ኢብራሂም ሻፊ / የትጉሁና አገር ወዳዱ ሰው ልብ ሰባሪ ስንብት

‘ኢብሮ’ በሚል ተቀፅላ ይጠራ የነበረውና የስፖርት ጋዜጠኛ፣ የፓለቲካ እና መሰል ጉዳዮች ተንታኝ እንዲሁም መምህር በመሆን ያገለገለው ኢብራሂም ሻፊ የሚወዳትን እና የሚሳሳላትን ሀገሩን ዳግም መመልከት ላይችል ባሳለፍነው ረቡዕ በስደት በነበረበት ኬንያ ናይሮቢ ላንጋታ አውራጃ ከዚህ አለም በሞት የተለየ ሲሆን ባሳለፍነው አርብ ቀትርም ኮልፌ በሚገኘው የሙስሊም መቃብር ግብዓተ መሬቱ ተፈፅሟል። ሚኪያስ በቀለም በቀጣዩ ፅሁፉ የትጉሁንና ሀገር ወዳዱን ጋዜጠኛ የህይወት ዘመን ገድል እና ልብ ሰባሪ ስንብት እንደሚከተለው በዝርዝር ይነግረናል።


በአዲስ አበባ ጣሊያን ሰፈር ተወልዶ ጨርቆስ እንዳደገ የሚነገርለት የፖለቲካ ሳይንስ ምርቁ ኢብራሂም ከስነዜጋና ስነምግባር (ሲቪክስ) መምህርነቱ በተጓዳኝ ለስፖርት (በተለይም ለእግር ኳስ) ያለው ጥልቅ ፍቅር እና የበዛ እውቀት በተለያዩ የሀገራችን የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሀን ዝግጅቶች ላይ ሀገሩን በትጋት እንዲያገለግል ምክንያት እንደሆነው ይነገራል።

በዚህም መሰረት ለብዙ አመታት የሰራበትንና ትልቅ አሻራ ያሳረፈበትን ‘ኢትዮ ስፖርት’ ጋዜጣ በዋና አዘጋጅነት ጭምር የመራ ሲሆን በማራቶን ጋዜጣ እንዲሁም ደግሞ ለተወሰኑ ጊዜያት ቢሆንም በስፖርት አለም አቀፍ ጋዜጣ በዋና አዘጋጅነት ያቀርባቸው የነበሩ የስፖርት ትንታኔዎች በብዙ የሀገራችን የስፖርት አፍቃሪያን ልብ ውስጥ ስሙን እንዲሰርፅ አድርጎታል።

ኢብሮ የስራ ዘመኑን አብዛኛውን ጊዜ ባሳለፈበት ኢትዮ ስፖርት ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን በእግር ኳስ ላይ ትኩረት በማድረግ ሁልጊዜም የሚታወስ ግልጋሎትን ማበርከት ችሏል። (ምስል : ከማህበራዊ ሚዲያ የተገኘ)

ኢብራሂም በጊዜ ሂደት ከስፖርት ጋዜጠኝነቱ ፈቀቅ በማለትም በሮዝ አሳታሚ ትታተም በነበረው ሮዝ መፅሄት በኋላም አዲስ ጉዳይ መፅሄት ላይ በምክትል አዘጋጅነት ሚና በብዛት በሀገር ውስጥ ስፖርት ላይ ባተኮሩ ረጃጅምና ጥልቅ ዳሰሳዎቹ እንዲሁም ምልከታዎች ጉልህ ስራዎችን ማበርከት የቻለ ሲሆን ከስፖርቱ ፈቀቅ በማለትም ሸንቆጥ በሚያደርጉ የፖለቲካ ትንተናዎቹ ሀገሩን ማገልገል ችሏል።

ከዚህ በተጓዳኝም ኢብራሂም በኤፍኤም 97 ላይ የሀገራችን አይረሴና ብርቅ የእግር ኳስ ትንታኔ ባለሙያዎች ከነበሩት አብይ ተክለማርያም እና ፍስሀ ተገኝ ጋር ያቀርቡት የነበረው “ቶክ ስፖርት” የተሰኘ የስፖርት ዝግጅት በብዙ የስፖርት ተከታታዮች የሚደመጥ ተወዳጅ ዝግጅት ነበር።

ከአመታት በኋላም ኢብሮ በሸገር ኤፍኤም ላይ ‘ኳስ ሜዳ’ የተሰኘው የስፖርት ፕሮግራምን ከባልደረቦቹ እንዳልክ ጥላሁን እና አብይ ወንዲፍራው ጋር ይዞ መምጣት የቻለ ሲሆን ‘እንዳልክና ማህደር’ በሚሰኘው የመዝናኛ ፕሮግራም ላይም ይሰራ ነበር።

የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርን በስራ አስፈፃሚነት ያገለገለውና ከሁሉም ጋር ተግባቢ የነበረው ኢብሮ በሸገር ኤፍኤም በሚቀርበው የቀጥታ እግር ኳስ ስርጭት ላይ በነበረው ጥልቅ ትንተናና እይታው ተለይቶ ይታወሳል።

ትጉሁ ኢብሮ የሚወደውን የጋዜጠኝነትና ስፖርት ለማገልገለም ከሌሎች የሚዲያ አካላት ጋር በመሆን የስፖርት ማህበርን በበላይ አመራርነት ለማገልገል ጥረት አድርጓል። (ምስል : ከአዲስ ዘመን ድረገፅ የተገኘ)

በ 2006 ዓ.ም ኢብራሂም በምክትል አዘጋጅነት ያገለግልበት የነበረውን ‘አዲስ ጉዳይ’ መፅሄት ጨምሮ በወቅቱ በነበሩ አምስት የሀገራችን መፅሄቶችን ላይ መንግስት “ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ በማሰብ ሲንቀሳቀሱ ነበር” በሚል ክስ የመሰረተባቸው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ መፅሄቷ ህትመት ለማቋረጥ ስትገደድ ኢብሮም ከሌሎች አራት የስራ ባልደረቦቹ ጋር ስደትን መርጦ ሀገሩን ለቆ ለመሄድ ተገዷል።

የጋዜጠኛ ኢብራሂም ሞት ከተሰማ በኋላ በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቁ መረጃዎች እንዳሳዩት ከሆነም በ1997 ከተካሄደው ምርጫ ጋር በተያያዘ እስረኛ በነበረበት ሸዋሮቢት ከነበረው ቆይታ ጋር በተያያዘ የደረሰበት የጉልበት ህመም ለህልፈት ለተዳረገበት በሽታ መንስዔ እንደሆነው የተገለፀ ሲሆን በተለያየ ጊዜም በአዲስ ጉዳይ መፅሄት አብረውት ይሰሩ የነበሩት ሀብታሙ ስዩምን የመሳሰሉ ጓደኞቹ በስሙ ገንዘብ አሰባስበው ሊያሳክሙት ቢያስቡም ፍቃደኛ ሳይሆን መቅረቱ ተያይዞ ተነግሯል።

ኢብሮ በስደት በቆየበት ኬንያ የጉልበት ህመሙ ከሀገሩ ፍቅር ጋር ተዳምሮ እጅግ ይፈትነው እንደነበር በቅርበት እናውቀዋለን የሚሉ ሰዎች ምስክርነታቸውን የሰጡለት ሲሆን ኬንያን ለቆ ወደ አውሮፓና አሜሪካ የመሄድ እድሉንም በህመሙ የተነሳ የህክምና ቀጠሮው ላይ መገኘት ባለመቻሉ እንዳመለጠው በማህበራዊ ሚዲያው በሚለቀቁ ፅሁፎች ተወስቶለታል።

ኢብሮ የመጨረሻ ቀናቱ የጠቆሩና ተስፋ መቁረጥ ያረበባቸው እንደነበሩ የሚያሳብቁ አይነት ነበሩ። (ምስል : ከማህበራዊ ሚዲያ የተገኘ)

ከዚህ በተጨማሪም የሀገሩ ጥልቅ ፍቅር የማያስችለው ኢብራሂም ለሁለት ጊዜያትም ወደእናት ሀገሩ ኢትዮጵያ ለመመለስ ሞክሮ እንዳልተሳካለት አንዳንድ ያልተረጋገጡ መረጃዎች ያሳዩ ሲሆን ከህልፈቱ ቀደም ባሉት ወራት እየከረረ የመጣበትና ከወቅቱ ብርዳማ አየር ጋር በተያያዘ ትልቅ ህመም የፈጠረበት የጉልበት ጉዳትም በመጨረሻ የህይወቱ ቀናት እጅግ እንደፈተነው እና በጣም ተስፋውን አዳክሞት እንደነበር አንዳንድ ወዳጆቹ በማህበራዊ ገፆቻቸው ይፋ ባደረጉትና ከእልፈቱ ቀናት በፊት ከእሱ ጋር በተለዋወጡት የመልዕክት ልውውጥ ላይ ታይቷል።

ኢብራሂም በስደት ላይ በነበረበት ጊዜም ያደገበትን የጨርቆስንና የሀገሩን ናፍቆት ለማስታገስ በመፅሀፈ ፊት (ፌስቡክ) ገፁ ትውስታዎቹን የሚያጋራበትና በኢትዮጵያ ፓለቲካዊ እና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ሀሳቡን ያንፀባርቅበት የነበረበት መንገድ በሀገር ውስጥ ሳለ በፅሁፎቹ ይወዱት ከነበሩት አድናቂዎቹ እንዳይራራቅ እገዛ አድርጎለት ነበር።

በስደት ላይ ሳለ የተለያዩ እገዛዎች እንዲደረግለት ሲጠየቅ አሻፈረኝ ይልና ከራሱ ይልቅ ለሌሎች ቅድሚያ እንዲሰጥ ይጠይቅ እንደነበር ቤተኛው እንደሆኑ በሚገልፁ ወዳጆቹ የተነገረለት ታታሪውና ሀገር ወዳዱ ኢብራሂም በክለብ ደረጃ የቀደመ ዝናውን ላጣው ለነጭና ጥቁር ዥንጉርጉር መለያው ኒውካስትል በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ደግሞ ለሶስቱ አናብስት እንግሊዞች የጠለቀ ፍቅር ነበረው።

አርቆ አሳቢው ኢብራሂም ከዩንቨርስቲ ተመርቆ ሲወጣ ባሰፈረው የመጨረሻ ቃሉ የበዛ የቤተሰብና የአገር አደራ እንዳለበት ቢያውቅና ምኝቶቱ ከፍተኛ እንደሆነ ቢገልፅም ያሰበውን ያህል መጓዝ ሳይችል እንደወጣ ቀርቷል። (ምስል : ከማህበራዊ ሚዲያ የተገኘ)

በመጨረሻ ግን ገና ሮጦ ሳይጠግብ፣ ከሚወደው ሙያ ተገሎና ተሰዶ እንዲሁም ከልቡ ይወዳት የነበረውን ሀገሩን ዳግም ሳያገኛት በሰው ሀገር ይፈትነው የነበረው የእናት ሀገሩ ፍቅርና ያመረቀዘበት የጉልበት በሽታው ዳግም ድምፁን ላንሰማው፣ መልኩን ላናየው እና ፅሁፉን ላናነብ ከፍቃዱ ውጪ ሞት ጨክኖ እስከወዲያኛው አይኑን ጨፍኖብን እስትንፋሱን ቀጥ አድርጎታል።

ነገርግን ለነበረው የበዛ መልካምነት እንዲሁም ላበረከተልን የማይዘነጉ ስራዎቹ ነፍሱ በሰላም ታርፍ ዘንድ የቀድሞ የስራ ባልደረባውና በስደት የሚገኘው የቅርብ ወዳጁ ሀብታሙ ስዩም በማህበራዊ ገፁ ያሰፈረውን አስታውሰን ነፍስ ይማር ብለን እንለያይ። “ዓይኖችህ በተከደኑ አፍታ – የገነት በሮች ሲከፈቱልህ ታውቆኛል፡፡ ወንድማለም እዚያ የማገኘህ ይመስለኛል፡፡ እስከዚያው ደህና ሁን ጓደኛዬ፡፡”  

ኢብራሂም ከቀድሞ የአዲስ ጉዳይ ባልደረባውና የስደት አጋሩ ጋር ወዳጅነቱን እንደጠበቀ የስዩሜን ልብ በሰበረ መልኩ ተለይቶት ላይመለስ ሄዷል። (ምስል : ከማህበራዊ ሚዲያ የተገኘ)

የኢብሮን ህልፈት ተከትሎ ተመርጠው የቀረቡ የወዳጆቹና አድናቂዎቹ የማህበራዊ ሚዲያ አስተያየቶች  

“የኢብሮ የመጨረሻ ቃል – ‘ካስዬ እባክህ ጥሩ ስሜት ላይ አይደለሁም … አዝኛለሁ … ደብሮኛል …ጉልበቴን አሞኛል …’ ሲለኝ ‘ኢብሮ ታዲያ መታከሚያ ገንዘብ…’ ንግግሬን አላስጨረሰኝም ‘ካስሽ እኔ ምንም አልፈልግም’ አለኝ። እና አሁን ላይመለስ ጥሎ ሄደ።”ካሳሁን ይልማ (ጋዜጠኛና የቅርብ ወዳጅ)

“አንዳንዴ ሞትን ሞት ቢገለው ምን አለበት።” – ሀብታሙ ምናለ (ጋዜጠኛ)

“ኢብራሂም የሚጽፋቸውን የስፖርት ትንታኔዎች አንድም እንከን አውጥቼላቸው አላውቅም። ስለኳስ ሲጽፍ እኔን መሰል ከኳስ እውቀት የጸዳ ሰው እንኳን ቀልብ መሳብ የሚችል ገራሚ ልጅ ነው። ጽሁፎቹ ደግሞ በዘፈቀደ ያለአላማ የሚጻፉ አይደሉም። ግብ አላቸው።ተጽዕኖ ይፈጥራሉ። በተለይ እግር ኳሱ አካባቢ የኢብራሂም ጽሁፎች ክፍተት አመላካችና አቅጣጫ ጠቋሚ ተደርገው እንደሚወሰዱ የሚገባኝ አንድ ጽሁፍ በጻፈ ማግስት ጽሁፉ ያነጣጠረበት አካባቢ ላይ የሚፈጠረውን ለውጥ እና ግርግር ስመለከት ነው።

ኢብሮ ዛሬ ረፋድ ከኬንያ ወደሀገር ውስጥ የገባው አስከሬኑ ቀትር ላይ በኮልፌ የሙስሊም መቃብር እንዲያርፍ ተደርጓል።

“ኢብራሂም ስለኳስ በተለይም ስለብሄራዊ ቡድናችን ሲጽፍ እኔ የማየው እንደአስራ ሁለተኛው ኳስ ተጫዋች ነው። …. ኢብራሂም ከስፖርት ውጪ የፖለቲካና የማህበራዊ ጉዳዮች ተንታኝ ሆኖ ብዙ ሰርቷል። የሱን ጽሁፍ አንድም እንከን አግኝቼበት አላውቅም። ጽንፍ አይይዝም። ቂም የለበትም። የራሱን አስተያየት በጽሁፎቹ አያካትትም። አላማው እውነታውን ማሳየት ብቻ ነበር። ፍርድን የሚተወው ለአንባቢ ነው። ኢብራሂም ጋዜጠኝነትን ብቻ የሰራ ጋዜጠኛ ነበር።

“ኢብራሂም ሲራመድ እግሩን ጥቂት ጎተት ያደርጋል። መኪና ላይ ለመውጣት ይቸገራል። … የህመሙ ምስጢር ምን እንደሆነ ያወቅኩት ግን ዛሬ ነው ። ‘ተገርፎ ነው’ የሚል ነገር አንብቤያለሁ። እኔ ሶስት አመት ሳውቀው አንድም ቀን ስለዚህ ጉዳይ ሲያነሳ ሰምቼው አላውቅም። ይልቅስ በአንድ የእጁ ጣት ጥፍር ላይ ላይ ስለወጣበት ጥፍረመጥምጥ እያነሳ በራሱ እየቀለደ ሲያወራ ነው የምሰማው።” – መላኩ ብርሀኑ (ጋዜጠኛ)

“እግር ኳስ ስራዬ ቢሆንም እንደ ኢብሮ ያህል ግን ኳስ እወዳለው ማለት አልደፍርም! ሀገሬን ይል ነበር ….ኳስን ይል ነበር።” – መንሱር አብዱልቀኒ (የቀድሞ የስራ ባልደረባና ጓደኛ)

“ባልደረባችን፣ ጓደኛችን፣ ወንድማችን ኢብራሂም ሻፊ (ኢብሮ) በርካቶች በስፋት ከሚያውቁለት በሳል የስፖርት ጋዜጠኝነቱ እና የስፖርት ክንውኖች ትንታኔ ልዩ ክህሎቱ ባሻገር የፖለቲካ ሳይንስ ምሩቁ ኢብሮ በበርካታ አገራዊ ሆነ ዓለምአቀፋዊ የፖለቲካ፣ ማሕበራዊ ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ላይ በጋዜጠኝነት ሙያው የድርሻውን የተወጣ፣ ለለውጥ የሚሆኑ በሳል ሐሳቦችን በየጊዜው ያመነጨ፣ ያመነበትን ነገር በአደባባይ በመናገር ለዚሁም ዋጋ የከፈለ ብዙ ለአገሩ ሆነ ለወገኑ የሚቸረው የነበረው ተወዳጅ ጋዜጠኛ ነበር፡፡” – የአዲስ ጉዳይ መፅሄት ዝግጅት ክፍል

“ሀበሻ ግን ሲሞት ውድ ነው ! ምናለ በቁም እንዲህ ብንረዳዳ ኢብሮ እንወድሃለን !”ፍፁም ጎሳዬ (የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ)

ኢብሮ በቁሙ ሳለ ማሳከምና ህይወቱን ማቆየት ባንችል እንኳን እሱን ላጡት ቤተሰቦቹ (በተለይም እናቱ) ጥቂት የገቢ ብርታት ይፈጥርላቸው ከሆነ ተብሎ በወዳጁ ጋዜጠኛ ካሳሁን ይልማ አነሳሽነት የተጀመረው የጎፈንድሚ የድረገፅ (online) የገንዘብ ማሰባሰብ በተጀመረ 18 ሰአታት ውስጥ ከ 122 ሰዎች ከ 6,000 የአሜሪካ ዶላር በላይ ማሰባሰብ ተችሏል። (ምስል : ከጎፈንድሚዶትኮም የተገኘ)

“…. በህልፈቱ የመጨረሻ ደቂቃዎች በዙሪያው የነበርን የስደት እና ስራ ዓለም ወንድሞቹ ትልቁ ፈተና የነበረው ደህንነቱን አብዝተው ለሚጠይቁን ቤተሰቦቹ መራሩን ሀዘን ማጋራት ነበር፡፡ ወንድማችን ለሀገሩ ለኢትዮጵያ መሬት ሳይበቃ፣ አስፈላጊው ሃይማኖታዊና የወግ ቅድመ ዝግጅት ሣይጠናቀቅ ድንገተኛ ስንብቱ ተሰምቶ በቤተሰቦቹ በተለይም በሚወዳቸው እናቱ ዘንድ ከበድ የመንፈስ ጉዳት እንዳይፈጥር በማሰብ እስከ ዛሬ ድረስ በይፋ ሳናሳውቅ ቆይተናል፡፡ አንዳንድ ወዳጆቹ ቀድሞ የተሰማው መረጃ በማህበራዊ ሚዲያዎች ከማጋራት ለተወሰነ ጊዜ እንዲታገሱን ስንለምን የነበረበት ምክንያት ከዚህ አንጻር ነው፡፡ ልመናችንን ሰምታችሁ ለተባበራችሁን ሁሉ ምስጋናችን ልባዊ ነው፡፡” – ሀብታሙ ስዩም (የቀድሞው የአዲስ ጉዳይ መፅሄት ባልደረባና ጓደኛ)

“ወዳጄ! ኢብራሂም ሻፊ ኢብሮ ልባችን ተሰብሯል ወንድሜ ፈጣሪ ነፍስህን በሰላም ያሳርፋት።” – ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)

“… ዛሬ ሞቱ ላይ ቆሜ የትናንት ሕይወቱን ሳየው እቆጫለሁ። ምን ነበረ እንደሌሎቹ ጓደኞቹ በስፖርት ዘርፍ ብቻ ተወስኖ የስፖርት ጋዜጠኛ ብቻ ተብሎ በቀረ እላለሁ። እንደማይሰደድ አስባለሁ። እንደማይንገላታ እርግጠኛም እሆናለሁ። እንደማይሞት ግን እርግጠኛ መሆን አልቻልኩም። ኢብራሂም ሻፊ ግን እንደእኔ አይደለም። ይኸው በሞቱ እርግጠኛ መሆን ቻለ። ይኸው ለእውነተኛ ጋዜጠኝነት፣ ይኸው ለእውነተኛ ኢትዮጵያዊነት ሲል ተሰደደ። ቤተሰቡን ሀገሩን ጥሎ ሄደ። በመጨረሻም ሕይወቱን ከፈለ። ምንም ተባለ ምን አሁን ኢብራሂም ሻፊ በሕይወት አይመለስም። ነፍሱን ይማር ! ጽናቱን ይስጠን !ኢትዮጵያዊነት እስከዛሬ ያበበው፣ ወደፊትም የሚያብበው ፣ እንደኢብራሂም ባሉ ወጣት አበቦች መርገፍ ነው። …” – ፋሲል ተካልኝ አደሬ (የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ አስተያየት)

😭 በመጨረሻም የኢትዮአዲስ ስፖርት ዝግጅት ክፍል የታታሪውንና ተወዳጁን የስፖርት ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ ያልተጠበቀ ሞትን ተከትሎ የተሰማውን ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቹ፣ ለአድናቂዎቹ እንዲሁም ደግሞ ህይወቱን ለሰጠላት ሀገሩ መፅናናትን ይመኛል። ኢብሮን በሞት ያጡ ቤተሰቦቹን (በተለይም እናቱን) መደገፍ የምትፈልጉ ካላችሁም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሂሳብ ቁጥር 0173018922800 ፋጡማ ሻፊ አህመድ ብላችሁ የቻላችሁትን ማድረግ ስትችሉ በድረገፅ እንቅስቃሴውን መርዳት ለምትፈልጉም ይህንን ማስፈንጠሪያ (ሊንክ) ከፍታችሁ የበኩላችሁን እገዛ ማበርከት ትችላላችሁ።

Advertisements