ይፋዊ / ባርሴሎና ፍሊፔ ኮቲንሆን ከሊቨርፑል ማስፈረሙን ይፋ አደረገ

ብራዚላዊው አማካይ ፍሊፔ ኮቲንሆ ወደ ካታላኑ ባርሴሎና ለማቅናት በሁለቱ ክለቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረው የዝውውር ሂሳብ ልዩነት በመጨረሻም በ 142 ሚሊየን ፓውንድ ለስምምነት እንዳበቃቸው ቢቢሲን ጨምሮ ሌሎች ታማኝ የመገናኛ ብዙሀን አመሻሹ ላይ በስፋት መረጃውን ይዘው ከወጡ በኋላ ባርሴሎና በይፋ ተጫዋቹን “እንኳን ደህና መጣህ” በማለት ዝውውሩ ማጠናቀቁን አሳውቋል።

ድንቅ ችሎታ እንዳለው ከቀዮቹ ጋር በሚገባ ማስመስከር የቻለው ኮቲንሆ ባሳለፍነው የክረምቱ የዝውውር መስኮት ዝውውሩን ገፍቶ መልቀቂያ እስከ መጠየቅ ደርሶ ነበር።

ኮቲንሆን በወቅቱ በኢሜል ለቀዮቹ በይፋ የልቀቁኝ ጥያቄ ካቀረበ ቦሀላ ባርሴሎናዎች ዝውውሩን ለማጠናቀቅ ላይ ታች ቢሉም በዝውውሩ ሂሳብ ላይ መስማማት ሳይችሉ ቀርተዋል።

ባርሴሎና ሶስት ጊዜ የተሻሻለ ሂሰብ ቢየቀርብም ከኔይማር እና ከምባፔ [ለጊዜው ዝውውሩ በውሰት ነው]ዝውውር በኋላ ጣሪያ የነካው የተጫዋቾች የዝውውር ሂሳብ ሊቨርፑሎች በኮቲንሆ ላይ ቆፍጠን በማለት ባርሴሎናዎችን ደጅ ሲያስጠኑ ቆይተዋል።

የካታላኑ ቡድን በድጋሚ በጥር የዘውውር መስኮት በመመለስ ዝውውሩን ከዳር ለማድረስ ያደረገው ጥረት ግን በመጨረሻም ፍሬ አፍርቶለታል።

ኮቲንሆ እንኳን ደህና መጣህ!

142 ሚሊየን ፓውንድ ሁለቱን ክለቦች ለስምምነት ያበቃ ሂሳብ መሆኑ ቢቢሲ ስፓርትን ጨምሮ ሌሎች የመገናኛ ብዙሀን መረጃውን ይዘው ከወጡ በኋላ ክለቡ እራሱ ተጫዋቹን”እንኳን ደህና መጣህ”በማለት የዝውውሩን ፍፃሜ ይፋ አድርጓል።

ሊቨርፑልም ጉዳዩን በማስመልከት ያወጣው መግለጫም”ከባርሴሎና ጋር ከስምምነት ላይ በመደረሱ የሊቨርፑል እግር ኳስ ክለብ ፊሊፕ ኮቲንሆ የህክምና ምርመራውን ከፈፀመና ግላዊ ጥቅሞቹን የተመለከቱ ጉዳዮች ካጠናቀቀ በኋላ ክለቡን እንደሚለቅ ለማረጋገጥ ይወዳል። አሁን ተጫዋቹ የተለመደውን ሂደት እንዲፈፅምና ዝውውሩን በቶሎ እንዲያጠናቅቅ ፍቃድ ተሰጥቶታል።” ሲል ተነቧል።

ተጫዋቹ በኑካምፕ 400 ሚሊዮን ዩሮ የሚገመት የዝውውር ማፍረሻ ያለው የአምስት አመታት የውል ስምምነት እንደሚፈራረም የሚጠበቀው ኮቲንሆ በነገው ዕለት አመሻሽ ባርሴሎና ሌቫንቴን ለሚያስተናግድበት ጨዋታ ምናልባትም ሊደርስ እንደሚችል ተያይዞ ተገልጿል።

የክፍያ ሁኔታውም ቀዮቹ በመጀመሪያ 105 ሚሊየን ፓውንድ የሚቀበሉ ሲሆን ቀሪዎቹ ክፍያዎች ለወደፊት በተጨማሪነት[Adds on] የሚከፈሉ ይሆናል።

ሊቨርፑል በውድድር አመቱ አጋማሽ ምክንያት በማድረግ ለጥቂት ቀናት እረፍት ለመውሰድ ወደ ዱባይ ቢያቀኑም በዝውውሩ ምክንያት ኮቲንሆ ከጉዞው ውጪ እንደሆነ ይታወሳል።

በጥር 2013 የጣሊያኑን ኢንተር ሚላን ለቆ ቀዮቹን በ 8.5 ሚሊየን ፓውንድ የተቀላቀለው ኮቲንሆ የዝውውሩን የወረቀት ስራዎች እስከ ሰኞ እንደሚያጠናቅቅ ይጠበቃል።

ነገርግን ከአዲሱ ክለቡ ጋር በመሆን በቻምፕየንስ ሊጉ የጥሎማለፍ ጨዋታ ላይ ቼልሲን ለመግጠም ፈቃድ አያገኝም ምክንያቱም ደግሞ በዚሁ መድረክ ላይ የሊቨርፑልን ማሊያ ለብሶ መጫወት በመቻሉ ነው።

ብራዚላዊው ተጫዋች በአጨዋወቱ በብዙዎቹ ተወዳጅ ሲሆን በተለይም ከግራ መስመር እየተነሳ ከሳጥን ውጪ ጠንካራ ያማሩ ኳሶችን በማስቆጠር ይታወቃል።

ይህ የተለየ ባህሪው ደግሞ በኳስ ንክኪዎች ላይ ላመዘነው የባርሴሎናዎች አጨዋወት ሌላ የጎል አማራጫቸው እንደሚሆን ይጠበቃል።

የዝውውር ሂሳቡ ከኔይማር  በመቀጠል ለአንድ ተጫዋች የወጣ ሁለተኛው ውዱ የዝውውር ሂሳብ ሆኗል።ነገርግን ፔዤ የምባፔን የውሰት ውል በቀጣዩ ክረምት ወደ ቋሚነት የሚቀይረው ከሆነ ዝውውሩ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል።

የአለማችን ከፍተኛ ዝውውር

1) ኔይማር ከ ባርሴሎና ወደ ፔዤ በ200 ሚሊየን ፓውንድ 

2) *ኪሊያን ምባፔ ከሞናኮ ወደ ፔዤ (በቋሚነት ለማዞር የሚያስችል አማራጭ ያለው የውሰት ስምምነት) በ 165.7 ሚሊየን ፓውንድ

3) ፍሊፔ ኮቲንሆ ከሊቨርፑል ወደ ባርሴሎና በ 142 ሚሊየን ፓውንድ

4) ኦስማን ዴምቤሌ ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ወደ ባርሴሎና በ 135.5 ሚሊየን ፓውንድ

5) ፖል ፖግባ ከጁቬንቱስ ወደ ማን ዩናይትድ በ 89 ሚሊየን ፓውንድ ናቸው።

Advertisements