ስኬት / ግብፃዊው መሀመድ ሳላህ የ2017 የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተመረጠ

በጋና ርዕሰ መዲና በሆነችው አክራ ምሽት ላይ በተደረገው ፕሮግራም ግብፃዊው የሊቨርፑሉ የምርጥ የግራ እግር ባለቤት መሀመድ ሳላህ ሳዲዮ ማኔ እና ፒየር ኤምሪክ ኦቦሚያንግን አስከትሎ የ 2017 የ ካፍ የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተመረጠ።

የ 25 አመቱ ተጫዋች በተጠናቀቀው 2017 ስኬታማ ጊዜን ማሳለፍ ችሏል።ከሀገሩ ጋር ከ 27 አመት በኋላ ወደ አለም ዋንጫ የተመለሰው በዚሁ አመት ነበር።

ጋና፣ኮንጎ እና ዩጋንዳ በነበሩበት ጠንካራው የምድብ ማጣሪያ ቀደም ብሎ ወደ ራሺያ እንዲያቀኑ ያገዘው መሀመድ ሳላህ ነበር።

በተለይ ከኮንጎ ጋር ሲጫወቱ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር የተጫወተው ሚና ትልቅ በመሆኑ በሀገሩ እንደ ጀግና እየታየ ይገኛል።

ተጫዋቹ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሮማን ለቆ ወደ ሊቨርፑል ሲቀላቀል ጠንካራ እና የሰውነት ንክክ በሚበዛበት ሊግ ላይ ሊከብደው እንደሚችል ተጠብቆ ነበር።

ነገር ግን ከሊቨርፑል ጋር በግሉ እጅግ ያማረ ቆይታን እያደረገ ይገኛል።ከወዲሁ 17 ጎሎችን በማስቆጠር የኮከብ ጎል አግቢነቱን እየመራ ይገኛል።

“ከ 28 አመት በኋላ ወደ አለም ዋንጫ መመለሳችን የተሰማን ያችን ስሜት ለመግለፅ ይከብዳል።ከክለቤ ሮማ እና ሊቨርፑል ጋራም ጥሩ አመትን አሳልፊያለው።ይህ ለኔ ትልቅ ሽልማት ነው።በእግርኳስ ህይወቴም የተለየ ወቅት ነው።” ሲል ሳላህ ከሽልማቱ በኋላ ተናግሯል።

ሳላህ የ 2017 የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች ለመሰኘት አብረውት የተወዳደሩት የቡድን አጋሩ ሳዲዬ ማኔ እና የዶርትሙንዱ ፒየር ኤሚሪክ ኦቦሚያንግ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

ግብፆቹ በዚህ ብቻ አላበቁም ብሄራዊ ቡድናቸው የአምቱ ምርጥ ብሄራዊ ቡድን ሲባል የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አርጀንቲናዊው ሄክቶር ኩፐር ደግሞ የአመቱ ምርጥ አሰልጣኝ ሆነው ተመርጠዋል።

የ2017 የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ የሆነው የሞሮኮው ዊዳድ ካዛብላንካ በበኩሉ የአመቱ ምርጥ ክለብ ተሰኝቷል።

Advertisements