ለሰማያዊዎቹ ሌላ ተጨማሪ በረከት ይሆናቸዋል። 

Advertisements