የፊርሚኖ ማስረጃ ያልቀረበበት የዘረኝነት ክስ ሊቨርፑል በኤቨርተን ላይ በተቀዳጀው ድል ላይ ጥላውን አጥልቷል

የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር የኤቨርተኑ ተከላካይ ማሰን ሆልጌት ሊቨርፑል በኤፍኤ ዋንጫ ጨዋታ በአንፊልድ ድል በተቀዳጀበት ጨዋታ በሮቤርቶ ፊርሚኖ የዘረኝነት ጥቃት እንደተሰነዘረበት ያቀረበውን ክስ ይመለከታል ተብሎ ይጠበቃል።

ቀዮቹ 2ለ1 ማሸነፍ በቻሉበት የአርብ ምሽቱ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ሄልጌት የሊቨርፑሉን የፊት ተጫዋች ወደማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ መገፍተሩን ተከትሎ ከተጫዋቹ ጋር ግጭት ውስጥ ገብቷል። ፊርሚኖም ወደኤቨርተኑ ተከላከይ በማምራት በከፍተኛ ስሜት ቁጣውን በተጫዋቹ ላይ ገልፅዋል። ሆልጌትም በብራዚላዊው ተጫዋች የቀረበበት የቁጣ ንግግር በእጅጉ እንዳበሳጨው ታይቷል። የቡድን አጋሮቹም እንዲረጋጋ አድርገውት የዘረኝነት ጥቃት የደረሰበት የሚመስለውን አቤቱታውን ለጨዋታው ዳኛ ሮበርት ሜድሊ አቅርቧል። ሜድሊም የተጫዋቹን አቤቱታ ለአራተኛው ዳኛ ጆን ሞስ ካቀረቡ በኋላ ጨዋታው እንደተጠናቀቀ የ21 ዓመቱን ተጫዋች ዳግመኛ አነጋግረውታል።

የሆልጌት ማስረጃ የለሽ ክስም ተጨማሪ እንቅስቃሴ አስፈለጊ መሆን አለመሆኑ ለሚወስነው የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር ለመቅረብ በማድሊ የጨዋታ ሪፓርት ላይ ይሰፍራል ተብሎም ይጠበቃል።

የሊቨርፑል ክለብ ቃል አቀባይ ጉዳዩን አስመልክተው “ክለቡና ተጫዋቹቹ እውነታው ይፋ እንዲሆን የግድ አስፈላጊ ከሆነና ጥያቄ የሚቀርብ ከሆነ ለሚመለከተው የስልጣን አካል ሙሉ ትብብር የሚያደረጉ ይሆናል። ጉዳዩ በሂደት ላይ ባለበት ሁኔታ ተጨማሪ አስተያየት አንሰጥም።” ብለዋል።

ፊርሚኖ ከጭዋታ በኋላ ስጉዳዩ እንዲያብራራ ጥያቄ ባይቀርብለትም ነገር ግን የእግርኳስ ማህበሩ በጨዋታው ሪፖርት ላይ ተንተርሶ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ አለማድረጉን ውሳኔ የሚያሳልፍ ይሆናል።

የኤቨርተኑ አሰልጣኝ ሳም አላርዳይስ “የትኛውንም ዘዴ በመጠቀም በትክክል የተከሰተው እና ያልተከሰተው ነገር እስኪደረስበት ደረስ ምን ልላችሁ አልችልም። እዚህ የተገኘሁት ስለእግርኳስ ለመናገር እንጂ ስለአወዛጋቢ ጉዳዮች ለመናገር አይደለም። ምክኒያቱም እግርኳስ ህይወቴ ነው። ከእግርኳስ ውጪ ያለውን ነገር ሊመለከተው የሚገባው የሚመለከተው ባለስልጣን መሆን ይኖርበታል። [ከሆልጌት ጋር] ተነጋገርኩም አልተነጋገርኩ በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለማንም አልናገርም። ይህ የሚመለከታቸው ሌሎች ናቸው። ይህንን ለእግርኳስ ዳይሬክተሩ የምተወውና ጉዳዩን እንዲያጣራ የምነግረው ይሆናል።” በማለት ስለጉዳዩ ተጨማሪ አስተያየት ከመስጠት ቢቆጠቡም የኤቨርተን የእግርኳስ ዳይሬክተር የሆኑት ስቲቭ ዋልሽ ግን በክለቡ የሚዲያ ክፍል በኩል ስለጉዳዩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ርገን ክሎፕም በበኩላቸው ጉዳዩን አስመልክተው “አንድ ነገር ሰምቻለሁ። ነገር ግን ከዚህ በላይ ልለው የምችለው ነገር የለም። አራተኛው ዳኛ የሆነ ነገር ነግሮኛል። የተናገራቸውን ቃላት ፈፅሞ ስላልሰማኋቸው ሆልጌት የፈፀመውን ጥፋት የሚመረምሩት መስሎኝ ነበር። በመጀመሪያ የገባኝም ይኸው ነው። ከጨዋታው በኋላ ግን አራተኛው ዳኛ [ጉዳዩን] አሳወቀኝ። ነገር ግን መጀመሪያ የተረዳሁት ያን አልነበረም።” ሲሉ ጉዳዩን ገልፃዋል።

Advertisements