ጅምር / የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አዲስ ሊጀምር ያሰበውን ኤሌክትሮኒክ የስታዲየም ትኬት አሰራር ለመገናኛ ብዙሀን አስተዋወቀ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ‘ክፍያ’ ከተሰኘው የወኪል ክፍያ ፈፃሚ ድርጅት ጋር በጋራ ሊጀምር ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ያለውን የኤሌክትሮኒክስ የስታዲየም ትኬት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሀን አካላት አስተዋውቋል። 

ይህ አዲሱ አሰራር የእግር ኳስ ተመልካቹ ከጨዋታዎቹ ቀናት በፊት ትኬቱን ቀደም ብሎ ቆርጦ የጨዋታው ሰአት ሲቃረብ ብቻ ትኬቱን ይዞ ወደስታዲየም በመምጣት የሚስተናገድበት እና ከዚህ ቀደም የነበረውን የስታዲየም ሰልፍ እና መጉላላት የሚያስቀር አሰራር እንደሆነ ተነግሮለታል።

ለመገናኛ ብዙሀን አካላት ትውውቅ በተደረገበት ስነስርዓት ላይም የፌደሬሽኑ የበላይ አካላትና እና የክፍያ የገንዘብ ተቋም ተወካዮች ተገኝተው ስለአገልግሎቱ በዝርዝር ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን አዲሱ አሰራር የስታዲየሙን ሰልፍ ከማስቀረቱ በተጨማሪ አዲስ አበባ ስታዲየም የሚይዘውን ትክክለኛ የተመልካች ቁጥር ማወቅ የሚያስችልና ዝርፊያና መሰል አላስፈላጊ ድርጊቶችን እንደሚገታ ተጠቁሟል። 

ይህ አዲስ አሰራር የመብራትም ሆነ የኢንተርኔት መቆራረጥ እክል የማይፈጥርበት እንደሆነና በስታዲየሙ ባሉ በሮች ላይ በሚገጠሙና  በቀጥታ ሀይልም ሆነ በተጠባባቂ ሀይል (Charge) በሚሰሩ ቀላል መቆጣጠሪያ ማሽኖች ትኬቱ ላይ ያሉትን መለያ ቁጥሮች (QR Code) በማንበብ የትኬቶቹን ትክክለኛነት በማረጋገጥ ተመልካቹን በተቀላጠፈ ሁኔታ እንደሚያስተናግድ ተያይዞ ተገልጿል።

ይህ የጨዋታ ትኬት በመጪው ጥር  12 ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ስታዲየም ሀዋሳ ከነማ በሚያስተናግድበት ጨዋታ ጥቅም ላይ የሚውል የክቡር ትሪቡን መግቢያ ትኬት ሲሆን በስታዲየሙ መግቢያ በር ላይ የሚገጠሙት የትኬት ማንበቢያ ማሽኖችም በስተቀኝ የምትመለከቱትን በጥቁር ቀለም የተሰራ የሳጥን ቅርፅ መለያ  (QR Code) በማንበብ በሚያገኘው ቁጥር ትኬቱ ትክክለኛ መሆኑን እና ሌላ ደጋፊ ቀድሞ ያልገባበት ያልተጭበረበረ ትኬት መሆኑን አረጋግጠው ተመልካቹን ወደስታዲየሙ የሚያስገቡ ይሆናል።

የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለመጀመር ያሰበው አዲስ አሰራር በሌሎች ሀገራት ላይ ብዙ አመታትን ያስቆጠረና የተለመደ ሲሆን አሰራሩን ይበልጥ ለማዘመንም የስታዲየሙ ታዳሚ በክፍያ ወኪሎች በኩል ከተለያዩ የንግድ ስፍራዎችና ሱቆች የስታዲየም ትኬትን ገዝቶ ከመጠቀም በተጨማሪ በቀጣይ ደህንነቱ አስተማማኝ የሆነ የሞባይል ክፍያ አሰራር ተመቻችቶ ተመልካቹ የሚፈልገውን ጨዋታ በድረገፅ በቀጥታ ከኢንተርኔት (online) ወይም በሞባይሉ እንዲገዛ የሚደረግበት አሰራር እንደሚጀመርም ተወስቷል።

በአዲሱ የትኬት ማስተዋወቅ ዝግጅት ላይ የመገናኛ ብዙሀን አካላት አሰራሩን እንዲሞክሩ ከተደረገበት መርሀ ግብር በኋላም ለፌደሬሽኑና ለወኪል ተቋሙ ወኪሎች ያላቸውን የተለያየ ጥያቄ አቅርበው ከመድረኩ የተብራራ መልስ የተሰጣቸው ሲሆን በአሰራሩ ላይ ያላቸውን ግብረ መልስ እንዲያሰፍሩም ተደርገዋል።

ክፍያ የተሰኘውና ከፌደሬሽኑ ጋር በወኪልነት አገልግሎቱን ለመጀመር የተሰናዳው የወኪል ክፍያ ፈፃሚ ድርጅት የመብራትና መሰል መንግስታዊ የክፍያ አሰራሮችን ለሁሉ በሚባሉት ቅርንጫፎቹ እየሰጠ ያለ እንዲሁም ደግሞ የአውቶብስ ተራን የኤሌክትሮኒክስ ትኬት አሰራር የጀመረ ተቋም መሆኑ በስነስርዓቱ ላይ ተነግሮለታል።

ይህ አዲስ አሰራር በአዲስ አበባ ስታዲየም ተጀምሮ በቀጣይ ወደሌሎች ስታዲየሞች እንዲስፋፋ የሚደረግ ሲሆን አንድ ሰው ከአንድ በላይ ትኬት የመግዛት መብት እንዳለውም ታውቋል።

Advertisements